“Serving of God & the fruits of the Holy Spirit”
“አገልግሎትና የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች”
ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ!
ሰይጣን በአንድ ወቅት ለአባ መቃርስ ጠላቶችህ በጣም በዙ ሲለው አባ መቃርስ “ሰው የሰው ጠላት የለውም” አለውና ሰይጣንን አሳፈረው! ዲያቢሎስም ታዲያ የሰው ጠላት ማን ነው? ብሎ አባ መቃርስን ጠየቀው። አባ መቃርስም የሰው ጠላትማ የእለተ አርቡን ሰው አዳምን የፈተነ ፣ ኢዮብን ፣ ዳዊትን ፣ የበቁ አባቶችን በሙሉ የፈተነ አንድ ፍጥረት ነበር፤ ጠላት እሱ ነው! “አንተ ይህን ፍጥረት አታውቀውም እንዴ?” አለው። ዲያቢሎስም ኧረ በጭራሽ ሰምቼ አላውቅም አንዳችም የማውቀው ነገር የለኝም፤ ይገርማል! እንዴት ያለ ጨካኝ ነው አለ ራሱን እየነቀነቀ! አባ መቃርስም አዎ እንዳልከው ጨካኝ ነው፤ ይህን ፍጥረት አለማወቅህ ግን ገርሞኛል። ይገርምሃል እሱ ጨካኝ ብቻ ሳይሆን የፈጠረውን በገዳመ ቆሮንጦስ የፈተነ ደፋርም ጭምር ነው። ጨካኝና ደፋር ቢሆንም በጌታችን ድል ተነስቷልና እኛም ይህችን ጾም ሰሞኑን እየጾምን እኮ ነው አለው። ይህን ግዜ “ዲያቢሎስ ድል ተነስቷል” የሚለውን ቃል ሲሰማ ሽንፈቱ ትዝ አለውና ተቁነጠነጠ።እንዳይታወቅበት ግን “አይ ደፋሩ ጉድ ጉድ! እያለ ማስመሳሉን ቀጠለ። አባ መርቃስም እንዴ አንተ ይህን ካላወቅህ አትጾምም ማለት ነው እንዴ? አለው ፍግግ እያለ።
ዲያቢሎስም ጾ… ጾ ….. ም…. ጾም ትንሽ ስለሚያመኝ…. እያለ ሲቀባጥር አባ መርቃስ አሁንም ፍግግ እያለ አይ አንተ የሰው ጠላት የምትሆነው እስከ መቼ ነው? መታመሜን አውቀህ እንዳልጾም ይህን ሁሉ ቀባጠርክ። ገና ስትመጣ ማን እንደሆንክ አውቅ ነበር! ገና እኔን ለመፈተን ስታስብ አውቅ ነበር! አይ ዲያቢሎስ የሰው ጠላት አንተ ብቻ ነህ! በል አሁን የጾም ግዜ ነውና ዞር በል ብሎ ገሰፀው። ዲያቢሎስም ከእርሱ ራቀ። ይህን የአባ መቃርስን ታሪክ ሳነብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ “ዲያቢሎስ እንደ ሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችሁ ይዞራል በእምነት ሆናችሁ ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል” የምትለዋ የሐዋርያው መልዕክት ፩ኛ ጴጥሮስ [፭:፰]
ይህን በደንብ እንረዳ ሰው የሰው ጠላት የለውም፤ ጠላት ማን ነው? ጠላት ዲያቢሎስ ነው። ይህን ከተስማማን አገልግሎታችንን እንዴት ከጠላት ዲያቢሎስ መጠበቅ እንደምንችል በአንድነት እንይ፦
የአገልግሎት መሰረት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችም፤
ፍቅር ደስታ ሰላም ትዕግስት ትህትና … ናቸው [ገላትያ 5:22]
አንድ አገልጋይ እነዚህን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች እንደ አገልግሎት መመሪያ ገንዘቡ አድርጎ ከያዛቸው በአገልግሎቱ ማንኛውም ማዕበል ቢያናውጠው እሱ እንደማይሰነጠቅ ዐለት ነው! ጆሮ ያለው ይስማ! የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችንም ለአገልግሎቱ በነጻ ይግዛ!!
“ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላቹ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋታቹ ወደ ኋላ አትበሉ” ሮሜ 12:11
Ø የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ያሉት አንድ አገልጋይ እንዲህ ይገለጻል፦
v ፍቅርን ፍለጋ፦
ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ!
አንድ አገልጋይ ከሁሉ ጋር ተስማምቶ ሁሉን እንደ ወንድምና እህቱ አይቶ ያገለግላል። ፍጹም ፍቅር ሲባል የሚወዱንን ብቻ መውደድ ሳይሆን የሚጠሉንንም መውደድ መቻል ማለት ነው። ቅ/ጳውሎስ “ተራሮችን የሚያፈርስ እምነት ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” እንዳለው [1ኛቆሮ 13]
“ብዙ ውሀ ፍቅርን አያጠፋትም፤ ፈሳሾችም አያሰጥማትም” መሓ [8:7]
ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ!
ፍቅር እንደ ሳሙኤል እናት ወላድ ናት እንጂ እንደ ሜልኮል መካን አይደለችም፤ ሐና 6 ልጆችን ወልዳ እነ ዳዊትን የቀባውን እንደ ሁለት የሚቆጠረውን ሳሙኤልን ስለ ወለደች መካኒቱ 7 ወለደች ተባለላት!! 1ኛ ሳሙ [2:21] ፍቅርም እንዲሁ እንደ ሐና ወላድ ናት፤ የበኩር ልጇም በሁኔታዎች መለዋወጥና በግዜ ብዛት የማይቀየር የወንድምና እህት ወዳጅነት ነው!! ፍቅርህ ከግዜ ብዛት ይቀየራል? ታላቁ መፅሐፍ እንዲህ ይልሐል፦
የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና የምነቅፍብህ ነገር አለኝ ራዕ [2:4]
ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ!
አንድ ሰው ቢያስቀይመን በይቅርታና በግልጽ ልብ እናሸንፈው፤ እንዲህ አይነቱ ሰው ለብቻው ሲሆን የሰራው ስራ በእርግጥ ይፀፅተዋል። ታላቅዋ ፍቅር እንዳትርቅህም አንድን ሰው በተደጋጋሚ አትገስጽ፤ የሚነበብ የፍቅር መጽሐፍ መሆን ከፈለክ ለሁሉም ሰው መልካም ቃል፣ ፈገግታና እውነተኛ ሰላምታ አቅርብለት። የምታናግረውን ሰው አእምሮው ላይ ከመድረስህ በፊት ወደ ልቡ ለመድረስ ሞክር፤ በዚህ ግዜ ልቡንም ሆነ አእምሮውን በእርግጠኝነት ታገኘዋለህ። ሐዋርያው ዮሐንስ በስራ እና በእውነት እንጂ በአንደበት ብቻ አንፋቀር እንዲል 1ኛ ዮሐ [3:18] የወንድምና የእህታችንን ችግርና ድክመት እንደ ራሳችን ችግር መቁጠር ስንችል ያኔ እንደ ጌታ 120 ቤተሰብ እንሆናለን፤ ከዛስ? ከዛማ መንፈስ ቅዱስ የአገልግሎት ኃይልና ፀጋ እንደሰጣቸው ለእኛም እንዲሁ ይደረጋል። የበቁ አባቶች ሰው የእግዚአብሔር ፍጡር ስለ ሆነ ብቻ ይወዱታል፤ ለሰው ልጅ ያላቸው ፍቅርም የተለየች ናት፤ ይህ ፍቅራቸው [ፍቅረ ቢጽ] ይባላል። ቅ/አውግስጢን “እንደ ርግቦች እንጣላለን እንጂ እንደ ተኩላዎች ፈጽሞ አንፋቀርም!!” ብሏል። ርግቦች እርስ በእርስ ይጠባበቃሉ፣ ለመመገብ አንድ ይሆናሉ፤ አንድ ላይም ይበራሉ! ጌታችንም እንደ ወንድምና እህት እንድንዋደድ እሱ ፍቅር ስለ ሆነ በፍቅር አሳይቶናል። ኦሪት 622 ሕግጋት ቢኖራትም ማሰሪያው ግን
ፍ ቅ ር ነው።
ሥራህን ድካምህንና የአገልግሎት ትዕግሥትህን አውቃለሁ
ራዕ [2:2]
v ትዕግሥት፦
ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ!
