Saturday, 17 March 2012

ዐቢይ ጾም

የደሃ ግድርድር ሀብታም ይጋብዛል! ብሎ ሀብታሙ ጓደኛዬ እኔን ለመተረብ ሲፍጨረጨር ምክር ከድሃ ነበርሽ ማን ቢሰማሽ” ብዬ የደሃ ከረባቴን ከፍ ዝቅ ባደርጋት “ራቁቱን ለተወለደ ጥብቆ መች አነሰው” ብሎ በተውሶ የለበስኳትን ሱፌን ናቃት! “ልፋ ያለው በህልሙ ክብደት ይሸከማል” ብዬ የሚለውን ላለመስማት ጆሮዬን ይዤ ከአጠገቡ ጠፋሁና ይህችን ጥሑፍ ጣፍኩ፦

አንድ ሰው በአንድ ወቅት እንዲህ  ብሎ ፈጣሪውን ጠየቀ፤ በቤትህ የቆምኩት ሰው ጠፋቶ ነውን? ከሰው ለይተህ የጠራኸኝስ ሰው ጠፍቶ ነውን? በዛች በአውደ ምህረት እንድቆም የፈቀድከውስ ሰው ጠፍቶ ነውን? እያለ ጥያቄዎችን አወጣ አወረደ፤ እንደ ቸርነትህ እንጂ እንደ በደሌ ያልከፈልከኝ እንደ ስራዬ እንደ ሀሳቤ ያልከፈልከኝ ቸርነትህ ብዙ ምህረትህ የበዛ ጌታ ሆይ ሁሉን የምታደርገው ሰው ጠፍቶ ነውን? እያለ ያ ሰው ፈጣሪውን ጠየቀ። ፈጣሪም እንዲህ ብሎ መለሰለት
ሰው የማያውቃቸው በሰው ዓይን ያልገቡ ለአገልግሎት የተመረጡ ብዙ ሰዎች አሉ፤ መዝሙረኛው ዳዊት በ129ኛው መዝሙሩ ላይ አንተ ኃጢአትን ብትቆጣጠር በፊትህ ማን ይቆማል? እንዳለ ሁሉን አይቼ እንዳላየሁ ሆኜ በቤቴ እንዳቆምኩህ አንተም ታውቃለህ!  

ከእንግዲህ የሰው ልጅ ሆይ ሰው ሁን!”


ዐብይ ጾም፦

እንደ ሰው ሆኖ ለመጾም በገዳም አደረ ፤
ከዲያቢሎስ ዘንድ ተፈተነ ፤
የጨለማን መኳንንት በአምላክነቱ ኃይል ሻረ።
 ጌታችን አርባ ቀንና አርባ ለሊት የጾመበት ገዳመ ቆሮንቶስ ይህን ይመስላል
እስራኤላዊያን በአንድ ወቅት ለምን ጾማችን በእግዚአብሔር አይሰማም? ብለው ይጠይቁ ነበር፤ በእውኑ ብዙ ግዜ ጾማችን የማይሰማው ለምን ይሆን? ለዚህ የእስራኤላዊያን ጥያቄ ነብዩ ኢሳይያስ ድምፁን ከፍ አድርጎ  ለእስራኤላዊያን  መለሰላቸው፤ እነሆ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእውኑ እኔ የመረጥኩት ፆም ይህ ነውን? ፆማችሁ በጥልና በክርክር የተከበበች ናት፤ የልባችሁን ሁሉ ትፈጽማላችሁ፤ በእውኑ እኔ የመረጥኩት ፆም ይህ ነውን? ኢሳ 58:5 ዛሬም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ እኛን ይጠይቀናል “በእውኑ እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነውን”? እኔ የመረጥኩት ጾም የሚለውን ስናሰምርበት እግዚአብሔር የመረጠው ጾም አለ ማለት ነው፤ እግዚአብሔር የመረጠው ጾም ምን አይነት ጾም ይሆን? መልሱን በወንጌል ላይ እንዲህ እናገኘዋለን፦
ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ ፊታችሁን በፍቅር ቅባት ተቀብታችሁ የምትጾሟት ጾም ታላቅ ዋጋ አላት [ማቴ. 6: 16] ስትጾሙ የሚለውን ቃል አሁንም ስናሰምርበት መጾም እንዳለብን ያስረዳናል።

ልበ አምክ ዳዊት ከመጾሙና ለመዘመር በገናውን ከመደርደሩ በፊት እንዲህ አለ፦
አቤቱ ንፁህ ልብን ፍጠርልኝ// ልበ ንጹኃ ፍጥር ሊተ እግዚኦ [መዝ. 50: 10] ዳዊት ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ ብሎ ከለመነ በኋላ በገናውን እየደረደረ ዘመረ ጾመ ፀለየ ፤ ጾምና ዝማሬውም በእግዚአብሔር ተሰማች! እኛም ለመዝሙር በገና ከመደርደራችን፤  ከመጸለያችንና ከመጾማችን በፊት አቤቱ ንፁህ ልብን ፍጠርልኝ ማለት እንዳለብን ልበ አምላክ ዳዊት አስተማረን።

ስለ ጾም በወንጌል ላይ እንዲህ ተጽፏል ይህ ጋኔን ያለ ጾምና ፀሎት አይወጣም” // ዝንቱ ዘመድ እይወጽዕ ዘእንበለ ጾም ወበ ፀሎት [ማቴ. 17: 21] ጾም አጋንንትን እንዃን የማስወጣት ታላቅ ኃይል አለው!!!  ነገር ግን የመናፍቃኑን መፅሐፋ ቅዱስ ስንመለከት ይህን ቁጥር ዘለውታል!
ጾም አጋንንትን ለማውጣት ኃይል እንዳለው ስለሚናገር የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ቁጥር 21 የሚለው እንዳለ ተዘሏል!

እኛ ግን ከስራችን በፊት ሁሉ መጾም ይገባናል፤ ሐዋርያቱ ከአገልግሎታቸው በፊት ጾሙ ጌታም ተዓምራት ከማድረጉ በፊት እኛን ሊስተምረን ጾመ፤ እነ ዳዊት ንጉሥ ሆነው ሳለ ጾሙ፤ ነብያቱ ሁሉ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በተስፋ እየተጠባበቁ    ጾሙ! 

ጾምሰ እማ ለፀሎት ወእህታ ለአርምሞ ወነቃየ ለአንብዕ //
ጾም የጸሎት እናት የትዕግሥት እህት የንስኃ እንባ ምንጭ ናት!


እንደ ዳዊት በንጹህ ልብ የምትጾም ጾም ዋጋዋ ታላቅ ናት፤ ለዚህ ነው ዲያቆኑ በቅዳሴ እንዲህ የሚለው፦

ሰው በልቦናው ቂምን እና በቀልን ማንም በማንም ላይ ቢሆን አይያዝ // ትዕዛዝ አበዊነ  ሐዋርያት እያንብር ብዕሲ ውስጠ ልቡ ቂመ ወበቀለ በቅንአተ ላዕለ ቢፁ ወኢላዕለ መኑሂ። የተጣላን ታርቀን የበደልን ይቅርታ ጠይቀን ከኃጢአት ሁሉ ርቀን ዋጋ ያላት ደስ የምታሰኝ፤ የእግዚአብሔርን ፀጋ ፤ ምህረቱን፤ ቸርነት ደግነቱን የምንቀምስበት ጾም ትሁንልን ፤አሜን።

No comments: