Saturday, 31 March 2012

ለአንዱ ወዳጄ በጠባብዋ የደሀ አልጋዬ ላይ አብረን እንድንተኛ ትንሽ ተጠጋሁለት። እሱ ግን እንዲህ እያለ በሞራሌ ላይ ተሯሯጠ
“የደሀ ግድርድር ሀብታም ይጋብዛል አሉ! ኧረ ተው! ሲጥጥጥ….  አለች እኮ አልጋዋ። ኧረረረ! ልክ እንዳንተ ትንሽ ሲነኳት ትጮኻለች; እኔ የምልህ በለንደን ባልጠፋ አልጋ መፃጉዕ ይተኛባት የምትመስለውን ይህችን አንድፍሬ ምን ልሁን ብለህ ገዛህ?” አለኝ ታላቁ ወዳጄ በጣም እያዘነልኝ። “ማግኘትንም ሆነ ማጣትን አይቻለሁ; ያለኝ ይበቃኛ ማለትን ተምሬያለሁ” የሚለውን ጥቅስ ከግድግዳው ላይ እንዲያነብ በዓይኔ ጋበዝኩት፤ እሱም በዓይኑ ለንባብ አላርጂክ እንደ ሆነ ነገረኝ። በንግግሩ አልጋዬም አዝናለች መሰል  ቋቋቋ…..ሲጥጥጥ….. እያለች ለሊቱን ሙሉ እያለቀሰች አደረች!  ወዳጄ ለምን መሰለህ ይህችን ጠባብ አልጋ የምወዳት? አልኩት። እህሳ? አለኝ። ጠባብ አልጋ የግድ ያስተቃቅፋል!”
ብዬ ማንኮራፋቴን ቀጠልኩ።
*  ይህች ሳምንት ኒቆዲሞስ ትባላለች። በአይሁድ ረበናት ፍራቻ ምክንያት ኒቆዲሞስ ከክርስቶስ ጋር የሚገናኘው በለሊት ነበር፤ ጌታችንም ስለ ጥምቀትና ስለ ነገረ ድህነት አስተምሮታል። ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን ሥጋ ለመከፈን በቅቷል። ታሪክ እንደነገረኝ ኒቆዲሞስ በመጨረሻ ጳጳስ ሆኗል።
አገልጋይና ንባብ // ብራናውን አምጣልኝ”

      ስትመጣ በጢሮአስ በአክርጳ ዘንድ የተውኩትን በርኖሱንና መጻህፍትን ይልቁንም ብራናውን አምጣልኝ። [2ኛ ጢሞ. 4:13]

የሕክምና ሰዎች ልዩ ልዩ ዓይነት ምግብ የሚመገብ ሰው የተለያዩ ቫይታሚኖች፣ ማዕድኖች እና ገንቢ ነገሮች የማግኘት ዕድሉ ይሰፋል እንደሚሉት ሁሉ ልዩ ልዩ ዓይነት መጻሕፍትን ማንበብም እንደዚሁ ነው፡፡ አንዳንድ መጽሐፍን ለመቅመስ ስንል አንዳንድ መጽሐፍትን ደግሞ ለመመገብ ስንል አንዳንድ መጽሐፍትን ደግሞ ለማጣጣም ስንል እናነባለን፤ እነሆ ንበብ ሰውን ሙሉ ያደርገዋልና።

ቅ/ጳውሎስ ስትመጣ በጢሮአስ በአክርጳ ዘንድ የተውኩትን በርኖሱንና መጻህፍትን ይልቁንም ብራናውን አምጣልኝ ነበር ያለው። እኛ ብንሆን ግን ስትመጣ ቅቤውን አትርሳ! በርበሬውም አይቅር! ኧረ ድርቆሹስ እንደምንም ተቸገርልኝ!! ነበር የምንለው።

ጠበቆች ሕግን በተመለከተ የተጻፉትን መጽሐፍትን በትጋት ያነባሉ፤ የሕክምና ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸውን መጽሐፍት ያነባሉ።  እንደዚሁ ሁሉም ባለበት ዘርፍ ሙሉ እውቀት እንዲያገኝ ማንበብ አለበት ማለት ነው።