አንድ አገልጋይ እንደ ቅዱስ አርሳሚዮስ “ብዙ ግዜ ብዙ እናገራለሁ በመናገሬም አዝናለሁ፤ በዝማታዬ ግን ያዘንኩበት ቀን የለም” ይላል። በፍፁም ትዕግስት ሁሉን ችሎ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ በትዕግስት ያገለግላል። ለመትከል ግዜ አለው ለመንቀልም ግዜ አለው፤ ትዕግስተኛ ሰው መቼ እና እንዴት ምን መስራት እንዳለበት ያውቃል። [መክ 3:1] ብርሐነ ዓለም ቅ/ጳውሎስ እንዲህ እንዳለው “ድፍረት የሌላቸውን አጽኗቸው ለደካሞችም ትጉላቸው ሰውን ሁሉ ታገሱ”
[1ተሰ. 5:14] በየዋህነት እርስ በእርሳቹ ታገሱ [ኤፌ 4:22] ታላቁ ሐዋርያ ቅ/ጳውሎስ 3 ዓመት ለአገልግሎቱ እየታገሰ የተጋው እንዴት ነበር?
ሶስት አመት ቀንና ለሊት በዕንባ የመከርኳችሁን እያሰባችሁ ትጉ
[ሐዋ. 20:31] የቅ/ጳውሎስ ትዕግስት አይደንቅህምን?
እነሆ ቅ/ጳውሎስና አገልግሎት፤ አገልግሎትና ትዕግስት የአንድ ርግብ 2 ክንፎች ናቸው፤ ሁለቱም አይለያዩምና!!! ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ! ታላላቅ አበው ትዕግሥተኛ ነበሩ፤ አረጋዊው ስምዖን የጌታን መወለድ ስንት አመት ነበር በትዕግስት የጠበቀው? አብርሐምስ ይስሐቅን ያገኘው ስንት ዓመት ታግሶ ነበር? ዳዊትስ ንጉስ እንዲሆን ከተቀባ በኋላ ሳኦልን ስንት አመት ነበር የታገሰው? አረጋዊው ስምዖን 500 ዓመታት አብርሐም 25 ዓመታት ዳዊትም 15 ዓመት ሙሉ በፍጹም ታገሱ!!!
ትዕግሥት መራራ ናት ውጤትዋ ግን ጣፍጭ ናት!
በአንድ ነገር ሲናደዱ ያለ ብስጭት ለመረጋጋት የሚለማመዱ ሰዎች እንዳሉም ይታወቃል።
ቅ/ዮሐንስ መነኮስ (St John Climacus) “ቁጣ እየወፈረች ስትመጣ አስቸጋሪ ልጅ የምትወልድ እናት ትሆናለች ብሏል”
ፍቅር ሁሉን ይገዛል! ጥበብ አገልግሎትን ፍሬያማ ያደርጋል!
ትህትና ደግሞ አገልግሎትን ከዲያቢሎስ ቅናት ይሸሽጋል!
v ትህትና፦
ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ! አንድ አገልጋይ በፍፁም ትህትና ሁሉን አክብሮ እንደ ዳዊት እኔ ትል ነኝ እያለ እንደ ቅ/ጳውሎስ እኔ ጭንጋፍ ነኝ እያለ በፍጹም ትህትና ያገለግላል። ሌሎችንም ሲመክር እንደ ቅ/ጳውሎስ በእንባ ሆኖ ለአገልግሎቱ እየሳሳ ያገለግላል።
[1ኛ. ቆሮ 15:7 ፤ ፊል 3:18] እንደዚህም ይላል “የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋቹ ግዜ ከቁጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን ልናደርግ የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል በሉ” [ሉቃስ 17:10] ታላቁ ሐዋርያ ቅ/ጳውሎስ ለአገልጋዮች ትህትናን ሲያስተምር እንዲህ አለ፦ ሐዋርያ ተብዬ መጠራት የማይገባኝ …. 1ቆሮ [15: 9] ለካስ እኛም አገልጋይ ተብለን የማንጠራ ጭንጋፍ ነን፤ እንዲያው በቸርነቱ ከቤቱ ገባን እንጂ!! ሙሴ በምድር ካሉት ሰዎች ሁሉ እጅግ ትሁት ሰው ነበር [ዘሁ. 12:3] “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ለትሁታን ግን ፀጋን ይሰጣል” [ያዕ 4:6] ስለሚል ከእግዚአብሔር ፀጋ እንዳይለይ ትህትናን ይወዳታል።
ለእያንዳንዱ ሰው ትህትና አሳይ፤ ትህትናህ በዕድሜና በማዕረግ ከአንተ ለሚያንሱት ለታናናሾችህም ሲሆን እንዴት ያምራል!!
እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የአገልግሎቱን ደመወዝ ይቀበላል 1ቆሮ [3: 8]
vሰላም፦
ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ!
“ቢቻላቹ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” [ሮሜ 12:18] እንዲል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም የሚኖር ሰው አቤት መታደሉ!! እንክርዳዱን በመንቀል ውስጥ ውስጣዊ ሰላማችሁንና ከሰዎች ጋር ያላችሁን ሰላም ልታጡ ትችላላችሁ፤ አርምሟችሁን ፣ የንፈስ እርጋታችሁንና ትህትናችሁን ጨምራችሁ ታጡታላችሁ። በሌሎች ያለውን ስንዴ ስትነቅሉ በእናንተ ያለውን ስንዴ እንዳትነቅሉ ተጠንቀቁ!! በተመሳሳይ ግዜ ስንዴያቸውን ጠብቀው እንክርዳዱን መንቀል የሚችሉት በጣም ጥቂት ናቸውና!!
እንክርዳዱን ለመንቀል ተመራጩ መንገድ ሁሉን በሰፊ ልብ አልፎ እንክርዳድ በበዛበት እርሻ ስንዴ ሆኖ መገኘት ነው። እኛ የምንጠየቀውም ለምን ስንዴ አልሆናችሁም? ተብለን ነው። እንክርዳዱን የተከልነው እኛ አይደለንምና ስለ እንክርዳዱ የሚጠይቀን የለም። “አህያ ሲጭኑ ሶስት ሆኖ ከሰው ጋር ሲኖሩ ብልጥ ሆኖ” ያለኝን ጓደኛዬን አልረሳውም።
አንደበቱን ሳይገታ እግዚአብሔርን የሚያገለግል የሚመስለው አገልግሎቱ ከንቱ እንዳይሆን ይጠንቀቅ [ያዕ 1:26]
v አንደበት፦ ሶቅራጠስ የተባለው ፈላስፋ “ቃላትህ
ከሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት ይወስናሉ” ብሏል። ከባለጸጋ የተወለደው በአለም የመጀመሪያ ባህታዊ የሆነው አባ ጳውሊ
