Thursday, 1 December 2011


   በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን እኛ የምንለምነውን ልመና እንዴት መስማት ይችላሉ???


አብርሐም በሉቃስ ወንጌል የተጻፈ አንድ ታሪክ አለ፤ ሃጥኡ ነዌ በሲኦል እያለ ከሩቅ በገነት አብርሐምን አየውና አብርሐም አባት ሆይ እኔ በሲኦል እሣት እጅግ እየተሰቃየሁ ነውና እባክህን ምላሴን በቀዝቃዛ ውሃ እንዲያርስልኝ አላዛርን ላክልኝ አለው፤ አብርሐምም በኛና በናንተ መካከል ታላቅ ገደል አለ ብሎ መለሰለት፤ ነዌም እንግዲያው በዓለም የሚኖሩ 5 ወንድሞች አሉኝና እባክህን አላዛርን ላከው አለ፤ አብርሐም የሚገርም ቃል ተናገረ ለነሱ ሙሴና ነብያት አሏቸው አለ ይገርማል አብርሐም ሙሴን የት አየው? መቼ ተገናኘው? አብርሐምና ሙሴ በዓለም አልተገናኙም ነገር ግን አብርሐም በአካለ ነፍስ ሆኖ ሙሴ እንደመጣ; መጽሐፍትን እንደጻፈ; ተዓምራትን እንደሰራ; የኤርትራን ባህር እንደከፈለ ያውቅ ነበር!! አዎ በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን በዓለም የሚከናወነውን ሁሉ ከእኛ በላይ ያውቃሉ; ስለእኛም ይለምናሉ፤

እንዃን ለአቡነ ተክለሐይማኖት እና ለሰማዕቱ ቅ/ጊዮርጊስ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!


ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ



ከቅዱስ ያሬድ ቀጥሎ ታላቅ ቦታየያዘ ኢትዮጵያዊ ሊቅ፡፡ 


ዐፄ ዳዊት  ደግሞ «ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ» ብለውታል፡፡

አባ ጊዮርጊስ የተወለደው 1357 . ነው፡፡ /ገድሉ ያረፈበትን ዘመንና ያረፈው በተወለደ 60 ዓመቱ መሆኑን ስለሚገልጥ ከዚያ በመነሣት የሚገኝ ነው፡፡/ ወላጆቹ ልጅ ስለሌላቸው ዘወትር እያዘኑ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ የተወለደው በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት መሆኑን ድርሳነ ዑራኤል ይተርክልናል፡፡



አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ አሁንም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡

ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ «ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ» ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀ መርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- «እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ 'አልዓዛርን የት ቀበራችሁትብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ? » ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡

በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱም እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ በአልጋ ላይ ሆኖም በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል «እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምንበዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡
አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱ «በምጽአት ጊዜ የሚመጣው ወልድ ብቻውን እንጂ አብና መንፈስ ቅዱስ አይመጡም»  የሚል ኑፋቄ ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ቢቱ ከዚህ ኑፋቄው በተጨማሪ የጥንቆላ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ቢቱ በጥንቆላ ሥራው የተሳ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት የነበረው ሰው እንደ ነበረ ገድሉ ይናገራል፡፡ ይህን መሰሉን ተግባር አጥብቆ የተዋጋው ዘርዐ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ ነገሥታቱ ምንም ክርስቲያኖች ቢሆኑ በዚህ መሰሉ ስንኩል ሕፀፅ ይዋጡ ነበር፡፡

ቢቱና አባ ጊዮርጊስ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ጳጳሱና ሊቃውንቱ ባሉበት እንዲነጋገሩ ስለ ወሰነ ጳጳሱ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ተንኮለኛው ቢቱ ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ከተከራከረ እንደሚረታ ስላወቀ ንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ክዷልና አትምጣ የሚል ደብዳቤ በአባ ጊዮርጊስ ስም ጽፎ ጳጳሱን ሊጠሩ በሄዱት መልእክተኞች እጅ ላከ፡፡ ወድያውም ለዐፄ ዳዊት ይህንን ነገር አሳበቀ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ፈጣን መልእክተኞች ልኮ የፊተኞቹ መልእክተኞች እንዲመለሱ አደረገና ደብዳቤው ተነበበ፡፡ የቢቱ ተንኮል ያልገባው ንጉሥ ዳዊት ይህን ደብዳቤ ሲመለከት አባ ጊዮርጊስን በደም አበላ እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡

አባ ጊዮርጊስ በወኅኒ ቤት እያለ ጴጥሮስና ጳውሎስ እየመጡ ያጽናኑት ነበር፡፡ ውዳሴ ሐዋርያት  የተሰኘውንና የሐዋርያትን ምስጋና የያዘውን መጽሐፍ ያዘጋጀው በወኅኒ በነበረ ጊዜ ነው፡፡ አብዛኞቹን ድርሰቶቹን በዚህ ጊዜ ሳያዘጋጃቸው እንደማይቀር ይገመታል፡፡ ዐፄ ዳዊት በሞተ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እጅግ አድርጎ አዘነ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች «በመሞቱ ደስ ልትሰኝ ይገባሃል እንጂ እንዴት ታለቅሳለህብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን «ጥቂት ቢኖር እወዳለሁ፤ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ነውና» ብሎ ነበር የመለሰው፡፡
ዐፄ ቴዎድሮስ አባ ጊዮርጊስን ከወኅኒ ቤት አውጥቶት በጥንቱ ቦታ አስቀመጠው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን የቤተ መንግሥትን ነገር ለመሸሽ ስለ ፈለገ በጋሥጫ ከመቀመጥ ይልቅ ርቆ ጥንት ወደ ነበረበት ወደ ዳሞት በመሄድ ማስተማር ጀመረ፡፡ ወደ ዳሞት ሲሄድ እግረ መንገዱን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን መቃብር ተሳልሟል፡፡ በዚያ ጊዜ የደብረ ሊባኖሱ አበ ምኔት እጨጌ ዮሐንስ ከማ /ሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ/ እንደ ነበሩ ገድሉ ይናገራል፡፡

ነገር ግን በዕውቀቱ የሚቀኑበት፣ በችሎታው የሚመቀኙት ሰዎች ነገር ሠርተው ከንጉሥ ቴዎድሮስ ጋር ስላጣሉት እልም ካለ በረሃ እንዲጋዝ ተደረገ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት የወጣው ዐፄ ቴዎድሮስ ሲሞት ነበር፡፡

የአባ ጊዮርጊስ ሌላው ተማሪ የነበረው ዐፄ ይስሐቅ 1399 . መንግሥቱን ሲይዝ አባ ጊዮርጊስን ከግዞት አውጥቶ ወደ ጋሥጫ መለሰው፡፡ በዚያ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እድሜው 42 ዓመት ሲሆን በስደትና በጤንነት መታወክ የተነሣ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜውን በጾም፣ በጸሎትና በድርሰት ያውለው ነበር፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ ? ይሉት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ «ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው» ብሎ መለሰው፡፡አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን «አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ እዚያው ገዳሙን ያገልግል » ብሎ እንደ ገና ላከው፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዕውቀት ስለ ተሠወረው ሁልጊዜ በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከ ይጸልይ ነበር፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር ፡፡ አንድ ቀን እመቤታችን ተገለጠችለትና «አይዞህ ዕውቀት የተሠወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነውና ታገሥ» አለችው፡፡ ከዚያም ጽዋዕ ልቦና አጠጣችው፡፡ ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ነበር፡፡
ከመነኮሰ በኋላ ወደ ሸግላ በመምጣት «ወእምድኅረዝ ኮነ አቡነ ጊዮርጊስ መምህር ለነገሥት ወለካህናት ዘደብተራ ወለኩሉ ዐበይተ ቤተ መንግሥት፣ ለንቡራነ እድ ወለመኳንንት፣ ለመሳፍንት ወለኩሉ ተዐይነ ቤተ መንግሥት- ከዚህ በኋላ ለነገሥታትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ካህናት እንዲሁም በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ታላላቆች፣ ለንቡራነ እድና ለመኳንንት፣ ለመሳፍንትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ባለሟሎች ሁሉ መምህር ሆነ፡፡»