አንድ ረጅም የባቡር ጉዙ የሚጠብቀው ሰው ራሱን ለንባብ ምቹ በሆነ የባቡሩ ማዕዘን ባለው ወንበር ላይ ይቀመጥና በዚህ ረጅም ጉዞ ለረጅም ጊዜ የሚጠቅመውን ብዙ ዕውቀት ያከማቻል! ባለንበት የአውሮፓዋ ሀገር ሰዎች በጉዟቸው ላይ ማንበብን የሚያዘወትሩት ለዚህ ነውና። ዓለም የምታውቀው በግል ተሽከርካሪው እየተጓዘ መፅሐፍትን የሚያነብ አንድ ታላቅ ኢትዮጲያዊ ነበር። ይህ ሰው ማን ነበር? እሱማ የማንበብን ልምድ ያስተማረን ባኮስ የተባለው ኢትዮጲያዊው ጃንደረባ ነው። ከደገኞቹ ሐዋርያት የነበረው ፊሊጶስም “የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው። ወዳጄ የምናነበውን ማስተዋል ታላቅ ነው። ታላቁ መፅሐፍ “አንባቢው ያስተውል!” ይላልና። [ማቴ 24]
እነሆ የግብፅ ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ የጳፋቸው ብዙ ድንቅ መጽሐፍት አሉ፤ መንፈሳዊ ቃላትና ጥቅማቸው፣ የባሕታዊያን ህይወት…. በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ቤተክርስቲያንህን እወቅ… ብናነባቸው እንዴት ታላቅና ጠቃሚ መጽሐፍት ናቸው። እነሆ የአስተሳሰብ አድማሳችንን ለማስፋት ማንበብ አለብን። እናንተ ካነበባችሁት ለእኛ ማካፈልን አትርሱ፤ እስኪ ለዛሬ እኔ ካነበብኩት ታሪክ ላካፍላችሁ፦
ዳግማዊ ምኒልክ (ሕዝቡ በፍቅር እምዬ ይላቸው ነበር) ኅዳር ፳፯ቀን ፲፰፻፹፰ (1888) .. ወላይታ ከጦና ዋና ከተማ ደልቦ ደረሱ፡፡ እዚኽ የመገኘታቸው ምስጢር የወላይታው ንጉሥ ጦና አልገብርም ብሎ በመሸፈቱ እሱን ለማረም ነበር፡፡“…አገር ከጠፋ በኋላ ሲያቀኑት ያሲቸግራል ግብርህን ይዘኽ ግባብለው በሽምግልና ቢሞክሩም መልሱ እምቢታ በመሆኑ አጤ ምኒልክ ዳሞት ተራራ ላይ ያሰፈሩትን ጦራቸውን አዘው በአንድ ጊዜ ወላይታን አስጨነቋት፣ንጉሥ ጦናም ቆስለው ተማረኩ፡፡ የሚገርመው ግን መፍቀሬ ሰብዕ እና የዲፕሎማሲ ሰው የሆኑት አጤ ምኒልክ አይ ወንድሜ እንዲያው በከንቱ ሕዝብ አስጨረስክብለው የንጉሥ ጦና ቁስል እንዲታጠብና እንዲታከም አደረጉ!!! ይህን ሳነብ በጣም ገረመኝ፤ አንድ የመፅሐፍ ቅዱስን ታሪክም ወዲያው ትዝ አለኝ፤ ነብዩ ኤላሳዕ የሶርያን ሠራዊት ካስማረከ በኋላ አብልቶና አጠጥቶ ወደ ሀገራቸው እንደላካቸው! ፪ ነገ ፮            
ታላቁ ሰው ምኒልክ የተማረከው የባላገሩ ከብት እንዲመለስ አድርገው፣ንጉሥ ጦና እስኪያገግሙ ጠብቀው የወላይታን ሕዝብ ሰብስበው“…እንግዲህ ወዲህ የሚያስተዳድርህ ልጄ ወዳጄ ጦና ነውና ተገዛለት፡፡ አውቆ ሳይሆን ሳያውቅ እኔን የበደለ መስሎት ሰው አስጨረሰ እንጂ ከድሮም ከአያቶቻችን ቂም የለንምና መልሼ እሱን ሾሜልሃለው፡፡እንግዲህ ወዲህ ብታምጽ በራስህ ዕወቅ፡፡ ግብሬን አግባ፡፡…”የሚል አዋጅ አስነግረው የወጉዋቸውን ጦናን ሾመው ጥር ፲፩ቀን አዲስ አበባ ገቡ። (አጤ ምኒልክ መጽሐፍ በጳውሎስ ኞኞ)

ወሥበሐት

 ለእግዚአብሔር

ተክለ መድህን

No comments: