Friday, 6 July 2012

ከባድ ጦርነት ታውጆብናል!



ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው የተነሱ የዓለማችን ኃያላን መንግሥታት ካልተቧቀስን አናርፍም ብለዋል። ዛሬ ጠዋት በወጣው የቢቢሲ ዜና ለዘመናት የተፈራው ታላቅ ጦርነት እንደሚነሳ ምንጮች እየዘገቡ ነው። የምን መታገስ ነው ሲሰበር ይንሰጠር ያሉም አልጠፉም። ቀን ሲደርስ አንባ ይፈርስ እንዲሉ የጦርነቱ ቀን ደረሰ።

ሥጋ ሠራዊቱን ዘመዶቹን እነ ዘረኝነትን እነ መከፋፈልን ፣ ዝሙትን፣ ቅናትን ፣ ምቀኝነትን አስከትሎ ደረቱን ነፍቶ ልቡን አሳብጦ ውረድ እንዋረድ እያለ ነፍስን ሊወጋ ይሸልል ጀመር። እትዬ ነፍስም በተራዋ ሠራዊቷን አስከትላ ዘመዶቿን እነ ፍቅርን እነ መቻቻልን ፣ ደግነትን ፣ ድንግልናን ፣ ጸሎትን ፣ስግደትን ፣ ጾምን ይዛ እንዲህ እያለች መፎከር ጀመረች።

አንተ ከንቱ በስባሽ አንተ ከንቱ አፈር፤
ሥጋ ለበሬ ነው ና እና በእኔ ተቀደስ።
አልመለስ ብትል ብትደነፋማ
ሞክረኸኝ እየኝ ጀግንነቴን እንካ

አለች እትዬ ነፍስ እየተውረገረገች።

ሥጋ ምድራዊ ነህ ነፍስ ሰማያዊ።

ሥጋ በስባሽ ነህ ነፍስ ዘላለማዊ።

ሥጋ ሟች ነህ ነፍስ ሕያው።

እንዲያው ወፈር ስትል ለዓይን ብትማርክ
ጉራህ አልተቻለ መቀመጫም አጣን።

እያለች ነፍስ ልቧ ቅቤ እስኪጠጣ ድረስ የልብ የልቧን እንደ ጉድ አዘነበችው።

አቶ ሥጋ በበኩላቸው አሸሼ ገዳሜ እሪ ብለው ጮኹ
አንቺ ነፍስ ዋ…. ዋ…. ዋ ዛሬ ጉድ ሳይፈላ
በትዕቢት ታውረሻል ዓይንሽ ይብራ እያሉ አብዝተው ፎከሩ።


እትዬ ነፍስ ለአቶ ሥጋ አንድ ታሪክ እንዲህ ብለው አወጓቸው፦ “ሰውዬው ድንኳን ሰባሪ ነው አሉ። ሁለት ቦታ የአቡዬ ድግስ እንዳለ ይሰማል፡፡ ሰዓቱ ሲደርስ እንደ ተጠራ ሰው የክት ልብሱን ለብሶ ይወጣል፡፡ የሁለቱም ድግስ የተለያየ ቦታ ነበር፡፡ ወደ አንደኛው እየሄደ ሳለ የዚያኛው ድግስ ቢበልጥስ ብሎ ተመለሰ፡፡ ወደዚያም ጉዞ እንደ ጀመረ የዚህኛው ምስር ሆኖ ያኛው ቁርጥ ቢሆንስ ብሎ እንደገና ተመለሰ፡፡ እንዲህ ሲያመነታ ሰዓቱ እያለፈበት ሄደ። በዚህ ጊዜ በመካከለኛ መንገድ ላይ ቆመና በጭንቀት ‹‹አቡዬ የዛሬን ብቻ ለሁለት ይሰንጥቁኝ›› ብሎ ጸለየ ይባላል!”

ዓለምንም እግዚአብሔርንም መያዝ አይቻልም፡፡ ሁለት አባሮም አንድ መያዝ አይቻልም፡፡ ሥጋንም ነፍስንም እሹሩሩ ማለት አይቻልም አሉ እትዬ ነፍስ አቶ ሥጋን እንደ ሕፃን እሹሩሩ እያሏቸው። ሕፃን ልጅ እናቱን አለቅሽም እያለ ገበያና ሥራ እስኪከለክል እንዳላስቸገረ፣ ሲያድግ ደግሞ እናቱን አትጠብቂኝ እያለ እንደሚፎክር እኛም እንደ ሕፃንኑ መሆን አንችልም አሉ እትዬ ነፍስ እያፌዙ። እዚህ ጋ አቶ ሥጋ አጎረመረሙ። እትዬ ነፍስ ግን አቶ ሥጋን ማናደድ እንደ ትርፍ ጊዜያቸው ያስደስታቸዋልና ማናደዱን እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ፦

 “ዓለማዊ ሰዎች ዓለምን ከፍ አድርገው እሽኮኮ ቢሏት በጀርባቸው ቢያዝሏት፣ እሹሩሩ ዓለም ቢሏት አይገርምም። ዓለማዊ ናቸውና ዓለምን ቢወዱ አይገርምም። ዓለም ራስዋ የሚገርማት ግን መንፈሳዊ ተብለን ዓለምን እሽኮኮ እናድርግሽ ስንላት ነው። በጀርባችን እንዘልሽ እሹሩሩ ዓለምዬ እንበልሽ ስንላት ዓለም ራስዋ ከትከት ብላ ትስቅብናለች! በዓለም ውስጥ ብንኖርም ዓለም በእኛ ውስጥ ከኖረች ግን አደጋ ነው! ደብረ ታቦር ላይ ዘምረው ቀራንዮ ላይ የከዱ ብዙዎች አሉ” አሉ እትዬ ነፍስ እንደ ምሁር ከረቫታቸውን ከፍ ዝቅ እያደረጉ።

ይህን ጊዜ አቶ ሥጋ ቦግ አሉ!! ንዴታቸው እንደ ጉድ ተቀጣጠለ። ወደ እትዬ ነፍስ ተንደረደሩና በያዙት ቢላ ክፉኛ ወግተው ዘነጣጥለው ፣ ዘነጣጥለው ገነጣጥለው ሊለቋቸው አሰቡና ተውት! እትዬ ነፍስን በቢላ ሳይሆን በቅኔ ወጋ ሊያደርጓቸው ፈለጉ። “ስለ ሥጋና ነፍስ ግዕዝ ምን እንዳለ አልሰሙም እንዴ?” አሉ አቶ ሥጋ እትዬ ነፍስን በፌዝ እያዩ።

ደግሞ ምን አለ? እትዬ ነፍስ ጠየቁ።

ስለ አንቺና እኔ ግዕዝ እንዲህ ብሏል

“ኢትቀውም ነፍስ ዘእንበለ ሥጋ”

ፐ… ፐ.. ፐ.. ደግሞ ምን ማለት ይኾን? አሉ እትዬ ነፍስ እየተውረገረጉ።

አቶ ሥጋም “ነፍስ ያለ ሥጋ አትቆምም ማለት ነዋ” ብለው በረዥሙ ሳቁ። አሁን ደግሞ እትዬ ነፍስ ቦግ አሉ። ቦግ ቦግ ማለት የሥጋና የነፍስ ልማዳቸው ሆነ። አይ ከዚያማ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው እንደ ጉድ ተቧቀሱ፣  እንደ ጉድ ታገሉ ፣  እንደ ጉድ ተፋጁ…. 


ቢቢሲ የዘገበው በሥጋና በነፍስ መካከል የተፋፋመውን ይህን ጦርነት ነበር!

ሰው የተፈጠረው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ነው። እነሱም እሳት ፣ ውኃ ፣ መሬት ፣ ነፋስ ናቸው።

አራቱ ባሕርያተ ሥጋ እርስ በእርሳቸው ተቃራኒ መስተፃርራን ናቸው። እሳት በውኃ ይጠፋል። እሳት ውኃን ያሞቃል። ነፋስ መሬትን ያንቀጠቅጣል። መሬት ተራራዎች ነፋስን ያቆማሉ። እንዲህ እርስ በእርሳቸው መስተፃርራን ናቸው። የሰው ልጅ ከነዚህ እርስ በእርሳቸው ተቃራኒ ከሆኑ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ስለተፈጠረ ሰውነቱ “የጦርነት ከተማ ነው” ይባላል። ሥጋና መንፈስ የሚዋጉበት ታላቅ የጦርነት ከተማ የሰው ልጅ ነው።

የነፍስ ሽለላ መቆሚያ አጣ
ትዘልፈው ዠመር ሥጋን እንዲህ ብላ

አልሰማህም ወይ አላለበብክም ወይ
ጳውሎስ በኤፌሶን ምን ብሎ እንደነበር?


ቅ/ጳውሎስ በሮማ እስር ቤት ታስሮ እያለ የእስር ቤቱን ጠባቂ እያየ መልዕቱን እንዲህ ብሎ መጻፍ ዠመረ።

የእምነት ጋሻ አንሱ ፤ የመዳንን የራስ ቁር አድርጉ፤ የመንፈስን ሰይፍ ያዙ። እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላመ ወንጌል ተጫምታችሁ ቁሙ። ጦርነቱ ከሥጋና ከደም ጋር አይደለም ከዚህ ዓለም ገዥ ከሆነው ከዲያቢሎስ ነው እንጂ ኤፌ [6: 14]


ምርጥ እቃ የተባለው ንዋየ ኅሩይ ቅ/ጳውሎስ የእስር ቤቱን ወታደር በማየት ብቻ ሚስጢር ያለውን መልዕክት ጽፏል።
ሮማዊያን ወታደሮች የሚለብሱት የጦርነት ትጥቅ ዘመናዊ ነበር። የራስ ቁር ማለት ከብረት የተሰራ በራስ ላይ የሚደረግ ሞተረኞች የሚያደርጉት እንደ ሄልሜት ያለ ነገር ነው። ዝናር ማለት ወገብን መታጠቂያ ነው። ጥሩር ማለት ከብረት የተሰራ የደረት መከላከያ ነው።


ይኼ ኹሉ ዝግጅት ጦርነት ስላለ ነው። ጦርነቱም በሥጋና በነፍ መካከል ነው። ሥጋ ሲያሸንፍ መበላላት ፣ መቦጫጨቅ ፣ መለያየት ፣ መነካከስ ፣ ዝሙት ፣ ዘረኝነት ምቀኝነት ጥላቻ ይሰለጥናሉ። ነፍስ እንደምንም ታግላ ተፍጨርጭራ ስታሸንፍ ፍቅር ፣ ሰላም ፣ ትህትና ፣ ትዕግስት ፣ ደግነት ይሰለጥናሉ። ለዚህ እኮ ነው ቅ/ጳውሎስ “ሥጋዬንም ለነፍሴ አስገዛዋለሁ” ያለው። 1ኛ ቆሮ. [9: 26]

       እነኾ የአቶ ሥጋና የእትዬ ነፍስ ጦርነት እስከ አለም ፍጻሜ ይቀጥላል። በመሃል እየገባን የጦርነቱን ዘገባ በትኩሱ እንዘግባለን። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሰበር ዜና እንደደረሰን ሥጋ በጦርነቱ ድል እየቀናው ነው። አያሌ ነፍሳት ዳግም እንዳይቆሙ ኾነው ተወግተው ቆስለዋል። የሕክምና ባለሙያዎቹ ካህናትም የቆሰሉትን ነፋሳት ለማከም ደፋ ቀና እያሉ ነው። የቀይ መስቀል ሠራተኞች መምህራንና ዘማርያንም የተቻላቸውን ለመርዳት እየተፋጠኑ ይመስላል። እንዲህ የተረዳችውም ነፍስ እያገገመች ትመስላለች።

ነፍስ ሥጋን ክፉኛ ልትወጋው ተንደረደረች!

አያያያያ ነፍሴ እንዴት ያለ ግሩም ቅጣት ምት ነበረች!

ግን ተስታለች!

ተስፋ

ለለፋ

ትመጣለች

ፊሽካ ሳይነፋ

እያለች ነፍስ አሁንም የሞት ሞትዋን ታግላ ተነሳች።

ማን ያሸንፍ ይኾን? 





ክርስትና እስልምና በኢትዮጲያ

አንድ የእስላም ባለ ሀብት ቤተክርስቲያን ለማሰራት ገንዘባቸውን ሰጡ አሉ። ቤተክርስቲያኑ ከተሰራ በኋላም በየአመቱ ኩንታል ጤፍ እየላኩ በዓላችሁን አክብሩበት ይሉ ነበር! እስላሙ ሕብረተሰብም በጉልበቱ ቤተክርስቲያን ሲሰራ ታይቷል። ክርስቲያኑም እንዲሁ ከእስላም የሃይማኖት መሪዎች ጋር በመሆን መስጊድ ሰርቷል። ይህ ነው ኢትዮጲያዊ ውበታችን!! ይህ ነው ከዓለም የሚለየን ውበታችን!!

ናይጄሪያ ነዳጅ ከማግኘትዋ በፊት ሰላም ነበረች። ነድጅ ስታገኝ የውጪ ኃይል ሰርገው ገቡና ከፋፈሏቸው። አይ ከዚያማ! እንደ ጉድ ተከፋፈሉ! እንደ ጉድ ተባሉ! እንደ ጉድ ተዘነጣጠሉ! እንደ ጉድ አለቁ! ይህን አታሳየኝ አለች ሴትዮዋ ይህንንስ ከኛ ያርቅልን። አንድነታችንና መቻቻላችን የሚፈተንበት ጊዜ አለ። የውጪ ኃይሎች ሰርገው ሲገቡ እንደ ጉድ እንፈተናለን እንደ ጉድ ብንከፋፈል እንደ ጉድ እናልቃለን ፣ እንደ ጉድ አንድ ብንሆን እንደ ጉድ እናድጋለን።

በፌስ ቡክ እና በ you tube ላይ የአክራሪነት መልእክት ያቀነቀኑ አሉ። እንጋደል፣ እናቃጥል፣ እንግደል የሚል ዜማ አውጥተው ነጠላ ዜማቸውን በቅርቡ የለቀቁ አሉ። ቢቻል ኦርጂናል ሲዲውን ካልሆነም ኮፒውን እንድንገዛ ብዙ አስተዋውቀዋል!  እውነተኛይቱ ሃይማኖት ግን እንዲህ አትልም። እውነተኞቹ የእስልምና አባቶች አክራሪነትን ስላልመረጡ ከስራቸው ተባረሩ። ለብዙ ዘመናት በየመስጊድ ጸሎት ሲያሰሙ የነበሩ ኢማም አክራሪ ስላልሆኑ ተባረዋል። እውነተኛቹ የእስልምና አባቶችና የእስላሙ ሕብረተሰብ የዋህ ናቸው። በአክራሪ ስም ቤተክርስቲያንን የሚያቃጥሉና ሰውን የሚገድሉ መጥፎ ፎቶዎችን በሕሊናችን ቀርጸዋል እንጂ የእስላሙ ሕብረተሰብ ማን እንደሆኑ የዋህ የሰላም ሰዎች እንደሆኑ በሚገባ እናውቃለን!

ቅ/ራጉኤል ቤተክርስቲያን ባሰራው ት/ቤት በምማርበት ጊዜ ከጎናችን መስጊድ አለ። ይህ መቻቻል ነው። በሌላው ዓለም ይህን እናድርግ ቢሉ ተባልተው ያልቃሉ እንጂ ይህ አንድነት የላቸውም። ባለሁባት በለንደን ከተማ የእስላም ሰፈር ለብቻው አለ። ክርስቲያኑ ደግሞ በተለየ ሰፈር ይኖራል። ይህ በሀገራችን ያለውን መቻቻል ፍንትው አድርጎ ያሳየናል።

 ሙሐጅር ለማ የሚባል ጓደኛ ነበረኝ። ከልጅነት ጀምሮ አብረን ነው ያደግነው። ትንሣኤ ሲሆን እኛ ቤት አይቀርም። እስላም እንደመሆኑ ለጓደኛዬ ብቻ ተብሎ የሚሰራ ምግብ አለ። የእስላም በዓል ሲሆን ደግሞ ቤታቸው እሄዳለሁ። እናትየው ለእኔ ብቻ ብለው የሰሩትን ምርጥ ምግብ እየደጋገምኩ እበላለሁ። ይህ ነው መቻቻል። ይህ ነው አንድነት። ይህ ነው የኢትዮጲያ ውበት። ክርስቲያኑ ሠርግ ቢደግስ ለእስላሙም ብሎ የተለየ ምግብ ያዘጋጃል። እስላሙም እንዲሁ። ልዩነታችን ውበታችን ነው! እዚህ ጋር እውነቷን መናገር አለብኝ። ስለ እስልምና እምነት ያለኝ አመለካከት የተዛባ ነበር። ለምን ቤተክርስቲያን ያቃጥላሉ፤ ለምን ሰው ይገድላሉ? ለምን? ምን ዓይነት ሃይማኖት ነው? የሚል የሕሊና ጥያቄ ነበረኝ። ይህ አመለካከቴ ግን በፍጹም ትልቅ ስህተት መሆኑ ገብቶኛል። ሃይማኖቱ ይህን አይልምና። እውነተኞቹ የእስልምና ሰዎች እምነታችን ይህ አይደለም እያሉ ኡ ኡ ብለው ሲጮሁ ዓይተናልና። ይህን ሁላችንም መረዳት ዓለብን። አክራሪ ነኝ የሚለ የኢትዮጲያ ጠላት ነውና በክርስቲያኑም ሆነ በእስላሙ ሕብረተሰብ መገለል አለበት።

ሁሉም ዜጋ እንዳይዘናጋ አለች ሴትዮዋ!


ከእስልምና ወደ ክርስትና የተቀየረ አንድ ሰው አውቃለሁ። ይህ ሰው መላ ዘመኑን  አክራሪ በሚባሉ ሰዎች እየተሰደደ ነው። የሃይማኖት ነጻነት የለም እንዴ? አንዱ እስላም ቢሆን እንዴት ብዬ መፎከር የለብኝም። የሰው ልጅ ክቡር ነውና ሃይማኖቴን እንደ ኮምፒዩተር ዳውንሎድ ላደርግበት አልችልም። ሲጀመር ፈጣሪ የሰጠውን ነጻነት የምነፍገው እኔ ማን ነኝ?  ፈጣሪ ከእውነተኛይቱ ሃይማኖት ውጪ ያሉትን ሰዎች ላጥፋ ቢል የእኛን እርዳታ አይፈልግምና!! ብዙ ሰዎች ያልተረዱት ይህንን ነው። ለሃይማኖት ተቆርቋሪ የሆኑ እየመሰላቸው ሃይማኖታቸውን ያስንቃሉ ያስገመግማሉም። ሃይማኖታቸው ስለ ፍቅር እያስተማራቸው እነሱ ግን ሕገ ወጥ ሕግ አስከባሪ ይሆናሉ!

  በየቤቱ ወረቀት እየተበተነ አክራሪ ሁን ማለቱንም የሃይማኖት አባቶች ተቃውመውታል። ይባስ ብሎ ከሃይማኖትህ ውጪ ጓደኛ አትያዝ ማለት የጀመሩም አልጠፉም። አንዳድ ጊዜ ደግሞ የፌስ ቡክ ጦርነትም አለ። በፌስ ቡክ የሚከራከሩ ሰዎች አይገርሟችሁም? አንዱ ይነሳና እኔ እምነቴ ክርስቲያን ነው ይልና ክርስቲያን ያላስተማረውን የሚተርክ አለ። ሌላውም እስላም ያላስተማረውን የሚተነትን አለ። አንዳንዶች ባለማስተዋልም ሆነ ሆን ብለው ሀገርን የሚያጠፋና የማይጠፋ እሳት  የሚያቀጣጥሉ አሉ። እነዚህ ሰዎች የኢትዮጲያና የሰላም ጠላቶች ናቸውና ሊገለሉ ይገባቸዋል። እነዚህ በሕሊና አናሳ የሆኑ ሰዎች ፍቅርን፣ ሰላምን፣ መቻቻልን፣ ሃይማኖትን ንቀዋልና ሊገለሉ ይገባቸዋል!!

ሰው ገድለህ ትድናለህ የሚል ሃይማኖት አልተፈጠረም። ይህን አይነቱ ሰው ሰይጣንም አብደሃል ሳይለው አይቀርም። ምክንያቱም ሰይጣን እንኳን እኔ የማምነውን ካላመንክ ብሎ ሰውን አልገደለምና!! ከሰይጣን እምነት የባሱ ናቸውና ሊገለሉ ይገባቸዋል!! በጎ ሕሊና ላለው ሰው ይህ እብደት እንጂ ጤንነት አይደለምና።

ሰላም ለኢትዮጲያ ይሁን!


Saturday, 30 June 2012

ጻድቃን ከሞቱ በኋላ እኛ የምንለምናቸውን ልመና እንዴት ይሰማሉ??

ጻድቃን ከሞቱ በኋላ እኛ የምንለምናቸውን ልመና እንዴት ይሰማሉ??

“Righteous From paradise  የቅዱሳን ምልጃ ከገነት”

አንድ ወንድሜ ጻድቃንን ከሞቱ በኋላ  ለምኑልን ጸልዩልን የምትሉት እኛ የምንሰራውን ስራ በምን ያውቃሉ? እንዴትስ ይሰሟችኋል? ብሎ ጠየቀኝ።  ወንድሜ የጠየቀኝን ጥያቄ እኔ ሳልሆን መፅሐፍ ቅዱስ መልሶለት ለሕሊናው ጥያቄ መልስ አግኝቶበታል። ለመሆኑ ጻድቃን ከሞቱ በኋላ እኛ የምንለምናቸውን ልመና እንዴት ይሰማሉ??

አብርሐም፦ በሉቃስ ወንጌል የተጻፈ አንድ ታሪክ አለ። ኃጥኡ ነዌ በሲኦል እያለ ከሩቅ አብርሐምን አየውና “አብርሐም አባት ሆይ እኔ በሲኦል እሣት እጅግ እየተሰቃየሁ ነውና እባክህን ምላሴን በቀዝቃዛ ውኃ እንዲያርስልኝ አላዛርን ላክልኝ አለው። አብርሐምም በኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል አለ ብሎ መለሰለት። ነዌም እንግዲያው በዓለም የሚኖሩ 5 ወንድሞች አሉኝና እባክህን አላዛርን ላከው አለ። አብርሐም የሚገርም ቃል ተናገረ “ለነሱ ሙሴና ነብያት አሏቸው” አለ። ይገርማል አብርሐም ሙሴን የት አየው? መቼ ተገናኘው? አብርሐምና ሙሴ በዓለም አልተገናኙም ነገር ግን አብርሐም በአካለ ነፍስ ሆኖ ሙሴ እንደመጣ፣ መጽሐፍትን እንደጻፈ፣ ተዓምራትን እንደሰራ፣ የኤርትራን ባሕር እንደከፈለ ያውቅ ነበር!! አዎ በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን በዓለም የሚከናወነውን ሁሉ ከእኛ በላይ ያውቃሉ። ስለእኛም ይለምናሉ። በሲኦል ያለው ነዌ ስለ ወንድሞቹ ከለመነ በገነት ያሉት ጻድቃንማ እንዴት ስለእኛ አይለምኑ?? አብርሐም “በአካለ ነፍስ” ሆኖ አላዛርና ነዌ በዓለም ምን እንደሰሩ ያውቅ ነበር። “አላዛር አንተ ችግርን ሁሉ ታገስክ; ነዌ አንተም ምቾትን ሁሉ ተቀበልክ” ያለው አብርሐም “በአካለ ነፍስ”  ሆኖ ምን እንደሰሩ ስለሚያውቅ ነው። አንዳንድ የዘመኑ ሰዎች ጻድቃን በአካለ ነፍስ ሆነው እንዴት ያውቃሉ ይላሉ አይደል? ወንጌሉ ይገለጥና ይነበባ። እውነትን ፍንትው አድርጎ በደንብ ያስረዳናል [ሉቃስ 16:19]

ነዌ አብርሐምን አነጋገረ። አብርሐምም መለሰለት። “አብርሐም መናገር መቻሉ ሕያው መሆኑን ያስረዳናል” ጌታችንም “እኔ የሕያዋን የአብርሐም የይሥሐቅ የያዕቆብ አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለሁም” ያለውም ለዚሁ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አለ “አሁን በመስታወት እንደሚያይ በድንግዝግዝ እናያለን ያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን” [1ኛ ቆሮ13:12]



አዎ ቅዱሳኑ ስለ ሀገራችን ስለ ዓለም ስለ ቤተክርስቲያን ስለ ራሳችን ለምኑልን ስንል ይሰማሉ፤ ቅ/ጳውሎስ እንዳለው ቅዱሳኑ ሁሉን ፊት ለፊት በግልጽ ያያሉና!!


በር እና ቁልፉ፦ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ላይ “እውነተኛ የበጎች በር እኔ ነኝ” ብሏል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ እንዳለ የበጎች በር ጌታችን ነው። በር ካለ ቁልፍ አለ ማለት ነው። የበሩ ቁልፍ የት ነው ያለው?

የበሩ ቁልፍማ በቅ/ጴጥሮስ እጅ ነው ያለው! ጴጥሮስ አንተ ዐለት ነህ። በዚህች ዐለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራታለሁ። የሲኦል ደጆች አይችላትም (የሲኦል ደጅ ጠባቂ አጋንንት አይችሏትም) “የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ” [ማቴ. 16:17]

የበሩን ቁልፍ ሳይዝ በሩን ለመክፈት የሚታገል ካለ መቼስ ምን እንላለን? ቁልፉን ሳይዙ በሩን ለመክፈት የሚታገሉ ሰዎችኮ በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ ታሪካቸው ተተርኳል! ትዝ አይላችሁም የሰዶምና ገሞራ ሰዎች የሎጥን ቤት ሲደበድቡ? የበሩ ቁልፍ ያለው ግን በሎጥ እጅ ነበር። የበሩ ቁልፍ ያለው በቅ/ጴጥሮስ እግር በተተኩት ምርጥ እቃዎች በቅዱሳኑ ዘንድ ነው። የበራችንን ቁልፍ ስናይ ፣ በራችንን ስንከፍት ይህ ትዝ ሊለን ይገባል። የበሩ ቁልፍ ያለው በአካለ ነፍስና በአጸደ ነፍስ ባሉ በቅዱሳኑ እጅ ነውና። ዐለት የተባለውን የሐዋርያት አለቃን ስለ እምነታችን ፅናት እስኪ እንለምነው “ከሞቴ በኋላ ስለ እምነታችሁ ፅናት ስለእናንተ እተጋለሁ” [2ኛ ጴጥሮስ 1:15]

ይህን በተመለከተ እስኪ ቤተክርስቲያናችን በቅዳሴ የምታዜመውን አብረን እንይ።“ተውህቦ መራሁት ለአቡነ ጴጥሮስ” ወድንግልና ለዮሐንስ ወመልዕክተ ለአቡነ ጳውሎስ እስመ ውእቱ ብርኃና ለቤተክርስቲያን።

ትርጉም፦ ለአባታችን ለጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ፣ ለዮሐንስ ድንግልና ለቅ/ጳውሎስም መልእክት ተሰጠው። [ማቴ. 16:17]

    
 ሙሴ ፦ከሞተ ዘመናት ያለፉት ሙሴ ከኤልያስ ጋር በደብረ ታቦር በተገለጸ ጊዜ ኤልያስና ሙሴ ከጌታ ጋር ይነጋገሩ ነበር። ስለ ኢየሩሳሌምም ትንቢት ተናገሩ እንዲል ሉቃስ [9:30] “ሙሴ መናገር መቻሉና ትንቢት መተንበዩ ሕያው መሆኑን ያስረዳናል”

 ደመ ሰማዕታት [Martyrdom]፦ ሰማዕታት ማለት ሰማ መሰከረ ሰማዕት ምስክር ማለት ነው። ደመ ሰማዕታት በታላቅ ድምጽ እየጮሁ “ደማችንን በከንቱ ያፈሰሱትን የማትበቀለው እስከመቼ ድረስ ነው?” አሉ [ራዕ 6:9] “በታላቅ ድምጽ መጮህ መቻላቸው” ሕያዋን መሆናቸውን ያስረዳናል። ደማችንን በከንቱ ያፈሰሱትን የማትበቀለው እስከመቼ ድረስ ነው? ማለታቸው ደማቸውን በከንቱ ያፈሰሱት እነ ዲዮቅልጥያኖስና ሌሎችም ገና እንዳልተቀጡ ስለሚያውቁ ነው። ጌታም ሌሎች ሰማዕታት ስላሉ እንዲታገሱ ነግሯቸው የንጽህና ምልክት የሆነውን ነጭ ልብስ ሰጣቸው። “ሰማዕታት ደማቸውን በከንቱ ስላፈሰሱት ፍርድን ሲጠይቁ ስለ እኛ ደግሞ ይለምናሉ”


“ዙሪያ ጥምጥም”

እዚህ ጋ ከላይ እንዳየነው ወንድሜ የጠየቀው ጥያቄ ትዝ አለኝ። ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ እኛ የምንሰራውን ስራ በምን ያውቃሉ? ብሎ ነበር የጠየቀኝ። የአብርሐምና የነዌ ታሪክ መልሶለታል [ሉቃስ 16:19] ወዳጄ ጥያቄውን እንዲህ እያለ ቀጠለ። እኛ ራሳችን እግዚአብሔርን በቀጥታ መለመን ስንችል ለምን በተዘዋዋሪ ዙሪያ ጥምጥም መጓዝ አስፈለገ? ብሎ ጠየቀኝ።

ጌታችን ለምጻሙን ሰው ከፈወሰው በኋላ ወደ ካህን ሔደህ ራስህን አሳይ ለምን አለው? እሱ ራሱ ካየው አይበቃም ነበር? እግዚአብሔር ቅ/ገብርኤልን ወደ እመቤታችን ለምን ላከው? እሱ ራሱ ለምን በቀጥታ አላነጋገራትም ብለን ልንጠይቅ እንችላለን? ብዬ ጠየኩት። ወጃጄ ነገሩ ሁሉ እየገባው መጣ።

ዳዊት፦ ንጉሥ ሰናክሬም ንጉሥ ሕዝቅያስን እጅግ ያስጨንቀው ነበር። በአንድ ወቅት ሰናክሬም የትዕቢት ደብዳቤ ጽፎ በንጉሥ ማሕተም አትሞ ሥጋህን ቆራርጬ ለአሞራ አጥንትህን ፈጭቼ ለነፋስ እሰጠዋለሁ እያለ ለሕዝቅያስ ላከበት። ንጉሥ ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ይዞ ወደ ቤተክርስቲያን ገሠገሠ። ወዲያው ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። አቤቱ ይህን ሁሉ ተመልከት፣ አቤቱ የጭንቅ ደብዳቤውን አንተ እይ እያለ ለመነ። እግዚአብሔርም የንጉሡን ጩኸት ሰማ። እስኪ የሚያስጨንቀንን ነገር ከቤቱ ገብተን እንደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤ በፊቱ እንዘርጋው። የከበደው ቀሎ፣ የጨለመው በርቶ አስጨናቂው ለሊት ሲነጋልን በዓይናችን አይተናልና!! በቤቱ እጁን ዘርግቶ ማን ባዶውን ይመለሳል? ጌታችን ሆይ በቃላት ስለማይነገረው ስጦታህ ሁሉ እናመሰግንሃለን።

ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ከዘረጋ በኋላ መልክተኞችን ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ። ነቢዩ ኢሳይያስ የነገሥታት አማካሪ ነበር። ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስንና ንጉሥ ዖዝያንን ያማክር ነበር። ዛሬ ቅዱሳንን የሚያማክር ከየት ይገኛል? ንጉሥ ሕዝቅያስ የነቢዩ ኢሳይያስን መልስ በተስፋ እየተጠባበቀ ነበር። እግዚአብሔርም መልሱን በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ላከለት። ልበ አምላክ ዳዊት ከሞተ ከብዙ ዘመን በኋላ “ስለ ዳዊት ስል ኢየሩሳሌምን ከጥፋት እጋርዳታለሁ” አለ [2ኛ. ነገ19:34]

ስለ ዳዊት ስል ኢየሩሳሌምን እምራታለሁ እንዳለ ስለ አቡነ ተክለሐይማኖት ፣ ስለ አቡነ አረጋዊ ፣ ስለ ቅ/ጊዮርጊስ ስትል ሀገራችንን ማር ብንል ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? የዘመኑ ሰዎች ለምን ስለ ዳዊት አልክ ብለው ፈጣሪንም ተሳስተሃል ይሉ ይሆን?

ንጉሥ ሕዝቅያስና ንጉሥ ዖዝያን ነቢዩ ኢሳይያስን እንደሚያማክሩ አይተን ነበር። ነቢዩ ኤልሳዕም እንዲሁ የእስራኤል ንጉስን ያማክር ነበር። ትዝ ካላችሁ የሶርያው ንጉሥ እስራኤልን ለመውረር ብዙ ሲሞክር ነቢዩ ኤልሳዕ በእስራኤል ሆኖ በሶርያ ቤተመንግሥት ውስጥ የሚመከረውን እያንዳንዷን ምክር ያውቅ ነበርና ሚሥጢሩን ለእስራኤል ንጉሥ ያቀብል ነበር። ኤልሳዕ ልክ እኛ በ CCTV እንደምናየው ሁሉን ያይ ነበር። የሶርያው ንጉሥ ግራ ገባውና ተጨነቀ። በመጨረሻም ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብሎ ወደ እስራኤል ገሠገሠ። የተዋጋው ግን ንጉሡን ወይንም የንጉሡን ሠራዊት ሳይሆን ኤልሳዕን ነበር። ኤልሳዕ ከጠፋ እስራኤል ጠፋች ማለት ነውና። ይህኮ በኛ ቤትም እየተሰራበት ነው። ቅዱሳኑ ከጠፉ ኢትዮጲያን ማጥፋት ቀላል ነው የሚሉ ብዙ የዘመናችን ሰዎች አሉና። እስኪ ልብ በሉ።

ፕሮቴስታንቱ ቢነሳ በኛ
ካቶሊኩ ቢነሳ በኛ  
ተሐድሶ ቢነሳ በኛ
እስላሙ ቢነሳ በኛ
ፖለቲከኛው ቢነሳ በኛ

አንዱ አንዱን ላጥፋ አይልም። ከውጪውም ሆነ ከሀገር ውስጥ ሁሉም ዓይኑ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ላይ ነው።

ቅድስቲቱን ከተማ ሃገራችንን ቤተክርስቲያናችንን ከጠላት እንዲጠብቅልን በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉ ጻድቃን ሰማዕታትን እንለምን። በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉ የቅዱሳኑ ምልጃ ከእኛና ከሃገራችን “ከኢትዮጲያና - ኤርትራ” አይለይ አሜን! /7-2-2010/


በቅዱሳን ላይ በትዕቢት የሚናገር አንደበት ዲዳ ይሁን! [መዝሙረ ዳዊት 30:18]



ነብያትን ይስሙ [ሉቃስ 16:19]

ነዌ ባለጠጋው ሃብቱን አከማችቶ
እለት ከእለት ባለም ተመቻችቶ
ይኖር ነበር አምላክን ረስቶ
ደሃው አላዛርም በደጁ ተኝቶ
አንድ ቀን ጌታዬ ያዝንኛል ብሎ
ቀን ይቆጥር ነበር በቁስል ተወርሶ
ቁራሽ ፍርፋሪን አገኛለሁ ብሎ።

ያ ባለጠጋ በልቡ ሳይራራ
በንቀት አየው ሲወጣ ሲገባ
ቀኑ ደረሰና ያ ደሃ ተጠራ
በአብርሃም እቅፍ መልካም ቦታ አገኘ
ነዌ ባለጠጋ ሃብቱ መች ጠቀመው
ቀኑ ሲደርስ እርሱም ሞት አገኘው
መልካም ስላልነበር በምድር የሰራው
በሲኦል ክፉ ሆኖ አገኘው
በስቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን አየው
አላዛርንም በእቅፉ ቢያየው
የጣቱን ጫፍ በውሃ ውስጥ ነክሮ
ምላሴን ቢያርሰው
አብርሃም አባት ሆይ አላዛርን እባክህን ላከው
ብሎ አላዛርን ሻተ በምድር ለናቀው።
አብርሃም መልሶ
አንተ በምድር ሳለህ መልካምን ተቀበልክ
አላዛርም ደግሞ እንዲሁ ክፉውን
ሁሉን ተቀብሏል አሁን ግን ይፅናናል
በኛና በናንተ ታላቅ ገደል ሆኗል።
ነዌ ይህን ግዜ 5 ወንድም አሉኝ
እነርሱም ደግሞ እንደኔ እንዳይሆኑ
አላዛርን ላከው ሁሉን ይንገርልኝ፤
ሙሴና ነብያት ለነርሱ አሏቸው
እነርሱንም ይስሙ መንገድ ይሁኗቸው
ሰምተው ቢፈፅሙት ህይወት ይሁናቸው
ብሎ መለሰለት እኛ እንድንሰማቸው።


/ተክለ መድህን/ 

በቅዱሳን ላይ በትዕቢት የሚናገር አንደበት ዲዳ ይሁን! [መዝሙረ ዳዊት 30:18]




Saturday, 23 June 2012

“ይድረስ ለኢትዮጲያ ሀገሬ // የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች”




       
      “ልጅ ለእናትዋ ምጥ አስተማረቻት” ቢሉ ማን ያምናል? ሕጻናትን ሳይንከባከቡ ፍሬውን መጠበቅም እንዲሁ ነው። “አለሽ መስሎሻል ተበልጠሽ አልቀሻል” አለች እምዬ ኢትዮጲያ። ፊት ለፊቴ አንድ ትንሽ ብላቴና ኳሷን እንደ ጉድ እያንከባለለ ትንፋሹ ቁርጥ እስክትል ድረስ እንደ ጉድ ይሮጥ ነበር። “የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች አሉ አባባ ተስፋዬ! የዛሬ አበባዎች ናቸው ለነገ ፍሬ የሚሆኑት” አለኝ ሕሊናዬ። ዛሬ ሕጻናት አበቦችን በስስት ሳንንከባከብ ፣ የተስፋ ውኃ ሳናጠጣ ፣ በስጦታ ሳንኮተኩት፣ ፀሐይ ጊዜያችንን ሳንሰጣቸው ምን ዓይነት ፍሬ ይሆን የምንጠብቀው? አለኝ ሕሊናዬ ደገመና። “አሁን ገና በራልኝ አለች እብድ ቤቷን አቃጥላ!”


   ከልጅነት ጓደኞቼ ጋር ኳስ ለመጫወት አንድ የሚገርም ኮድ አለን። በለሊት ቀድሞ የነቃ ለዘመናት ዝናብና ፀሐይ ያደከመው ቆርቆሮ ላይ ድንጋይ ይወረውራል። ያኔ ሆዳቸውን የባሳቸው አያሌ የሰፈራችን ቆርቆሮዎች እዬዬ ብለው ብሶታቸውን ያሰማሉ። ድንጋይ ውርወራው የኛ የብልጦቹ “ኮድ” ነው። ለቆርቆሮዎቹ ያዘነ ደግሞ ድንጋይ መወርወር ትቶ ያፏጫል። ልክ ያቺ ድንጋይ ቋ ቋ ቋ ስትል አልያም ፉጨቱ ሲሰማ ኮድ ነውና ሁላችንም ብንን እንላለን።         

     እንደዚህ የኳስ ፍቅር ያለን ልጆች በደንብ ብንያዝ ኖሮ ዛሬ ከመካከላችን አንዱ ለሀገር የሚበቃ ኮኮብ በሆነ ነበር። “ብረትን መቀጥቀጥ እንደጋለ ነው” ይላል የአንጥረኞች መፈክር። በጋለው የልጅነት ፍላጎታችን ትንሽ ድጋፍ ቢገኝ የት በተደረሰ ነበር። ባለሁበት በለንደን ከተማ ለሕጻናቱ ያላቸው የጋለ ድጋፍ ይደንቀኛል። ገና በማህፀን እያሉ ለአንድ ክለብ ይፈርማሉ።  እስከ ሰባት ዓመት ሲሞላቸው አሰልጣኝ ተቀጥሮ እንደ ጉድ ውድድር ይደረጋል። እንደ ጉድ ሕዝቡ ይደግፋቸዋል። እንደ ጉድ ሀገራቸውን ያስጠራሉ። እንደ ጉድ ኮኮቦች ይሆኑና እንደ ጉድ ያበራሉ!

         “ልጅህንም አባትህንም ስታጎርስ ለአንዱ ታበድራለህ ለሌላው ትከፍላለህ” እንዲሉ እስኪ ለልጆቻችን ሞራል እናበድራቸው። ለሕጻናቱ ትኩረት መስጠት በኛ ሀገር እንደ ሕልም ነው የሚታየው። የኛ ነገር “ሞት ሲደርስ ቄስ ጦር ሲደርስ ፈረስ” ሆነብንኮ ሰዎች! የልጆች አስተዳደግ ፣ ፍላጎት፣ ዓላማ ወዘተ ተረፈዎች ለኛ ትርፍ ነገር ናቸው። በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ ሕይወት አንዳች ድጋፍ አናደርግላቸውም። “በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ” የሚለው ቃል ተረስቶ “በአባቶችሽ ፋንታ ልጅ የሚወልድልሽ ጠፋ” እንዳይሆንብን ያሰጋል። የሰለጠነው ዓለም ግን ልቡና ዓይኑ በታዳጊዎች ላይ ነው ያለው። ሩኒ ፣  ጄራርድ ፣ መሲ እና ሮናልዶ ከሰማይ የወረዱ አይደሉም። እነዚህ ፍሬዎች ሁሉ በዓላማቸው ላይ ከጎናቸው በቆሙ ወላጆችና በሕብረተሰቡ ታቅፈው ያፈሩ የወይን አትክልቶች ናቸው። ይህ ሁሉ እኛ ቤት ቢዘገይም እስከ መጨረሻው ግን አይቀርም። “ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል” አለች ሴትዮዋ። እስኪ ሁላችንም ሕጻናቱን በፍላጎታቸው እንደግፋቸው። ሴቷ ስትሮጥ ዘላል ወንዱ ኳስ ሲያንከባልል ዱርዬ ከማለት እስኪ የአስተሳሰብ ለውጥ እናምጣና እናበረታታቸው። ያኔማ በርቱ ብለን ብናሞግሳቸው አልፎም ስጦታ ብንሰጣቸው በሞራልና በራስ መተማመን ያድጋሉ። በሞራልና በድፍረት ያደገችው ሴቷ ብትሮጥ መሰረት ደፋር ትሆናለች!


      “ቁንጫ መሔድ ሳትማር መዝለል ተምራለች” እንዲሉ ኳስ ማንከባለል ሳናስተምር በኃይለኛው ለግቶ ግሩም ግብ እንዲያገባ እንጮኻለን። ሌላው ቀርቶ ደጋውን ሲወጡ ቆላውን ሲወርዱ ሲሮጡ ሲደክሙ ላባችሁን መተኪያ ብለን ውኃ እንኳን ሳንገዛላቸው ማራቶኑን ፣ 10ሺውን ፣ 5ሺውን እንዴት በኬንያና በቻይና ተበላን ብለን እዬዬ እያልን እንጮኻለን። “ባትዋጋ እንኳን ተሰለፍ” ይላል የወታደሮች መፈክር። እኛ ባንዋጋ እንኳን በሞራል እንሰለፍ እንጂ ጎበዝ!

አልሰማችሁም እንዴ? አልሰማን ግባ በለው አሉ። (ሉሲዎቹ) የኢትዮጲያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለ8ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አለፉ! ሴቶቻችን ታንዛኒያ ዳሬሰላም ገሥግሠው ውድ ልጃችን “ብሩክታይት” ጎሉን እንደ ጉድ አግብታ በድል ተመልሰዋል!! ይህ ውጤት ከየት መጣ? ልብ በሉ አንዳች የሴቶች ውድድር በሌለበት ሀገር ነው ይህን ውጤት ያመጡት። ዋልያዎቹ (የኢትዮጲያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን) ቤኒን ገሥግሰው “አዳነ ግርማ” ጎሉን አግብቶ 1 ለ 1 በመውጣት ተጋጣሚውን ጥሎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። ከ15 ቀን በኋላ ዕጣ ይወጣና ከአንድ ቡድን ጋር ተመድበን በደርሶ መልስ ካሸነፍን ከ35 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ እናልፋለን ማለት ነው! ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ምድባችንን እየመራን ነው! ይህ ግሩም ድንቅ ውጤት ነው። ሌሎቹ በአውሮፓ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱ ሲሆን የኛዎቹ ግን ሙሉ በሙሉ በሀገርቤት የሚጫወቱ ናቸውና።
ቅ/ጴጥሮስ ካስተማረ በኋላ ሕዝቡ “ምን እናድርግ?” አሉ። እስኪ እኛም “ምን እናድርግ?” እንበል። ለጀግኖቹ ደማቅ አቀባበል ማድረግ ፣ የወንዶቹንም የሴቶቹንም ቡድን በአንድላይ አድርጎ ልዩ ብሔራዊ ቀን በማወጅ ማበረታታት ፣ መሸለም ፣ ማድነቅ ፣ ማወደስ ብሎም ቀጣዩ ዋና ስራ ምን መሆን እንዳለበት መወያየት ከኛ ይጠበቃል። የሴት ብሔራዊ ቡድናችን የተከበሩት አሰልጣኝ 15 ሺህ ፣ ምክትል አሰልጣኞች 10 ሺህ ተጫዎቾቹ ደግሞ እያንዳንዳቸው 15 ሺህ ብር ተሸልመዋል።

“እርሻው ሲያምር ዳቦው ያምር” አለች ዳቦ ጋጋሪዋ እውነቷን እኮ ነው። ልጆችን ስንኮተኩታቸው የሚገመጡ ዳቦ ይሆናሉ። “የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ” እንዲል እኛም ታዳጊዎችን ብንኮተኩት ያልበሰለው በስሎ የበሰለው አምሮ ቢታይ የሚያጓጓ ቢበላ የሚያረካ ፍሬ ይሆናሉ። የዛሬ አበባዎቹ የነገን ፍሬ ያፈራሉ! “የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች አሉ አባባ ተስፋዬ” ይህ ሁሉንም ሕብረተሰብ ይመለከታል። እስኪ ቃል እንግባ። እስኪ ሁላችንም በቤታችን ያሉትን ሕጻናት ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ቀርበን ለአበባዎቹ የሚያስፈልጉትን ሁሉ እናድርግላቸው! እስኪ በአካባቢያችን ያሉትን ሕጻናት ኮትኩተን ኢትዮጲያን የሚያኮሩ ከዋክብት እናድርጋቸው! “ኮከብ እም ኮከብ ይኄይል በክብሩ” እንዲል አንዱ ኮከብ ከሌላው ይበልጣንና እስኪ ለጎበዞቹ ስጦታ እየሰጠን እናበርታቸው። እነሱን አይተው ብዙ ከዋክብት ይወጣሉና።
እዚህ ጋር እውነታኛ ታሪኬን ላውጋችሁ። ኳስ በጣም ስለምወድ በየሳምንቱ ቅዳሜ በጠዋት ለመነሳት እንቅልፍ አይወስደኝም ነበር። “አምራለሁ ብላ ተኩላ ዓይኗን አጠፋችው ቸኩላ” እንዲል ለሊቱ ይነጋልኝ ዘንድ እቸኩል ነበር። ታዲያ አንድ ቀን ሳፈጥ አመሸሁና በለሊት ተነሳሁ። ብጠብቅ ኮዱ የለም። ድንጋይ አይወረወርም። ብጠብቅ ከወፍ በስተቀር የሚያፏጭ የለም። ጥለውኝ ሔዱ ማለት ነው ብዬ ተናደድኩና ከምሽቱ 9 ሰአት ላይ በሩን ከፍቼ ወደ ኳስ ሜዳ ገሠገሥኩ። ሜዳ ላይ ደረስኩ። አንዳች ፍጥረት የለም። ደነገጥኩ። በልቤ “ሹሩባ ልትሰራ ሔዳ ጸጉሯን ተላጭታ መጣች” የሚለው ተረት ተፈጸመብኝ ማለት ነው እያልኩኝ በመጣሁበት እግሬ እየሮጥኩ ቤቴ ተመልሼ አንኳኳሁ። የሚከፍትልኝ ጠፋ። ከወንድምና እህቶቼ ጋር በተለየ ክፍል ነው የምናድረውና አባ ወራና እማ ወራ ይህን ኹሉ ጉድ አያውቁም። በሩን ብደበድብ ሁሉም እያንኮራፉ ይገለባበጣሉ እንጂ የሚከፍትልኝ ጠፋ። ተስፋ ቆርጬ በሩን ደገፍ ብዬ እንደቆመኩ እንቅልፍ ሸለብ አደረገኝ። ወዲያው ግን “ሁለተኛ ጥፋት ቆሞ ማንቀላፋት” ብዬ መላ መፈላለግ ጀመርኩ። ዞር ስል አንደኛው ቤት ወለል ብሎልኛል። ቁልፉ የት እንዳለ ስለማውቅ ከፈትኩና ገባሁ። ማዕድ ቤት ነበር። ዶሮዎቹ እንተኛበት እንጂ እያሉ በልሳነ አእዋፍ እንደ ጉድ ጮሁብኝ። ምን ላድርግ ብዬ ጸምሩን ዘረጋግቼ ፣ ድንጋዩን ተንተርሼ ፣ ዶሮዎቹን ታቅፌ ማንኮራፋት ጀመርኩ። “ልፋ ያለው በሕልሙ ሸክም ይሸከማል” እንዲሉ የዛች ለሊት ሕልሜ ለሕልም ፈቺውም ሕልም ሆኖበት ነበር። ሕልሜን ብነግራችሁ ደስ ባለኝ ነበር። ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል እንዲሉ ይለፈኝ። ያቺ ለሊት ግን እንደ ጉድ  አስተምራኛለች። “ሌሊት የምክር እናት” ትል ነበር እናቴ።

ወቅቱ የዓለም ዋንጫ የሚካሔድበት ጊዜ ነበር። ያኔ በቴሌቭዥን ያየነውን ኮከብ እኛም ለመሆን ወዲያው ኳስ ለማንከባለል ወንዝ እንወርዳለን። እናንተዬዋ አይጣል ነውኮ! አሁን ኳስ ለመጫወት ወንዝ መውረድ ምን ይሉታል? እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች አሉ! በሰፈራችን አንዳች የመጫወቻ ሜዳ የለምና ወንዝ መውረድ አለብን። ሰፈር ብንጫወት ሰምተነው የማናውቀው የእርግማን ዓይነት ይወርድብናልና ሜዳ ፍለጋ ወንዝ መሻገር አለብን። ወንዙ ደግሞ ድልድይ የለውም። ረዥሙ ወንዝ በረዥም እንጨቶች ድልድይ ተሰርቶላቸዋል። እኛም ያቺን ኳስ ክብልል ለማድረግ ይህን ወንዝ ማቋረጥ ግድ ይለናል። ያ- ለዘመናት ጡረታ ልውጣ እያለ በልሳነ ዕጽዋት እዬዬ ያለው እንጨት ሲጢጢጢጢ ቋቋቋቋቋ ሲል የልጅነት ልባችንም አብሮ ፈራ ተባ ይላል። ቀስ ብለን ማገሩን ይዘን ተራ በተራ ለማለፍ ስንሞክር ከፍ ዝቅ እያለ ኪሏችንን ይቀንሰዋል። አንድ ቀን ያቺ እንጨት ብትቀነጠስ ስንት ሕጻናት ይሆኑ የሚያልቁት?

የሀገር ያለህ ፣ የሀገር ያለህ ፣ የሀገር ያለህ! ይድረስ ለኢትዮጲያ ሀገሬ። ይህ ሁሉንም ሕብረተሰብ ይመለከታል!!
ጆን ደብልዩ ሎረንስ የተባለ ፀሐፊ በመጽሐፉ እንዲህ ብሏል፡-
ልጅ እየተወቀሰ ካደገ ማውገዝን ይማራል፡፡
ልጅ በጥላቻ አካባቢ ካደገ መደባደብን ይማራል፡፡
ልጅ እየተፌዘበት ካደገ ዓይነ አፋርነትን ይማራል፡፡
ልጅ በሐፍረት ካደገ ጥፋተኝነትን ይማራል፡፡
ልጅ በመቻቻል ካደገ ትዕግሥተኝነትን ይማራል፡፡
ልጅ በመበረታታት ካደገ በራስ መተማመንን ይማራል፡፡
ልጅ በመሞገስ ካደገ ማድነቅን ይማራል፡፡
ልጅ በአግባብ ካደገ ፍትሕን ይማራል፡፡
ልጅ ዋስትና ባለው ኑሮ ካደገ ሰውን ማመን ይማራል፡፡
ልጅ በተቀባይነትና በወዳጅነት ካደገ በአጠቃላይ ዓለም ፍቅርን ማግኘት ይማራል፡፡

ከተበላሸ ወተት ጥሩ እርጎ አይገኝምና ሕፃናትን ሀገር ወዳድ አድርገን እናሳድጋቸው!

****-//-****

“የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች አሉ አባባ ተስፋዬ” ይህ ሁሉንም ሕብረተሰብ ይመለከታል!! እስኪ አስተያየታችሁን በነጻ ለግሱ።
እስኪ በአካባቢያችን ያሉትን ሕጻናት ኮትኩተን ኢትዮጲያን የሚያኮሩ ከዋክብት እናድርጋቸው!! እስኪ ሕጻናቱን ለመኮትኮት በተከበረችው በሀገራችን በኢትዮጲያ ሥም ቃል እንግባ!!

Tuesday, 19 June 2012

"እንኳን ለቅ/ሚካኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ"


ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ አሪፍ ታሪክ ልንገራችኹ!

የተከበሩት አባት እንዲህ ብለው ጠየቁ፤

መላእክት እንደ ሰው የሚታጠፍ እና የሚዘረጋ እግረ ሥጋ የላቸውም፤ ታዲያ መላኩ ቅ/ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት “የምቆመው” ገብርኤል ነኝ ሲል ምን ማለቱ ነው?? ሉቃስ [1: 19]


ይህች ጥያቄ ያለንበትን ክፍል ዝም አስባለች። ኹላችንም በልባችን ለምን ይኾን? እያልን መጠየቅ ጀመርን።
  
የተከበሩት አባት መልሱን እንዲኽ እያሉ አስረዱን፤ በእርግጥ ግሩም ጥያቄ ነው፤ መላእክት መንፈስ ናቸውና እግረ ሥጋ የላቸውም፤ አይቀመጡም አይነሱም አይቆሙምም! ሊቀ መላእክት ቅ/ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት “የምቆመው” ገብርኤል ነኝ ማለቱ ምህረትን ጠያቂ አማላጅ ነኝ ሲል ነው አሉን።

በክፍላችን ውስጥ የነበሩ የሌላ እምነት ተከታዮች ነበሩና  “አሁን ማን ይሙት ይኼ ከአማላጅነት ጋር በምን ይገናኛል?” አሉ በልባቸው። ይኽን ሐሳባቸውን የተከበሩት አባት ስለገባቸው ፍግግ አሉ። እንዴት ማለት ጥሩ ነውና እንዴት? እንበል አሉን። እንዴት አልን በልባችን። እንዲህ ብለው ቀጠሉ፦



ይህን እንድንረዳ ልበ አምላክ ዳዊት የዘመረውን አብረን እንይ፤  የተመረጠው ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት “ባይቆም” ኖሮ ሕዝበ እሥራኤላዊያን በቅጽበት በጠፉ ነበር ይለናል መዝ. [105:23] ሙሴ ቀጥ ብሎ ስለ ቆመ አይደለም እስራኤላዊያን ምሕረት ያገኙት፤ ሕዝቡን ከምታጠፋ ሥሜን ከሕይወት መጽሐፍ ላይ ደምስስ!!! እያለ የለመነው ልመና ነው እስራኤላዊያንን ያስማራቸው ዘፀአት [32:32]

ስለዚህም “መቆም” ማለት ቀጥ ብሎ መቆም ብቻ ሳይሆን  መለመን ፣ ማማለድ እንደሆነ ባህረ ጥበብ የሆነች ቤተክርስቲያናችን እንዲህ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያበሰለች ትመግበናለች!

የተከበሩት አባት በግርማ ሞገሳቸው ጎርደድ እያሉ “እስኪ በአንድምት እንምጣ” አሉ። አንድም ስለ ሕዝቡ “የሚቆመው” ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል ዳንኤል [12:1] ቅ/ሚካኤል እግረ ሥጋ የለውም፤ ስለ እኛ ምህረትን ይለምናል እንጂ። አንድም መላዕክትም በእግዚአብሔር ፊት “ለመቆም” መጡ፤ ሰይጣንም በመካከላቸው ነበር። ኢዮብ [1:6] ሰይጣን ከሳሽ ስለሆነ ቆመ አልተባለም መላዕክቱም ቆሙ የተባሉት ቀጥ ብለው ቆሙ ለማለት አይደለም፤ ሊለምኑ መጡ ለማለት ነው እንጂ። አንድም እግርህ በድንጋይ እንዳይመታ “በእጆቻቸው ያነሱሃል” ይላል፤ መዝ. [90: 11] መላዕክት እንደ ሰው እጅ የላቸውም መንፈስ ናቸውና፤ ነገር ግን ሎጥን ከሰዶም እሣት እጁን ይዘው እንደወጡ ፈጥነው ደራሽ መሆናቸውን ሲያስረዳን ነው።



አንድም መላዕክት እንደ ሰው የሚያዩበት ዓይነ ሥጋ የላቸውም፤ መንፈስ ናቸውና፤ በወንጌል ግን ጌታችን እንዲህ አለ፦ ከታናናሾቻችሁ ማንንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ ጠባቂ መላእክቶቻቸው ዘወትር የአባቴን ፊት “ያያሉና” ማቴ. [18:10] “ያያሉና” ማለት መላዕክት በዓይናቸው እግዚአብሔርን ያያሉ ለማለት አይደለም; መላዕክት ዓይነ ሥጋ የላቸውም ተብሏልና፤ “ያያሉ ማለት ይለምናሉ” ለማለት ነው፤ አንድም እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም ይለናል፤ 1ኛዮሐ.[4: 12]  “ያያሉ” ማለት ይለምናሉ ማለት እንደሆነ አየህን?

አንድም “ጠባቂ መላእክቶቻቸው” የሚለውን ስንመለከት “ጠባቂ” የሚለው ቃል መላዕክት ጠባቂ እንደሆኑ አይነግረንምን? አንድም “መላእክቶቻቸው” የሚለው ቃል እያንዳንዱ ሰው ፪ ዑቃቢ መልአክ /ጠባቂ መልአክ/ እንዳሉት አይነግርህምን? ፩ዱ በቀን ሲጠብቅህ ፩ዱ በለሊት እንደሚጠብቅህ አታውቅምን? አሉ የተከበሩት አባት በማይጠገብ ፈገግታቸው እያዩን። ይህችንም ማስታወሻ ሰጡን፦ “የጥቅስ ጥናት ዘዴ”

የቅ/ሚካኤል በዓል የሚውለው በ 12 ነው ስለዚህ ዳንኤል [12:1]
የቅ/ገብርኤል በዓል የሚውለው በ 19 ነው ስለዚህ ሉቃስ [1: 19]


የተከበሩት አባት ውድ ልጆቼ ሆይ ይህን ሁሉ ባሕረ ጥበብ ቤተክርስቲያን ታስተምረናለችና “ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!” አሉን። ይህን ሲሉ ለመጻፍ የማይቻል አንዳች የመንፈስ ደስታ ይታይባቸው ነበር።

“ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!”  አሉ በድጋሚ፤ እኛም “ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!” አልን በልባችን።




Saturday, 16 June 2012

የሰማዩ ቤተ መንግሥት!

በሕንድ የማላባር ግዛት ይኖር የነበረ ንጉሥ ጎንዶፓረስ በኢየሩሳሌም ይኖር ስለነበረው የሰለሞን ቤተ መንግሥት ዝና እየሰማ እርሱም በግዛቱ ያን ዓይነት ቤተ መንግሥት መሥስራት ይፈልግ ነበርና ነጋዴዎች በየሀገሩ ሲጓዙ የታወቀ ግንበኛ እንዲያመጡለት አዟቸው ነበር። ነጋዴዎቹም በሀገሩ ሕንፃ በማነፅ ኑሮውን ይገፋ የነበረውን ሐዋርያው ቶማስን ለንጉሡ አመጡለት። ንጉሡ ቶማስን ከከተማው አጠገብ ወደሚገኘው ጫካ ወሰደውና ቤተ መንግሥቱ የሚሰራበትን ሰፊ መሬት አሳየው።     


ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሥ ጎንዶፓረስ ለቤተ መንግሥቱ ማሰሪያ ይኾን ዘንድ “ለሠራተኛ መቅጠሪያ ፣ ለድንጋይና ዕብነ በረድ ፣ ለብርና ለወርቅ ፣ ለብረትና እንጨት መግዣ” እያለ ያለ የሌለውን ገንዘብ ለቶማስ ይልክለት ጀመር። ቅ/ቶማስ ገንዘቡን ሲያገኝ የተጓዘው ወደ ገብያ ወይም ሠራተኛ ፍለጋ ሳይኾን ወደ ድኾች መንደር ነው። በዚያም ለተራቡ ምግብ ለታረዙ ልብስ በየቦታው ለወደቁ መጠለያ እየገዛ ማደል ጀመረ። 

ንጉሥ ጎንዶፓረስ “አይደርስ የለ ደርሶ ባየኹት” እያለ ቤተመንግሥቱን ለማየት ጉዞውን በጉጉት ጀመረ። ቤተ መንግሥቱ ይሰራበታል በተባለበት ቦታ ላይ ሲደርስ ንጉሡ ክው አለ። ጫካው አልተነካም። ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ቀርቶ የወደቀ ድንጋይ የለም። ንጉሡ የልቡ ምት ጨመረ። በዚያ በኩል የሚያልፍ አንድ መንገደኛ ጠራና “ቶማስ የት አለ”? ብሎ አፈጠጠበት። 

ቶማስ የተራቡትን እያበላ ፣ የተጠሙትን እያጠጣ ፣ የታረዙትን እያለበሰ በድኾች መንደር ይገኛል ብሎ መንገደኛው መለሰ።

“እርሱ ባልከፋ ታዲያ የሰራልኝ ቤተ መንግሥት የት አለ”? ንጉሡ መንገደኛው ላይ እንዳፈጠጠ ጠየቀው።

“በድንጋይ የተሰራ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ ጌታዬ፤ ነገር ግን በሕዝቦ ገጽታ ላይ ደስታና ፈገግታ ማንበብ ይችላሉ” አለው መንገደኛው።

በዚህ ጊዜ ንጉሡ ያ ሁሉ ገንዘቡ እንደባከነበት መጠርጠር ጀመረ። ወዲያው ወታደሮቹ ቶማስን ፍለጋ አካባቢውን አጥለቀለቁት።

ቅ/ቶማስ ተይዞ እንደመጣ “ቤተ መንግሥቴን ለምን አልሰራህልኝም”? አለው ንጉሡ።

“ሠርቻለሁ ጌታዬ” ቶማስ መለሰ።

“የታለ? ጫካው እንኳን መች ተነሣ?”

