Monday, 12 August 2013

ስምህ ማን ነው?





ማልኮስ ንጉሥ ማለት ነው። ሆኖም በወንጌል የሊቀ ካህናቱ ባርያ ተባለ።

ቄሳር ብርኃን ማለት ነው። በጭለማ ኖረና ስሙን አቃለለ።

አይሁድ ማለት ታማኝ ማለት ነው። ለጌታቸው አልታመኑምና ክቡር ስሙን አቃለሉት።

እረኛ፦

በጉን የሚጠብቅ እረኛ ለበጉ ነፍስ አስቦ ነውን? ከተኩላ የሚጠብቀው ስለምንድን ነው? በጉ በሰባ ጊዜ አጋድሞ አርዶ ሊበላው አይደለምን? እራሱ ባይበላው እንኳን ወደ ገበያ አውጥቶ ሊሸጠው አይደለምን? ታማኝ አይደለምና ይህ ምንደኛ እረኛ ይባላል። አዬ ስም! አዬ እረኛ!

የዓለም እረኛ በግ ሆኖ ተወለደ! እውነተኛው እረኛ ግን ከተኩላ የጠበቀን ሊበላን አልያም ሊሸጠን ያይደለ ለታላቅ ፍቅር ነው። ይልቁንም በበጎቹ ፋንታ እረኛው በግ ሆነ። ከተኩላ የጠበቀን ሊበላን አልያም ሊሸጠን አይደለምና ይልቁንም ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ አለን።

እኛም ስማችን እንደ ግብራችን ካልሆነ ይቅርብን። ክርስቲያን ሆነን አህዛብን ከመሰልን ከንቱ ነው። ስማችን ከብዶናልና እንደ ባስ በቁጥር ብንጠራ ሳይሻል አይቀርም። 24 31 እየተባልን ብንጠራ የሚል ሐሳብ አለ አሉ!

ዳንኤል ማለት እግዚአብሔር ዳኛዬ ነው ማለት ነው፤ ለዳንኤል ዳኛው ጠንቋይ ከሆነ ክቡር ስሙን አቃለለ ይባላል። ነቢዩ ዮናስ ልክ እንደ ስሙ የዋህ ነበር፤ ዮናስ ተብለን ክፉ ከሆንን አያድርስ ነው። እስኪ የራሳችሁን ስም ተርጉሙትና ትክክል መሆኑን ፈትሹ። ስሙ ከግብሩ የሰመረለት እድለኛ ነው።

አንዲት እናት ለልጅዋ ሜልኮል የሚል ስም አወጣችላት። እንዴት ሜልኮል አልሻት ? ብለን ጠየቅናት። ሜልኮል የሚለው ስም ደስ ይላል የዳዊት ሚስት እንደሆነችም ሰምቻለው አለችን። ሜልኮል እኮ የዳዊትን ዝማሬ ተቃውማ ማህጸንዋ የተዘጋ ሴት ናት ብለን የልጅቱ ስም ሩት በሚል ተቀየረ። አንዳንዶች ባለማወቅ ኤልሻዳይ ብለው ራሳቸውን ይጠራሉ። ይህ ግን ስህተት ነው። ኤልሻዳይ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ብቻ ነውና!

የውኃ እናት ፦ በውኃ ውስጥ የምትኖር እንስሳ ናት። ውኃ ከሌለ የውኃ እናት የለችምና ስሟ የተዛባ ነው። የውኃ ልጅ መባል ሲገባት የውኃ እናት ተብላለችና። የብርኃን እናት፣ እመ አምላክ፣ የፍቅር እናት፣ የሰላም እናት! ስሟ ከግብሯ የሰመረ ይህች ድንቅ እናት ማን ናት? ማርያምስ ክቡር ስሟን አላቃለለችም።

http://yonas-zekarias.blogspot.com/

No comments: