Tuesday, 27 March 2012

ነህምያ! ለነገሮች ሁሉ ጸሎትን በማስቀደም እታወቃለሁ፤ በምርኮ ሀገር እያለሁ ሰዎች “የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈራርሷል በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ፤ “ይህን ነገር በሰማሁ ግዜ ተቀምጬ አለቀስኩ ነህምያ [1:4]


“እምዬ ቤተክርስቲያን ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስታውስሽ ምላሴ ከትናጋዬ ጋር ይጣበቅ"

የለንደን ወጣቶች "ለቤተክርስቲያን ያልሆነ ፓውንድ ይበጣጠስ ብለናል!!"... እውነት እኮ ነው ኪስ ቢገባ አያሞቅ ባንክ ቢገባ አይሞላ! እኛ የስደት ልጆች እናታችን ቤተክርስቲያን ተቸግራ በተደላደለ አልጋ ላይ የሚያርፍ ጎንም ሆነ ሕሊና የለንም!!

እነሆ ባለፈው እሁድ ማታ እስከ 3am ድረስ ስለ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ስናወጣና ስናወርድ አመሸን።

“እምዬ ቤተክርስቲያን ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስታውስሽ ምላሴ ከትናጋዬ ጋር ይጣበቅ" አልን በእንባ ጭምር!! እንደ ነብዩ ነህምያ አንዳች ስራ ለመስራት በጸሎት ጀመርን።

10 የምንሆን ልጆች የዝቋላ ገዳምን እርዳታ በተመለከተ ምን እናድርግ? አልን። ይህን የመሰለ ውይይት ዘወትር እሁድ ለምደናልና። እንደ ጉድ ሀሳብ አዋጣን፣ እንደ ጉድ ተነጋገርን እንደ ጉድ መፍትሄ መጣ። ሕዝበ ክርስቲያኑን በፌስ ቡክ እና በተለያዩ ዘዴ ሀሳቡን አስረድተን አንዳች ስራ ይሰራ ተባለ። ቀጠሮም ተያዘ። እነሆ በመጪው እሁድ መጋቢት 23 /April 1st/ ከቅዳሴ በኋላ የዝቋላ ገዳምን የእሳት ቃጠሎ የሚያሳዩ ቲሸርቶችንና የተለያዩ ጥቅሶችን በማንገብ ስማ በለው ሕዝቡን እንበል፣ ከ2 ፓውንድ ጀምሮ የተቻለውን ያድርግ ተባለ። ከእኛ ይጀመር ተባለ። ከእኛም ተጀመረ። አንዱ £100 አለ፤ ቀጠለ አንዱ ለቤተክ ያልሆነ! £100 ይሁና አለ። ቀጠለች ሌላዋ £50 አንደኛዋም ተከተለቻት። ያላትን ሰጥታ በጌታ የተመሰገነችው የአንድ ዲናር ባለቤትዋ ሴትም ከእኛ ጋር ነበረችና ከሁላችንም የበለጠ ሰጠች!! እንዲህ እያለ በዚያን ቀን ብቻ * ፓውንድ ተገኘ! ስንት እንዳገኘን በቁጥር መግለጹ ያልተፈለገው ዋናው ልብን መስጠት ነው እንጂ የሒሳብ ክፍለ ግዜ ስላልሆነ ነው።


ገና ሌሎችም የሰ/ት/ቤቱ ተማሪዎች ሲጨመሩ፣ የሕዝበ ክርስቲያኑ በለንደንም በየከተሞቹም ያሉት ሲደማመር ለቤተክርስቲያናችን ጥሩ ፖውንድ ሳይሆን ጥሩ ልብ እናዋጣለን። አሐዱ ተብሎ ሲጀመር እናት ቤተክርስቲያን ልባችንን እንጂ መቼ የእኛን ገንዘብ ፈለገችና? ቤተክርስቲያን ያጣችው ገንዘብ ሳይሆን ቅ/ጳውሎስን የመሰለ ሁነኛ ልብ ነው። ወዳጄ ሆይ ማወጣት ፈልገህ ባይሆንልህ ልብህን አዋጣ! አዎ ልብህን ለቤተክርስቲያን ስጥና ያንኑ አዋጣ።

ወጣት የነብር ጣት ሆይ ጊዜው አሁን ነው ። እስኪ በአውሮፓም ፣ በአረብ ሀገር ፣ በአለም ሁሉ ያለን የቤተክርስቲያን ልጆች ይህን የመሰለ ህብረት ፍጠሩና አንዳች ስራን እንስራ። በያላችሁበት የሰ/ት/ቤቱን ወጣት አስተባብሩና ስሩ፤ ብርቱ ጉዳይ አለብንና ጊዜው የስራ ነውና ወዳጄ ሆይ ልብህ አይተኛ። የቤተክርስቲያን ድምጽን ስትሰማ ተፈጥሮ ነውና ዓይንህ ቢዘጋ ልብህ ግን አይተኛ! ቤተክርስቲያንን የሚያቃጥል እሳት የእኛንም ልብ ያቃጥላል! የቀደሙት አባቶቻችን እሳት ላይ ቆመው የጠበቁልንን ቤተክርስቲያን እኛ ይህን እሳት ማጥፋት ካቃተን የእኛ መኖር ምኑ ላይ ነው? ለቤተክርስቲያን ድምጽ ዲዳው ይናገራል መስማት የተሳነውም ይሰማልና እስኪ ህዝቡን አስተባቡሩ እስኪ በስደትም ሆነ በሀገር ያለን ሁላችንም እንነሳና እያንዳንዳችን ቢያንስ 2 ችግኝ እንትከል፤ አንዱ ቢደርቅ አንዱ ይጸድቃልና!!

እነሆ ገዳሙን መርዳት የምትፈልጉ ምእመናን ከዲ/ዳንኤል ክብረት ብሎግ ኮፒ እንደተደረገው የገዳሙ የባንክ አድራሻ የሚከተለው ነው፡፡
ለዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ
የባንክ የቁጠባ ሂሳብ ቁጥር 19789
በአካውንቱ የላካችሁ ምእመናን በኢሜይል አድራሻ dkibret@gmail.com መላካችሁን ብትገልጡልን ለገዳሙ መልእክቱን ለማቀበል ይረዳናል



“እምዬ ቤተክርስቲያኔ ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ
ባላስታውስሽ ምላሴ ከትናጋዬ ጋር ይጣበቅ"

ለቤተክርስቲያናችን ፍፁም ሰላም ክብርና ሞገስ ይስጥልን አሜን።

እኛ ባርያዎቹ እንነሳለን የሰማይ አምላክም ያከናውንልናል ነህምያ 2:20

ከለንደን ቅ/ሥላሴ ቤተክ ሰ/ት/ቤት

No comments: