//የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ//
//የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ// ይህችን አባባል ያስቀደምነው ዛሬ ያነበቡትን ነገ ደግመው ለሚጠይቁ ሰዎች የሚስማማ በመሆኑ ነው። ጥያቄ፦ ለመላዕክት የክብር ስግደት ይገባል ?ይህስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው?
መልስ :-
ቆርኔሌዎስ "ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል። ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው።እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ።ጌታ ሆይ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው። ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ።"ሐዋ.10፡3-4
መላእክት ክብራቸዉ አንዳንዶች እንደሚያስቡት አይደለም።መላእክት ግርማቸዉ እጅግ ድንቅ እና የሚያስፈራ ነዉ።ምክንያቱም የአምላክን ስም ይዘዋልና አምላካቸዉን ለብሰዋልና።"በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት።"ዘጸ.23:20 እንዲል መጽሃፍ።ነገር ግን ሁሌም ሲያረጋጉ አየዞዋችሁ አትፍሩ ነው፡፡እኛም የተዋህዶ ልጆች የአምላክነት ሳይሆን የጸጋ( ከእግዚአብሔር የተሰጠ) ክብር ስለምንሰጣቸው አይዞዋችሁ ይሉናል፡፡የጸጋም ስግደት መጽሃፍ ስለሚያዝ እንሰግድላቸዋልን።
ሆኖም አንዳንዶች ስህተት ነዉ ይሉናል።ለመልአክ ይሰገዳል ወይስ አሰግደም? በእርግጥ ብዙ ቦታ እግዚአብሔር የመረጣቸዉ የቀደሙ አባቶች ለመላእክት ሰገዱ ተብሎ ተጽፋል። እንዚህ አባቶች ሲያመልኩ የነበረዉ እግዚአብሔርን ነዉ ነገር ግን ለመላእክት የአክብሮት የጸጋ ስግደት ሰግደዋል ታድያ እነዚህ አባቶች ተሳስተዋል? እግዚአብሔርን አላመለኩም? ያመለኩት መላእክትን ነዉ ይባል ይሆን?።አልተሳሳቱም ምክንያቱም መረጃዉ የተገኝዉ በመንፈስ ቅዱስ ከተደርሰዉ መጽሃፍ ቅዱስ ነዉና ሁሌም እዉነት ነዉ።ሰማይና ምድር ያልፋሉ እንጂ ቃሌ ግን አያልፍም ብሎናልና።ማቴ.24:35።ነገር ግን አንዳንዶች በራእይ 22:8 ያለዉን የእግዚአብሄር ቃል በመያዝ ትከከለኛ ሚስጥሩን ባለማዎቅ ለመላእክት አይሰገድም ይሉናል።ግልጽ ለማድረግ እስቲ ለእያሱ የተገለጠ መልአክ እና ለዮሃንስ የተገለጠዉን መልአክ በማነጸጸር አብረን እንመልከት።
ኢያ. 5 ፡14 “ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደ” ለመልአኩ።ራእ.22:8 “በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ” እርሱም፦ እንዳታደርገው አለዉ።ካንተ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ አለዉ ::ለምን? አንዳንድ ወንድሞች ራእ.22:8ን ይዘው ለመልአክት አይሰግደም ይሉናል።ምስጥሩ ምንድን ነው? ለኢያሱ የተገለጠ መልአክ ስህተተኛ ነበር? ለምን አትስገድልኝ አላለውም? ለዮሐንስ የተገለጠውስ ለምን አትስገድልኝ አለ? ሁለቱም ጋ መላዕክት ናቸው ሁለቱም ሰዎች ሰግደዋል አንዱ መልአክ ኢያሱ ሲሰግድለት ምንም አላለም ሌላኛው መልአክ ግን ዮሐንስ ሲሰግድለት አትስገድልኝ አለው።
እስኪ ይህን ተቃዋሚ ወንድሞች በምን ያስማሙታል? የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ
አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ ማለት ይህ ነው። ለመሆኑ ቅዱስ ዮሐንስ እና ኢያሱ ዛሬ እኛ ካለን እውቀት ያነሰ እውቀት ስላላቸው ነው የሰገዱት? እዉነት ለመናገር ኢያሱ እና ቅዱስ ዮሐንስ በዚያን ጊዜም ቢሆን ለማን መስገድ እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ።”እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን"።ኢያ.24:15 ያለ ኢያሱ ሆነ ፍቁረ እግዚእ (የጌታ ወዳጅ የተባለ) የስላሴ ሚስጥ አስፋፍቶ የጽፈ(ዮሐ.1:1) ሰማያዊዉን ህይዎት በራእይ መልእክቱ ይሳየን።ምድራዊ ሞትን ያልሞተ።ክብሩ እጅግ የበዛ ዮሐንስ ፈጽሞ የአምላክን ክብር ለመልአክ አሳልፈዉ አይሰጡም።ዮሐንስስ መልአክ መሆኑ ጠፍቶት ነው? እንዲህ እንዳንል ከፍ ብሎ ባሳየኝ በመልአኩ እግር.. ይላል።ዮሐንስ አንድ ግዜ ብቻ አይደለም ለመልአኩ የሰገደለት ቀደም ብሎ በራእ.19:10 ሰግዶለታል።እንዴት ሁለት ገዜ ተሳስቱአል ይባላል? ለነገሩ አልኩ እንጂ ሶስተኛም ቢያገኝዉ ይስግድለታል ምክንያቱም ዮሐንስ ክርስትያናዊ ግዴታዉን እየተዎጣ ነዉና።ዕብ.13:7 "የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው"።የቀደሙት እነማን ናቸው?? ዳዊት ሎጥ ዳንኤል ጌዲዮን ወዘተ...የእነዚህን ፍሬ መመልከት መልካም ነው ፍሬያቸው ያማረ ነው።ዮሐንስ እነሱን መስሎ ሰገደ።ምክንያቱም ቅዱስ ዮሐንስ ለመላእክት እንደሚሰገድ ያውቃል ከቀደሙት አባቶች ተምራልና [ኢያ.5:13_15... ዳን.8:15_17....ዘኁ.22:31]።መልአኩም የጌታን ምሳሌ ተከትሎ እራሱን ዝቅ አደረገ።ዕብ.2:9 ።
ትምህቱ ይህ ነው እራስን ዚቅ ማድረግ እንጂ ስግደት ይፈቀዳል ወይም አይፈቀድም ለሚል መልስ አይደለም።ለምሳሌ አንድ ትልቅ ሰው ቤታችን ሲመጣ ከወንበር ብድግ ስንል አይገባም ተቀመጡ ቢለን ሌላ ጊዜ ቢመጡ አይገባም ብለውናል ብለን ከወንበራችን አንነሳም? ዮሐንስም ያደረገዉ ይህንኑ ነዉ።ስለዚህ ለመልአክ የሚሰገደው የአክብሮት ስግደት መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል።ነገር ግን ዮሐንስ በክብሩ ታላቅ ስለሆነ መልአኩ እኔም እኮ ባርያ ነኝ አትስገድልኝ ብሏል።እንደዉ ለማስረዳት ያህል እንጅ ስግደት እንኳን ለመልአክ ለሰውም ይሰገዳል።ዘፍ.23፡12 “አብርሃምም በአገሩ ሰዎች ፊት ሰገደ ...”ዘፍ.23፡ 7 “አብርሃምም ተነሣ፥ ለምድሩ ሕዝብም ለኬጢ ልጆች ሰገደ።”ዘጸ.18፡7 “ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ወጣ ሰገደም ሳመውም...”ይልብሃል። አብርሃም ለኬጢ ልጆች የአክብሮት ለእግዚአብሔር የአምልኮ ስግደት እንደሚያስፈልግ ጠንቅቆ ያዉቃልና ።አብርሃም የአምላክን ክብር ለሰው አሳልፎ የሚሰጥ አይነት ደካማ ሰው አይደለም(እነደዚህም ዓይነት ስህተት አይሰራም)።እነደዚህስ ተብሎ አልተጽፈም “ራእይ.3:9 እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ”።በዚህ ጥቅስ አምልኩ ነው ያላቸው ወይም አክብሩት ???
እንዲሁም 1ኛ.ዜና መዋ.29:20 "ዳዊትም ጉባኤውን ሁሉ።አምላካችሁን እግዚአብሔርን ባርኩ አላቸው።ጉባኤውም ሁሉ የአባታቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ባረኩ ራሳቸውንም አዘንብለው ለእግዚአብሔርና ለንጉሡ ሰገዱ"።ለእግዚአብሄር የአምልኮ ለንጉሱ የአክብሮት ስግደት እንደሚገባ ዳዊት አበክሮ ይናገራል።ታዲያ የዘመኑ ሰዎች ምን ነካቸዉ ትህትና ምነዉ ከንሱ ጠፋ??? እንግዲህ ምን እንላልን በመንፈስ ቅዱስ የተደርሰዉ የእግዚአብሄር ቃል መጽሃፍ ቅዱስ ለቅዱሳኑ ስግደት እንደሚገባ ስላስተማረን እንሰግድላቸዋለን።የአምልኮ ስግድት ግን አልፋና ኦሜጋ ለሚባል ይህን አለም ካለመኖር ወደ መኖር ላመጣ በፍጥርት ሁሉ ላይ ስልጣን ላለዉ የዘለአለም ንጉስ የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ የነገስታት ንጉስ ለሚሆን ለአንድ እግዚአብሔር ብቻ!!!
==>የቅዱሳን መላእክት ምልጃ እና እረዳትነት አይለየን።
No comments:
Post a Comment