የመጀመርያው ድርሰቱ አርጋኖን  የተሰኘውና በቅኔ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚያመሰግነው መጽሐፉ ነው፡፡ ስለ አርጋኖን ድርሰቱ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጠዋል «ወሰመዮ በሠለስቱ አስማት ዘውእቶሙ አርጋኖነ ውዳሴ፣ ወመሰንቆ መዝሙር ወእንዚራ ስብሐት - በሦስት ስሞችም ሰየማቸው እነርሱም አርጋኖነ ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙርና እንዚራ ስብሐት  ይባላሉ፡፡»

እመቤታችን አርጋኖንን ስለ ወደደችለት ዚማት ሚባለው ሀገር በነበረ ጊዜ «ከድርሰቶችህ ሁሉ እንደ አርጋኖን የምወደው የለም»  ብላዋለች፡፡ ዐፄ ዳዊትም ድርሰቱን በጣም ከመውደዱ የተነሣ በወርቅ ቀለም እንዳጻፈው ገድሉ ይገልጣል፡፡

ከዚህ በኋላ የደረሰው ድሰት ውዳሴ መስቀል ይባላል፡፡ ቀጥሎም መጽሐፈ ስብሐት ዘመዓልት ወዘሌሊት የተባለውን /ወይም እርሱ ራሱ መጽሐፈ ብርሃን ብሎ የሰየመውን/ መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

በዚያ ጊዜ በነበረው ልማድ ካህናቱ ቁርባን በሚያቀብሉ ጊዜ ሕዝቡ ወደ ካህናቱ መጥተው ሲቀበሉ ንግሥቲቱ ግን ካለችበት ካህናቱ ሄደው ነበር የሚያቆርቧት፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን «ይህ ቁርባን ንጉሠ ነገሥት ነውና ንግሥቲቱ ወደዚህ መጥታ ልትቀበል ይገባታል እንጂ እኛ መሄድ የለብንም » ሲል ተቃወመ፡፡ ይህ ነገር ንግሥቲቱንና አባ ጊዮርጊስን ስላጋጫቸው ዐፄ ዳዊት ችግሩን ለመፍታት አባ ጊዮርጊስን ወደ ሀገረ ዳሞት ንቡረ እድነት ሾሞ ላከው፡፡
አባ ጊዮርጊስና አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የተገናኙት አባ ጊዮርጊስ ወደ ዳሞት በሚጓዝ ጊዜ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ አለባበሱ እንደ ተርታ ሰው በመሆኑ አቡነ ሳሙኤል በመጀመርያ አላወቁትም ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ አባ ጊዮርጊስ ቅር ብሎት ወደ ዳሞት ተመለሰ፡፡ እንደ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ግምት ሁለቱን ያላግባባው ሥርዓተ ጸሎት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚያ ጊዜ በዋልድባ ሥርዓተ ጸሎቱ ሰባት ጊዜ በቀን መጸለይን የሚያዝ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በቀን ሰባት ጊዜ ብቻ መጸለዩ ለእግዚአብሔር ያንሰዋል ብሎ ያምን ነበር፡፡ ምናልባትም በዚያን ጊዜ 22 ሰዓት የሚፈጀውን ሰዓታት ሳያዘጋጅ አልቀረም፡፡

ከዚህ በኋላ የአባ ጊዮርጊስ ዋናው ትኩረቱ በድርሰቱ ላይ ሆነ፡፡ ወደ ጳጳሱ ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ዘንድ በመሄድ የቅዳሴ ድርሰት ለመድረስ እንዲፈቀድለት ከጠየቀ በኋላ የቅዳሴ ድርሰት ማዘጋጀቱን ገድሉ ይገልጣል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ቅዳሴያት ደራሲያቸው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍንጭ የሚሰጠን ይሆናል፡፡ ገድሉ እንደሚተርከው አንዳንድ ካህናት የአባ ጊዮርጊስን ቅዳሴ ተቃውመው ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አርዮስን በቀጣበት መንገድ ቀጥቷቸዋል፡፡

«ወበአሐቲ መዋዕል ተስዕሎ አሐዱ መስፍን ዘስሙ ቴዎድሮስ ዘይሰመይ ካዕበ ሊቀ ሐራ በእንተ ሃይማኖት ርትዕት ወደረሰ ሎቱ መጽሐፍ ዘይሰመይ ፍካሬ ሃይማኖት፡፡ ወሶበ ርእይዎ ወአንበብዎ ለውእቱ መጽሐፍ ንጉሥ ወኩሎሙ ካህናተ ምሥጢር ይቤሉ አማንኪ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ ወቄርሎስ አፈ በረከት ተንሥኡ በመዋዕሊነ፡፡ ኢትዮጵያ ተመሰለት በቁስጥንጥንያ፣ ወተአረየታ ላዕለ እስክንድርያ - አንድ ቀን ቴዎድሮስ የተባለ መስፍን፣ ዳግመኛም የጦሩ አዛዥ የሚሆን አባ ጊዮርጊስን ስለ ርትዕት ሃይማኖት ጠየቀው፤
አባ ጊዮርጊስም ፍካሬ ይማኖት  የተባለውን መጽሐፍ ደርሶ ሰጠው፡፡ ንጉሡና የምሥጢር ሊቃውንት የሆኑ ካህናት ይህንን በተመለከቱና ባነበቡ ጊዜ በእውነት ዮሐንስ አፈወርቅና አፈ በረከት የሆነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ቁስጥንጥንያን መስላለች፣ ከእስክንድርያም በላይ ከፍ ከፍ ብላለች ብለው አደነቁ» ይላል ገድሉ፡፡  የዘረዘራቸው የመናፍቃን ስሞችን እና ክህደታቸውን ስናይ በዘመኑ የነበሩ ሊቃውንት ስለ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያላቸውን ዕውቀት ያሳየናል፡፡

አባ ጊዮርጊስ መከራ ያልተለየው አባት ነበር፡፡ ገድሉ እንደሚተርከው በቤተ መንግሥቱ የነበሩ ሰዎች የርሱን መከበርና መወደድ አይፈልጉትም ነበር፡፡ በተለይም ፍካሬ ሃይማኖት  የተሰኘውን መጽሐፍ በመጻፉ የተነሣ መከበሩ አልተዋጠላቸውም፡፡ ስለዚህም ነገር ሠርተው ከዐፄ ይስሐቅ ጋር አጣሉት፡፡

ዐፄ ይስሐቅ አባ ጊዮርጊስን አሳስሮ ውኃ ወደማይገኝበት ዐለታማ ቦታ አጋዘው፡፡ በዚያም በመከራ ለብዙ ጊዜ ኖረ፡፡ በዚያ እያለ ዘወትር በጸሎት አብዝቶ ይተጋ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዐፄ ይስሐቅ ወደ ልቡናው እንዲመለስ አደረገ፡፡ ንጉሡ በአባ ጊዮርጊስ ላይ የፈጸመው ነገር ሁሉ ፀፀተው፡፡ አገልጋዮቹንም ጠርቶ አባ ጊዮርጊስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ተንኮል ሠሪዎች የአባ ጊዮርጊስ መምጣት ተንኮላቸውን ስለሚያጋልጠው አባ ጊዮርጊስ ሞቷል ብለው አስወሩ፡፡ ይህንን ሲሰማ ዐፄ ይስሐቅ ፈጽሞ አዘነ፡፡

አባ ጊዮርጊስ ሞቷል እየተባለ መወራቱን ከደቀ መዝሙሩ ስለ ሰማ በሕይወት የመኖሩን ዜና ጽፎ ለዐፄ ይስሐቅ እንዲያደርስለት አውሎ ንፋስን ላከው፡፡ አውሎ ንፋሱ ደብዳቤውን ተሸክሞ በመሄድ ዐፄ ይስሐቅ በድንኳን ተቀምጦ በነበረ ጊዜ ጉልበቱ ላይ አስቀመጠው፡፡ ንጉሡ ምትሐት የተሠራበት ስለ መሰለው ደነገጠና መኳንንቱንና ሕዝቡን ሰብስቦ ጉዳዩን ገለጠ፡፡ ወዲያውም አሳት አስነድዶ ቢጥለው ሊቃጠል አልቻለም፡፡ ወደ ውኃም ቢጨምረው አልጠፋም፡፡ በዚህ ተደንቆ ወረቀቱን ከፍቶ አነበበው፡፡ ደብዳቤው ከአባ ጊዮርጊስ የተላከ መሆኑን ሲያውቅ ዐፄ ይስሐቅ ደነገጠ፡፡ እነዚያን መልእክተኞች ይዞ ወደ ወኅኒ ጨመራቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስንም ከግዞት ያወጡት ዘንድ ላከ፡፡

አባ ጊዮርጊስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመጣ ንጉሡ በደስታ ተቀበለው፡፡ ደብዳቤውን በማን እጅ እንደ ላከውም ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ደብዳቤውን በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በነፋስ እንደ ላከው አስረዳ፡፡

ከግዞት ከተመለሰ በኋላ እመቤታችን ተገልጣለት መከራው ሁሉ እንደ ሐዋርያት መሆኑን ገለጠችለት፡፡ አእምሮውን ብሩህ፣ ልቡናውን ትጉኅ የሚያደርግ እጅግ ብዙ ምሥጢር ነገረችው፡፡ ተሰናብታው ከሄደች በኋላ «እጅግ ብዙ መብራት አቅርቡ አምስት ፈጣን ጸሐፊዎችንም አምጡ » ብሎ አዘዘ፡፡ እርሱ እየነገራቸው እነርሱ እየጻፉ እረፍት ሳያደርጉ ሦስት ቀን ሙሉ አስጽፎ መጽሐፈ ምሥጢር የተሰኘውን መጽሐፍ ፈጸመ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ይህንን ያደረገው ምናልባት በስደትና በመከራ ስለ ደከመ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አምስቱ ጸሐፍት የየድርሻቸውን አጠናቅቀው በ፩ድ አደረጉት፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይህን ተመልክቶ በእጅጉ አደነቀ፡፡ «እኔ የዚህን መጽሐፍ ቃል አልተናገርኩም፤ መንፈስ ቅዱስ በእኔ አፍ ተናገረ እንጂ » ሲል በወቅቱ መመስከሩን ገድሉ ይናገራል፡፡

ይህንም መጽሐፍ መጽሐፈ ምሥጢር ሲል ሰየመው፡፡ የጻፈው 1409 . እድሜው 52 በደረሰ ጊዜ ሲሆን የዚህ መጽሐፍ ቅጅ በነጋድያን እጅ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ በወቅቱ ሄዶ እንደ ነበር ገድሉ ያስረዳል፡፡

መጽሐፈ ምሥጢር የተጻፈበትን ዘመንና ምክንያት የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዜና መዋዕል ከዚህ በተለየ ነው የሚያስቀምጠው፡፡ «በመዋዕሊሁ ለዝንቱ ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ኮነ ተቃሕዎ በእንተ ሃይማኖት ወተዋሥአ አባ ጊዮርጊስ ምስለ አሐዱ አፍርንጅ ወሞዓ እስከ ከሠተ ወጸሐፈ መጽሐፈ ምሥጢር - በዚህ በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በሃይማኖት ምክንያት ክርክር ሆነ፡፡ አባ ጊዮርጊስም ከአንድ ፈረንጅ ጋር ተከራክሮ ረታው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢር የተባለውን መጽሐፍም ደረሰ፡፡»  ይላል፡፡ ይህ ግን የሚያስኬድ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ዐርፎ ነበርና፡፡