“በእርግጥ ምድር ላይ የድንጋይ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ፤ እኔ ግን በሰማይ ላይ ቤተ መንግሥት ሠርቼልዎታለሁ” አለው ቶማስ ለንጉሡ። ይህን ጊዜ ንጉሡ ተቆጣ! ቶማስን እጅ እግሩን እየቆራረጡ እንዲያሰቃዩት አዝዞ ወደ እስር ቤት አወረደው።


በዚያች ለሊት የንጉሡ ወንድም የሆነው ልዑል ጋድ በድንገተኛ በሽታ መጣደፍ ጀመረ። ሊነጋጋ ሲልም ነፍሱ ወጣች። የጋድ ነፍስ በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማያት ወጣች። ካጀቧት  ቅዱሳን መላዕክት አንዱ ብዙ አብያተ መንግሥታትን እያሳያት “ትኖሪበት ዘንድ ደስ ያለሽን ምረጪ” አላት። የጋድ ነፍስም ውብ የኾነውን ቤተ መንግሥት መረጠች። “ይህ ቤተ መንግሥት የአንቺ አይደለም ቶማስ ለንጉሥ ጎንዶፓረስ የሠራለት ሰማያዊ ቤተ መንግሥት ነው” አላት። በዚህች ሰአት የልዑል ጋድ ነፍስ ከሥጋው ጋር ተዋሐደች። ጋድ ሊቀብሩት በተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተንቀሳቀሰ። ከዚያም አፈፍ ብሎ ተነሣ። ልዑል ጋድ በዚያች ቅጽበት የተመለከተውን ለንጉሥ ጎንዶፓረስና ለተሰበሰቡት ሁሉ ነገራቸው።

ንጉሡ ይህን ሲሰማ በቶማስ ላይ በሰራው ግፍ ሁሉ አዘነ። ተፀፀተም። ያ-ያሰበው ቤተ መንግሥት መሰራቱን ሲሰማ ቶማስን ከእስር ቤት አወጣው። እርሱና ቤተሰቡም ክርስቶስን አምነው ተጠመቁ። ንጉሥ ጎንዶፓረስ “ሌላም ቤተመንግሥት ስራልኝ” እያለ ያለውን ሁሉ ገንዘብ ለቶማስ ይሰጠው ጀመር።  

************
“የለንደኑ ንጉሥ ጎንዶፓረስ ማን ይሆን?”

አሁን ለቤተክርስቲያናችን የሚያስፈልገን ንጉሥ ጎንዶፓረስን የመሰለ ልብ ነው። አሁን የለንደን ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን ብዙ ንጉሥ ጎንዶፓረስን የመሰሉ ሰዎች ያስፈልጋታል። የንጉሡን ያክል ሀብት ሳይሆን የንጉሡን ያክል ልብ ያስፈልገናልና።

      በለንደን ቅ/ሥላሴ በተደረገው ጉባኤ ዲ/ምንዳዬ ቃል ገባ። “ለዚህች ታዳጊ ቤተክርስቲያን አንድ የመዝሙር ሲዲ ሰርቼ ገቢው ለቤተክርስቲያኑ ማሰሪያ ይኹን” አለ። እንዳለውም በቅርቡ ለንደን ገብቷል። የመዝሙር ካሴቱንም በቅርቡ ያስመርቃል።

       የለንደን ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን የተመሰረተበትን 6ኛ ዓመት በቅርቡ አክብሮ ነበር። ይኽ በአጭር ጊዜ በፍጥነት ያደገ ቤተክርስቲያን ነው። ቤተክርስቲያኑ በየዓመቱ በሚያደርገው ጉባኤ ብዙ የባዘኑ ነፋሳት ረፍት አግኝተዋል ቢባል ማጋነን አይኾንም። ይኽ ቤተክርስቲያን የዛሬ 6 ዓመት በአባታችን በአቡነ ሙሴ ሲመሰረት የመጀመሪያ የመባዕ ገቢው 20 ፓውንድ ነበር። አኹን ግን ምዕመናኑ በቁጥር በዝተዋል። የአገልግሎቱ አድማስም እየጨመረ ነው። 6 አመት ተንስኡ ለፀሎት ያለው ወንድማችን በቅርቡ ሰላም ለኩልክሙ ብሎ ሥልጣነ ክህነትን ተቀብሎ ቀስስ ቴዴ ተብሏል!
  
ይኽን ቤተክርስቲያን የምንገለገለው በክራይ ነውና ካሕናቱ ለቅዳሴ መሯሯጥ ግድ ይላቸዋል። ቦታውን በተሰጠችን አጭር ጊዜ መልቀቅ አለብንና ረጋ ብሎ መቀደስ አይታሰብም። ሰፋ ያለ ትምህርት መስጠት አይታለምም። መዘምራን 3 መዝሙሮችን ለመዘመር ቢያጠኑም ሰአት የለምና መዝሙራችን በአጭሩ ትቀራለች። ሕጻናቱን ማስተማር ማዘመር ወዘተ ተረፈዎች በጊዜ እጥረት አናስባቸውም። ከብዙ በጥቂቱ ከረጅሙ በአጭሩ የዘወትር አገልግሎታችን ይህ ነው።

 የራሳችንን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለምን አንሰራም ተባለ። “አንድ ሺህ ለአንድ” የሚል ንድፍ ተነደፈ። እያንዳንዳችን አንድ ሺህ ብር አዋጥተን አንዲት ብሎኬት ብንገዛ ሙሉው ቤተክርስቲያን ይሰራል ተባለ።

ቤተክርስቲያናችን ንጉሥ ጎንዶፓረስ የመሰለ ብዙ ሰዎችን ትፈልጋለች ብለን ነበር፤ ይህ ንጉስ ባለው ፀጋ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ሰርቷል። እኛም እንደ አቅማችን ትንሹ ንጉሥ ጎንዶፓረስ መኾን ይገባናል። ልብ በሉ! የዚህ ስራ መሰረቱ ልብ እንጂ ገንዘብ አይደለምና ልብ ሲሰጥ እጅም ይሰጣል።

አንድ ብሎኬት ብቻዋን ብትቀመጥ ለምንም አትጠቅምምና ብቸኝነት ይሰማታል። አንዱ የራሱን ብሎኬት ሲያስቀምጥ ሌላውም በዚያ ላይ ሲደርብ ቀጣዩ ሲቀጥል ቀስ እያለ እስከ ጣራው ይደርሳል። አራቱም መአዘን ይገጣጠሙና የፍቅር ቤት ይሰራል። በሕብረትና በፍቅር ስንሰራው ፍቅር ያለበት ቤት ትኾናለች። ብዙዎች ሕንጻ ኖሯቸው ፍቅርና አንድነት የሌላቸው አሉና ይኽን በሕብረት መስራቱ ዋጋ አለው። ይኽ ሚሥጢር እንደምን ያለ ሚሥጢር ነው! ይኽ ሕብረት እንደምን ያለ ሕብረት ነው! ወርቃማው የኢትዮጲያዊያን አባባል እንዲኽ ይላል። “ግድግዳ እርስ በእርሱ ካልተደጋገፈ አይቆምም” ይኽ እውነት ነው። ለመቆም መደጋገፍ ያስፈልጋልና። ቀብሩን ለቀባሪ ሳይሆን ለሟች አረዱ እንዲል ይህችን ታላቅ ስራ ሳይደጋገፉ መስራት አይቻልም።


ይህች አንዷ ብሎኬት የፍቅር ምሳሌ ናት!

ይህች አንዷ ብሎኬት የሕብረት ምሳሌ ናት!

ይህች አንዷ ብሎኬት ታላቅ ዋጋ አላት!

“ግንበኛ የናቀው ድንጋይ የማዕዘን ራስ ይኾናል” ተብሎ ተፅፋልና ይህች አንዷ ብሎኬት የቤተክርስቲያን ራስ የኾነው የጌታ ምሳሌ ናት!