Friday, 6 July 2012

ከባድ ጦርነት ታውጆብናል!



ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው የተነሱ የዓለማችን ኃያላን መንግሥታት ካልተቧቀስን አናርፍም ብለዋል። ዛሬ ጠዋት በወጣው የቢቢሲ ዜና ለዘመናት የተፈራው ታላቅ ጦርነት እንደሚነሳ ምንጮች እየዘገቡ ነው። የምን መታገስ ነው ሲሰበር ይንሰጠር ያሉም አልጠፉም። ቀን ሲደርስ አንባ ይፈርስ እንዲሉ የጦርነቱ ቀን ደረሰ።

ሥጋ ሠራዊቱን ዘመዶቹን እነ ዘረኝነትን እነ መከፋፈልን ፣ ዝሙትን፣ ቅናትን ፣ ምቀኝነትን አስከትሎ ደረቱን ነፍቶ ልቡን አሳብጦ ውረድ እንዋረድ እያለ ነፍስን ሊወጋ ይሸልል ጀመር። እትዬ ነፍስም በተራዋ ሠራዊቷን አስከትላ ዘመዶቿን እነ ፍቅርን እነ መቻቻልን ፣ ደግነትን ፣ ድንግልናን ፣ ጸሎትን ፣ስግደትን ፣ ጾምን ይዛ እንዲህ እያለች መፎከር ጀመረች።

አንተ ከንቱ በስባሽ አንተ ከንቱ አፈር፤
ሥጋ ለበሬ ነው ና እና በእኔ ተቀደስ።
አልመለስ ብትል ብትደነፋማ
ሞክረኸኝ እየኝ ጀግንነቴን እንካ

አለች እትዬ ነፍስ እየተውረገረገች።

ሥጋ ምድራዊ ነህ ነፍስ ሰማያዊ።

ሥጋ በስባሽ ነህ ነፍስ ዘላለማዊ።

ሥጋ ሟች ነህ ነፍስ ሕያው።

እንዲያው ወፈር ስትል ለዓይን ብትማርክ
ጉራህ አልተቻለ መቀመጫም አጣን።

እያለች ነፍስ ልቧ ቅቤ እስኪጠጣ ድረስ የልብ የልቧን እንደ ጉድ አዘነበችው።

አቶ ሥጋ በበኩላቸው አሸሼ ገዳሜ እሪ ብለው ጮኹ
አንቺ ነፍስ ዋ…. ዋ…. ዋ ዛሬ ጉድ ሳይፈላ
በትዕቢት ታውረሻል ዓይንሽ ይብራ እያሉ አብዝተው ፎከሩ።


እትዬ ነፍስ ለአቶ ሥጋ አንድ ታሪክ እንዲህ ብለው አወጓቸው “ሰውዬው ድንኳን ሰባሪ ነው አሉ። ሁለት ቦታ የአቡዬ ድግስ እንዳለ ይሰማል፡፡ ሰዓቱ ሲደርስ እንደ ተጠራ ሰው የክት ልብሱን ለብሶ ይወጣል፡፡ የሁለቱም ድግስ የተለያየ ቦታ ነበር፡፡ ወደ አንደኛው እየሄደ ሳለ የዚያኛው ድግስ ቢበልጥስ ብሎ ተመለሰ፡፡ ወደዚያም ጉዞ እንደ ጀመረ የዚህኛው ምስር ሆኖ ያኛው ቁርጥ ቢሆንስ ብሎ እንደገና ተመለሰ፡፡ እንዲህ ሲያመነታ ሰዓቱ እያለፈበት ሄደ። በዚህ ጊዜ በመካከለኛ መንገድ ላይ ቆመና በጭንቀት ‹‹አቡዬ የዛሬን ብቻ ለሁለት ይሰንጥቁኝ›› ብሎ ጸለየ ይባላል!”