 ንጉሥ ይስሐቅ ክረምቱን ያሳልፍበት በነበረው ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠራ፡፡ በዚያም በማስተማርና በጾም በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ በጋሥጫ እያለ ዐፄ ይስሐቅ አስጠራው፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሡ የመናገሻ ማርያምን ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ ስለ ነበር እንዲባርክለት ፈልጎ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ታምሞ የተኛም ቢሆን ወደ ንጉሡ ተጓዘ፡፡ እዚያ ሲደርስ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ለመፈጸምም ዐቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ይስሐቅ በአልጋ ተሸክመውት እንዲዞሩና ቤተ ክርስቲያኗን እንዲባርካት አደረገ፡፡

ቡራኬውን ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሮቹን ሰብስቦ «ከሞትኩ አባቴ በጸሎተ ሚካኤል መከራ ወደ ተቀበለባትና እኔም ቤተ ክርስቲያን ወዳነፅኩባት ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩኝ» ሲል አዘዛቸው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻ የስንብት ትምህርቱን እያስተማራቸው እነርሱም በአልጋ ተሸክመውት ወደ ጋሥጫ እያመሩ ሳለ በመንገድ ላይ ሐምሌ ሰባት ቀን 1417 . 60 ዓመቱ ዐረፈ፡፡

 ከመናገሻ ወደ ጋሥጫ የሚወስደው መንገድ በአዲስ አበባ በኩል አድርጎ፣ በደብረ ጽጌ በኩል ወጥቶ፣ በመርሐ ቤቴና በጉንደ መስቀል በኩል በማለፍ በሚዳና በወረሞ በኩል ወደ ቦረና የሚሻገር ይመስላል፡፡

እስካሁን ድረስ ያሉን ምንጮች የአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች ቁጥራቸው ከዐርባ በላይ እንደሆኑ ይገልጣሉ፡፡ በስም የምናውቃቸው ግን የሚከተሉትን ብቻ ነው፡፡ ምናልባት ብዙ ጥናት ማድረግ ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡

1. ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት

2. ኖኅተ ብርሃን /ከመጽሐፈ አርጋኖን ጋር አብሮ ታትሟል/

3. ውዳሴ መስቀል

4. ቅዳሴ

5. ውዳሴ ሐዋርያት

6. አርጋኖነ ውዳሴ

7. ፍካሬ ሃይማኖት

8. መጽሐፈ ምሥጢር

9. ውዳሴ ስብሐት

10. እንዚራ ስብሐት

11. ሕይወተ ማርያም

12. ተአምኖ ቅዱሳን

13. መጽሐፈ ብርሃን

14. ጸሎት ዘቤት ቤት

የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ገዳም በደቡብ ወሎ ቦረና ውስጥ ይገኛል፡፡ ከደሴ እስከ ከላላ አንድ ቀን፤ ከከላላ እስከ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አንድ ቀን ይወስዳል፡፡ ገዳሙ ዙርያውን በሙስሊም የተከበበ፤ በተራራ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር የአካባቢው ሙስሊሞች ለገዳሙ ልዩ ከበሬታ አላቸው፡፡


ባለፈው ጊዜ ስለ ኢትዮጲያዊው ሙሴ ጸሊሙ አይተን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ከብዙ በጥቂቱ ከረጅሙ በአጭሩ ስሙ እና ክብሩ የተዘነጋውን ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አይተናል። በቅርቡ የሌሎች ቅዱሳን ታሪክ ይጠብቆታል ፤ ማን ይሆን? ቅ/ መቃርስ? አባ አጋቶን?  አባ መርትያኖስ? ወይስ ማን? ይቆየን

“ከልብ ለምወዳት ሰንበት ትምህርት ቤቴ”

ይጎብኙ ገንቢ አስተያየትም እንዲሰጡ በአክብሮት ተጋብዘዋል፦

ልዩ ልዩ አዝናኝና አስተማሪ ጽሁፎች ፤ ስንክሳር /Holly Father’s Encyclopedia/   ገድላት ፤ ታሪኮች ፤ ሀገራዊ እይታዎች ፤ ይነበብበታል።