[St Abba Pauli] “አንደበት እሳት ነው” የሚለውን የያዕቆብ መልዕክት ሲነበብ ሰምቶ ያዕ [3:6] እኔም አንደበቴ ሰውን ብታሳዝንስ ብሎ ቤተሰቦቹን ጥሎ የበረሀ ኑሮ ጀመረ። ዳዊትም አቤቱ ለአንደበቴ መዝጊያ አኑርልኝ ብሏል፤ ለካ አንደበትም መዝጊያ በር አለው፤ ኧረ ምን አንደበት ብቻ ዓይንም፣ ምላስም፣ ጆሮም በር አላቸው! ሁል ጊዜ ክፍት ከሆኑ አደጋ ነው፤ ሁሉ ጊዜም ዝግ ከሆኑ ችግር ነው! የእነዚህ በሮች መክፈቻ በእጃችን አለ። መዘጋት ባለባቸው ግዜ ይዘጋሉ መከፈት ካለባቸውም ይከፈታሉ!! ክርስቲያን ማለት ልክ ዮሐንስ እስኪወለድ ድረስ ዘካርያስ ዲዳ እንደሆነው መሆን አለበት ማለት አይደለም፤ የክርስትና መለኪያ አለመናገር ሳይሆን በንግግሩ ማንንም አለማስቀየም ነው! ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ! ቅ/ኦጊሪስ [St Aughiris] ዝምታን የተማርኩት ከተናጋሪ ሰው ነው ብሏል። ይህም ሕይወታችንና ንግግራችን አንደበታችን መንፈሳዊ ናቸውን? ብለን እንድንጠይቅ ነው። ሰው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስለ ሆነ ከዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ መዝሙርና መንፈሳዊ ቅኔ ይወጣል፤ የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ስለ ሆነም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በውስጡ ይገኛሉ። ገላትያ [5:22]
እኛ ኃይለኞች የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንን ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል ሮሜ [15:1]
v ደስታ፦
ከልብ የምወዳችሁ ውድ ወንድም እህቶቼ!
ሰዎችን በመልካምና በጣፋጭ ቃል ፍግግ እያልክ ተቀበል። አንድ አገልጋይ ለሁሉ ደግ ፊት አሳይቶ ደስ እያለው ያገለግላል። “ምንም እንኳን የበለስ ዛፍ ባያፈራ፤ ላሞች በበረት ውስጥ ባይገኙ እኔ ግን በጌታዬ ደስ ይለኛል” [ዕንባቆም 3:17] እንዳለ ምንም እንዃን አገልግሎቱ እንዳሰበው ባይሆንለትም የተመኘው አገልግሎት ሩቅ እንደማይሆን ስለሚያውቅ ያለችውን አገልግሎት በሚባርክለት በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል። ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ “በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ አንዴ አይደለም አሁንም ደስ ይበላችሁ” ሲል በአገልግሎቱ ምንም እንከን ሳይኖርበት ቀርቶ ሁሉ ተሳክቶለት አልነበረም፤ ነገር ግን የጎደለው በጌታ እንደሚሞላ ስለሚያውቅ በተስፋ ተጽናንቷል። በደስታ ጊዜም መንፈሳዊ መሆን እንችላለን፤ አለበለዚያማ ዘላለማዊ ደስታ ባለበት መንግስተ ሰማያት እንዴት መንፈሳዊ መሆን እንችላለን!?
በጎውን አይቶ ያልሰራው ኃጢአት ነው ያዕ [4:17]
v የተግሳጽ መመሪያዎች፦
አንድ መንፈሳዊ ሰው የዲያቢሎስን ኃይልና የሰውን ደካማ ተፈጥሮ ስለሚያውቅ የወደቀውን ሰው አይገስጸውም፤ በእርሱም ላይ አይፈርድም። በሌላ በኩል ቅ/ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “ገስጽ” ብሎታል። 2ኛ ጢሞ [4:2] ይህን ሲል ሁላችንም መገሰጽ አለብን ማለት አይደለም። የሚገስጸው ሰው ጳጳሱ ጢሞቴዎስ ለመገሰጽ ያለው ዓይነት ስልጣን አለኝ? ብሎ ሊጠይቅ ያስፈልጋል። የምንገስጸውስ እንዴት ነው? ብሎ ማሰብ አለበት። ቅ/ጳውሎስ እንደ ደካማ ሰው እያለቀሰ ነበር የሚገስጸው። ሐዋ [20:31]
ስለዚህም ማንንም ስትገስጽ በፍቅርና በትህትና ይሁን፤ ያኔ በፊት ካየኸው ውጤታማ ስለምትሆን ፍግግ ማለት ግድ ይሆንብሃል!!
ተሰሚነት እንዳታጣም ስለ እያንዳንዱ ስህተት በዕድሜም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወት ከበታችህ ያሉትን አትገስጽ “አቤቱ አንተ ኃጢአትን ብትቆጣጠር በፊትህ ማን ይቆማል” መዝ [129:3] እንዲል አንዳንዴ አይቶ እንዳላየ መሆን ይጠቅማል። አንተ ስታጠፋ ጌታ አይቶህ እንዳላየ እንደሚሆነው ማለት ነው!! ዘወትር የምትገስጸው ከሆነ ሰውየው በመንፈሳዊ ዝለት ይወድቃል። በመግባባትና በፍቅር በውዳሴ የተጀመረ ምክር ውጤቱን ወዲያው በዓይንህ ታየዋለህ፤ ማንም ሳይጎዳ ፍሬውን በማየትህ ደስ ይልሃል።
ወዳጄ ሆይ! በቀላሉ ፍሬ አፍርተህ ደስ መሰኘት ስትችል ለምን በረጅሙ እየደከምክ ታዝናለህ?!
ወንድሞቼ ሆይ ልዩ ልዩ ፈተና በደረሰባችሁ ግዜ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት ያዕ [1:2]
v ፈተና፦ አንድ አገልጋይ አገልግሎት ሲጀምር
ዲያቢሎስም ፈተናውን ይጀምራል። የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው ዲያቢሎስ በአገልግሎታችሁ እንደሚቀና አስባችሁ ታውቃላችሁን? በእርግጥ እሱ ይቀናልና ማንኛውም ፈተና ቢገጥምህ ከአንተ አስቀድሜ ስጠብቀው ነበር በለው እንጂ አትገረም። በአገልግሎትህ እግዚአብሔር ሲደሰት ዲያቢሎስ ይከፋዋል፤ በአንድ ሰው ንስኃ መግባት የሰማይ መላዕክት ደስ እንደሚላቸው ሁሉ በአንድ ጻድቅ ውድቀትም የዲያቢሎስ ሰራዊት አጋንንት ደስ እንደሚላቸው አትዘንጋ!! በአገልግሎትህ ብትወድቅ የዲያቢሎስ ቅናት መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውምና እንዲህ በለው
“ጠላቴ ሆይ ብወድቅ ደስ አይበልህ፤ በጨለማ ብሄድ እግዚአብሔር ብርኃን ይሆነኛልና ብወድቅ በእርሱ እነሳለሁ” ሚክ [7:8]
ዲያቢሎስ ከሌሎች አብልጦ እጅግ የሚያስደስቱት 2 ነገሮች አሉ፤ አንደኛው ተስፋ ማስቆረጥ ነው፤ ሁለተኛው አሁንም
ተስፋ ማስቆረጥ ነው!!