ዓለምንም እግዚአብሔርንም መያዝ አይቻልም፡፡ ሁለት አባሮም አንድ መያዝ አይቻልም፡፡ ሥጋንም ነፍስንም እሩሩ ማለት አይቻልም አሉ እትዬ ነፍስ አቶ ሥጋን እንደ ሕፃን እሹሩሩ እያሏቸው። ሕፃን ልጅ እናቱን አለቅሽም እያለ ገበያና ሥራ እስኪከለክል እንዳላስቸገረ፣ ሲያድግ ደግሞ እናቱን አትጠብቂኝ እያለ እንደሚፎክር እኛም እንደ ሕፃንኑ መሆን አንችልም አሉ እትዬ ነፍስ እያፌዙ። እዚህ ጋ አቶ ሥጋ አጎረመረሙ። እትዬ ነፍስ ግን አቶ ሥጋን ማናደድ እንደ ትርፍ ጊዜያቸው ያስደስታቸዋልና ማናደዱን እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ፦

 “ዓለማዊ ሰዎች ዓለምን ከፍ አድርገው እሽኮኮ ቢሏት በጀርባቸው ቢያዝሏት፣ እሹሩሩ ዓለም ቢሏት አይገርምም። ዓለማዊ ናቸውና ዓለምን ቢወዱ አይገርምም። ዓለም ራስዋ የሚገርማት ግን መንፈሳዊ ተብለን ዓለምን እሽኮኮ እናድርግሽ ስንላት ነው። በጀርባችን እንዘልሽ እሹሩሩ ዓለምዬ እንበልሽ ስንላት ዓለም ራስዋ ከትከት ብላ ትስቅብናለች! በዓለም ውስጥ ብንኖርም ዓለም በእኛ ውስጥ ከኖረች ግን አደጋ ነው! ደብረ ታቦር ላይ ዘምረው ቀራንዮ ላይ የከዱ ብዙዎች አሉአሉ እትዬ ነፍስ እንደ ምሁር ከረቫታቸውን ከፍ ዝቅ እያደረጉ።

ይህን ጊዜ አቶ ሥጋ ቦግ አሉ!! ንዴታቸው እንደ ጉድ ተቀጣጠለ። ወደ እትዬ ነፍስ ተንደረደሩና በያዙት ቢላ ክፉኛ ወግተው ዘነጣጥለው ፣ ዘነጣጥለው ገነጣጥለው ሊለቋቸው አሰቡና ተውት! እትዬ ነፍስን በቢላ ሳይሆን በቅኔ ወጋ ሊያደርጓቸው ፈለጉ። ስለ ሥጋና ነፍስ ግዕዝ ምን እንዳለ አልሰሙም እንዴ?” አሉ አቶ ሥጋ እትዬ ነፍስን በፌዝ እያዩ።

ደግሞ ምን አለ? እትዬ ነፍስ ጠየቁ።

ስለ አንቺና እኔ ግዕዝ እንዲህ ብሏል

“ኢትቀውም ነፍስ ዘእንበለ ሥጋ

ፐ.. ፐ.. ደግሞ ምን ማለት ይኾን? አሉ እትዬ ነፍስ እየተውረገረጉ።

አቶ ሥጋም ነፍስ ያለ ሥጋ አትቆምም ማለት ነዋ” ብለው በረዥሙ ሳቁ። አሁን ደግሞ እትዬ ነፍስ ቦግ አሉ። ቦግ ቦግ ማለት የሥጋና የነፍስ ልማዳቸው ሆነ። አይ ከዚያማ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው እንደ ጉድ ተቧቀሱ፣  እንደ ጉድ ታገሉ ፣  እንደ ጉድ ተፋጁ…. 


ቢቢሲ የዘገበው በሥጋና በነፍስ መካከል የተፋፋመውን ይህን ጦርነት ነበር!