የእነ ቅ/መቃርስ ፣ ቅ/አጋቶን ፣ቅ/ያሬድ ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ፤ ፣ ሙሴ ጸሊሙ ፣ አባ ቢሶይ ... ድንቅ ትምህርቶች ገበታ ተዘርግቶ ይበላባታል፤

የእነ ቅ/ጳውሎስ ፤ የሐዋርያቱ ሁሉ ግሩም ትምህርት ይታይባታል፤

ከግብጽ ፓትርያርክ ከአቡነ ሺኖዳ የተለያዩ ምክር አዘል ጽሁፎች ይቀርብባታል፤

የሃገራችንን ታሪክ እነ አጼ ቴዎድሮስ እነ ሚኒሊክ ሌሎችም ከታሪካቸው ያስተምሩናል፤

ይህች የምወዳት ሰ/ት/ቤቴ ያልዃት በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥርዓቷንና ደንቧን የጠበቀች ስትሆን ከማንኛውም ዘር እና ፖለቲካ 100% Neutral ነጻ ናት።

-//-

7 comments:

Yeti Mehari said...

Kale hiwot yasemalen yetsadkan yesemaetat yekdusan amalajinet zewetir ayileyen bereketachew yiderbn amen !!!Tuesday at 8:51pm via mobile · LikeUnlike · 1Helen Free likes this.

Aklilu Tegenu said...

GOD bless you!!! That clears many doubts.Tuesday at 12:38pm · LikeUnlike

Gezahagn Fantahun said...

እግዚአብሔር አምላክ ከመረጥኩት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረኩ እንዳለ መዝ 88(89) ፡3 ቅዱሳን ከዕረፍተ ሞታቸው በኋላ እንደቀደመው በአጸደ ስጋ እያሉ ሲያደርጉ እንደነበረው የመጾም ፤የመስገድ ፤ ልዬ ልዬ መከራዎችን መቀበል ባይኖርባቸውም አስቀድመው ባደረጉት ተጋድሎ በተሰጣቸውን የማማለድ ጸጋ አምነው ስማቸውን የሚጠሩ ሰዎች ሲድኑበት እናያለን ለዚህም ቆላ 2፡5 ‹‹በስጋ ምንም እንኳ ብርቅ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ ›› እንዳለ ሐዋሪያው ይህም የሚያስረዳን ቅዱሳን ከእረፍታቸው በኋላ ከእኛ የማይርቁ መሆኑን ነው፡፡ በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርገን ከብሉይ ኪዳን 2 ነገ 13፡20 ‹‹ኤልሳዕ ሞቶ ቀበሩትም ከሞዓብም አደጋ ጣዬች በየዓመቱ ወደ ሀገሩ ይገቡ ነበር፡፡ ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዬች አዬ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዬው ድኖ በእግሩ ቆመ ›› ነብዬ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝ 88፡34 ‹‹ኪዳኔንም አላረክስም ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም ››እንዳለ ሐዋሪያው ይሁዳ ከላይ የተገለጸውን ቃል ሲያጠናክር ይሁ 1፡14-16 ‹‹……ስለ ሰው ልጆችም ፈጽመው ይለምናሉ ይፀልያሉ ›› በማለት ቅዱሳን በዚህ ዓለም ስላሉ ሰዎች እንደሚማልዱ የገለጸው፡፡Tuesday at 1:34pm · LikeUnlike · 3Yeti Mehari, Rahel Alemu and Memar Alebachew like this.

Gosaye Alemu said...

kal hiwet yasemalenTuesday at 7:57pm · LikeUnlike · 1Helen Free likes this.

Anonymous said...

Tewodros Kebede Mekonnen, Yeti Mehari, Genet Salomon and 15 others like this.

Girum Aramde said...

Kibret kale hiwote yasemalen!Tuesday at 9:36pm · LikeUnlike

Tige Love said...

inkan abero adresen......betame ijig betam geta yibarike berta legha tilike temeret new,,,,,kale hiwotin yasemalin!!!! thank you