ወዳጄ ሆይ! በአገልግሎት መቆም ብቻ ሳይሆን መውደቅም እንዳለ ፣ ወድቆ መቅረት ብቻ ሳይሆን መነሳትም እንዳለ ማወቅ አለብን።
ለካ እንደ ኢሳይያስ በለምጽ ከተመቱ በኋላ መፈወስና ማገልገልም አለ፤ ኢሳ [6:1] ለካ ከአገልግሎት ኮብልሎ በአሣ አንበሪ ውስጥ ከተዋጡ በኋላ ነነዌን ለመስበክ እንደገና ለአገልግሎት መጠራትም አለ! የዚህ ነብይ ታሪክ በአገልግሎት ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን አስተምሮን አልፏል።
እግዚአብሔር ያለቀውንና የተቆረጠውን ተስፋ ይቀጥላል [ኢሳ. 10]
v የአገልግሎት ጥበብ፦
ወዳጄ ሆይ! ቅ/ጳውሎስ ሁሉንም በአገልግሎት ለማቀፍ ጥበብ ይጠቀም ነበር። “ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁድ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንኩ” 1ኛ ቆሮ [9:19] ይህም በአገልግሎት ሁሉን ለማቀፍ ባለው ፍላጎት ነበር።
የእግዚአብሔርን ስራ በቸልታ የሚሰራ ርጉም ይሁን ኤር [48:10]
ይህች ቃል አገልጋዮች ትንሿን ስራም ቢሆን በቸልታ መስራት እንደሌለብን ያስተምረናል።
v ፀሎት፦
ገና ከእንቅልፋችሁ ስትነሱ የምትነጋገሩት ከማን ጋር ነው? ከአጠገብህ ካለው ሰው ጋር ወይስ ከራስህ ህሊና ጋር? በጠዋት ማንንም ሳታናግር ማናገር ያለብህ ቸር ፈጣሪህን ነው። አንድ አገልጋይ አገልግሎቱን እግዚአብሔር እንዲቀበልለት ማንኛውንም ነገር ከመጀመሩ በፊት ጸሎትን ያስቀድማል፤ ቅ/ጳውሎስ “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” 1ኛ ቆሮ [10:12] እንዳለው እሱ ራሱ እንዳይወድቅ ስለ ራሱና ስለ ወንድም እህቶቹ አገልግሎት በጸሎት ይለምናል።
ማጠቃለያ፦
ወዳጄ ሆይ! ታላቁ መጽሐፍ “አንባቢው ያስተውል!!” ይላል፤ ትላንት ከአጠገብህ የነበረ ስንቱ አገልጋይ ከአገልግሎት ቀረ? ይህ በእውነት ከልብ ያሳዝነናል። ለዚህ ምክንያቱ ልዩ ልዩና ብዙ ነው። የሰውን ፊት አይቶ ከአገልግሎት ወደ ኋላ የሚለውን ቤቱ ይቁጠረው! የሰውን ንግግር አይቶ ከአገልግሎት የቀረውንስ ማን ይቁጠረው? ሲጀመር እኛ የመጣነው እኮ የሰውን ፊትና ንግግር ለማየት ሳይሆን የጌታን የምህረት ቃል ለመስማት ነበር፤ ሰውን አይተን ወደ ኋላ ማለታችን ግን ያሳዝናል!! በሌላ በኩል ለሰው መሰናክል እንዳንሆን መጠንቀቅ እንዳለብንስ አያስረዳንምን? አባ ፒሾይ “ቤተክርስቲያን የእያንዳንዱን ልጇን የጥፍር ቁራጭ ትፈልጋለች” እንዲል ከአገልግሎት የራቁ ሁሉ እንዲመለሱ የልብ ምኞታችን ነው። ይህችን ጽሁፍ ማንበባችንም እንዲህ አይነቱ እንዳይደርስብን እንደሚጠቅመን ይታመናል። የዚህች ጽሁፍ ዋና አላማዋም ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በአገልግሎት ህይወቱ ሁሉን ዳሶ ሁሉን አይቶ እንደ ተናገረው የአገልግሎት መሰረት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን “ፍጹም ፍቅር ፍጹም ትዕግስት ፍጹም ትህትናን” ገንዘብ አድርገን በአገልግሎታችን እንበረታ ዘንድ ነው።
በከመ ይቤ ቅ/ጳውሎስ
ታላቁ ሐዋርያ ቅ/ጳውሎስ እንዳለው እኛም ቢቻለን ከሰው ሁሉ ጋር በፍቅር በሰላም በደስታ በትህትና በትዕግስት ለመኖር እንመኝ፤ በፀሎትም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የሆኑትን ሁሉ እንዲሰጠን እንለምን “ለምኑ ይሰጣችኋል ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋል” እንዲል ይህን የሚለምን ሰው የለመኑትን በማይነሳ አምላክ ይሰማል፤ ከራሱና ከሰው ሁሉ ጋር ሰላም ሆኖ በሰላም ያገለግላል።
ቁጠረኝ እንደ አንዱ “ከአገልጋዮችህ” [ሉቃስ 15:11]
አባቴ ሆይ መጥቻለሁ
ይቅር በለኝ በድያለሁ
ይቅር ባይ ነህና የበደሉህን
ቂም እንዳቲዝብኝ በደሌን ቆጥረህ
ስለማይገባኝ ለመባል ልጅህ
ቁጠረኝ እንዳንዱ ከአገልጋዮችህ
አባቴ ሲቆጣኝ አልመለስ ብዬ
ስትመክረኝ እናቴ አልሰማሽም ብዬ
ከወንድሜ ጋራ ሀብቴን ተካፍዬ
ከሰው ሃገር ሄድኩኝ ከአባቴ ተለይቼ
የማይጎዳ መስሎኝ የሃጥያት መከራ
ኮብልዬ ነበረ ወደ ሃጥያት ተራ
አሁንግን ተመለስኩ ጥፋቴን አውቄ
የሰማይ አባት ሆይ ይቅር በለኝ
በአባቴ ቤት ሞልቶ ማርና ወለላ
በአባቴ ቤት ሞልቶ የቅኔው አዝመራ
ሄድኩኝና መንገድ በሰፊው ጎዳና
ናፍቆቱ በዛብኝ ያሬዳዊው ዜማ
እኔም ልብ ስገዛ ስመለስ ከቤቴ
ገና ከሩቅ አይቶኝ ይቅር ባይ አባቴ
ወደኔ ሮጦ አቀፈና ሳመኝ
በልቤ እየገረመኝ ወዲያው መታቀፌ
ትንሽ ሊወቅሰኝ ነው ብዬ ስጠባበቅ
መች እሱ ሊያስታውስ የትላንቱን ዛሬ
ደገመና አዘዘ አዲስ ልብስ ለእራሴ
ደግሞም ቀለበት ለጣቴ ; ጫማንም ለእግሬ
ይቅር ባይ ነህና የበደሉህን
ቂም እንዳቲዝብኝ በደሌን ቆጥረህ
ስለማይገባኝ ለመባል ልጅህ
ቁጠረኝ እንደ አንዱ ከአገልጋዮችህ
“The Passion of Christians Love”
“የ ፍ ቅ ር - ታ ላ ቅ ነ ት”
ስለ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ፍቅር
ሐዋርያው ጳውሎስ አብዝቶ ሲናገር
ለቆሮንቶስ ሰዎች እንዲህ ብሎ ነበር
ብንናገር በሰው በመላእክት ልሳናን
ትንቢት ተገልጦልን ብናውቅም ሚስጥርን
ተራራን የሚያፈርስ ታምራት ቢኖረን
ጥበብና እውቀት ቢሰጠን በዝቶልን
በእምነታችን ፀንተን ፍቅር ግን ከሌለን
እንድማይጠቅም እቃ ባዶ ነን ከንቱ ነን
ድሆችን ለመርዳት ሃብታችንን ከፍለን
ሥጋችንን በእምነት ወደ እሳት ብንጥል
በፆምና ፀሎት ዘወትር ብንጋደል
ፍቅር ግን ከሌለን የለንም በጎ እድል
በአለም ላይ ያለውን ሁሉን ለማሸነፍ
በህይወት መዝገብ ላይ በክብር ለመፃፍ
ሊኖረን ይገባል ፅኑ የፍቅር ደጃፍ።
ሰው በተስፋ ተሞልቶ በእምነቱ ቢተጋ
ከአምላክ ይሰጠዋል ከፍተኛ ዋጋ።
የእመቤታችን ፀጋ ለአገልግሎታችን የፀጋ ልብስ ይሁንልን ፤
ወ ሥ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
አሜን
-//-
No comments:
Post a Comment