ሰው የተፈጠረው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ነው። እነሱም እሳት ፣ ውኃ ፣ መሬት ፣ ነፋስ ናቸው።

አራቱ ባሕርያተ ሥጋ እርስ በእርሳቸው ተቃራኒ መስተፃርራን ናቸው። እሳት በውኃ ይጠፋል። እሳት ውኃን ያሞቃል። ነፋስ መሬትን ያንቀጠቅጣል። መሬት ተራራዎች ነፋስን ያቆማሉ። እንዲህ እርስ በእርሳቸው መስተፃርራን ናቸው። የሰው ልጅ ከነዚህ እርስ በእርሳቸው ተቃራኒ ከሆኑ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ስለተፈጠረ ሰውነቱ የጦርነት ከተማ ነው” ይባላል። ሥጋና መንፈስ የሚዋጉበት ታላቅ የጦርነት ከተማ የሰው ልጅ ነው።

የነፍስ ሽለላ መቆሚያ አጣ
ትዘልፈው ዠመር ሥጋን እንዲህ ብላ

አልሰማህም ወይ አላለበብክም ወይ
ጳውሎስ በኤፌሶን ምን ብሎ እንደነበር?


ቅ/ጳውሎስ በሮማ እስር ቤት ታስሮ እያለ የእስር ቤቱን ጠባቂ እያየ መልዕቱን እንዲህ ብሎ መጻፍ ዠመረ።

የእምነት ጋሻ አንሱ ፤ የመዳንን የራስ ቁር አድርጉ፤ የመንፈስን ሰይፍ ያዙ። እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላመ ወንጌል ተጫምታችሁ ቁሙ። ጦርነቱ ከሥጋና ከደም ጋር አይደለም ከዚህ ዓለም ገዥ ከሆነው ከዲያቢሎስ ነው እንጂ ኤፌ [6: 14]


ምርጥ እቃ የተባለው ንዋየ ኅሩይ ቅ/ጳውሎስ የእስር ቤቱን ወታደር በማየት ብቻ ሚስጢር ያለውን መልዕክት ጽፏል።
ሮማዊያን ወታደሮች የሚለብሱት የጦርነት ትጥቅ ዘመናዊ ነበር። የራስ ቁር ማለት ከብረት የተሰራ በራስ ላይ የሚደረግ ሞተረኞች የሚያደርጉት እንደ ሄልሜት ያለ ነገር ነው። ዝናር ማለት ወገብን መታጠቂያ ነው። ጥሩር ማለት ከብረት የተሰራ የደረት መከላከያ ነው።


ይኼ ኹሉ ዝግጅት ጦርነት ስላለ ነው። ጦርነቱም በሥጋና በነፍ መካከል ነው። ሥጋ ሲያሸንፍ መበላላት ፣ መቦጫጨቅ ፣ መለያየት ፣ መነካከስ ፣ ዝሙት ፣ ዘረኝነት ምቀኝነት ጥላቻ ይሰለጥናሉ። ነፍስ እንደምንም ታግላ ተፍጨርጭራ ስታሸንፍ ፍቅር ፣ ሰላም ፣ ትህትና ፣ ትዕግስት ፣ ደግነት ይሰለጥናሉ። ለዚህ እኮ ነው ቅ/ጳውሎስ “ሥጋዬንም ለነፍሴ አስገዛዋለሁ” ያለው። 1ኛ ቆሮ. [9: 26]

       እነኾ የአቶ ሥጋና የእትዬ ነፍስ ጦርነት እስከ አለም ፍጻሜ ይቀጥላል። በመሃል እየገባን የጦርነቱን ዘገባ በትኩሱ እንዘግባለን። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሰበር ዜና እንደደረሰን ሥጋ በጦርነቱ ድል እየቀናው ነው። አያሌ ነፍሳት ዳግም እንዳይቆሙ ኾነው ተወግተው ቆስለዋል። የሕክምና ባለሙያዎቹ ካህናትም የቆሰሉትን ነፋሳት ለማከም ደፋ ቀና እያሉ ነው። የቀይ መስቀል ሠራተኞች መምህራንና ዘማርያንም የተቻላቸውን ለመርዳት እየተፋጠኑ ይመስላል። እንዲህ የተረዳችውም ነፍስ እያገገመች ትመስላለች።

ነፍስ ሥጋን ክፉኛ ልትወጋው ተንደረደረች!

አያያያያ ነፍሴ እንዴት ያለ ግሩም ቅጣት ምት ነበረች!

ግን ተስታለች!

ተስፋ

ለለፋ

ትመጣለች

ፊሽካ ሳይነፋ

እያለች ነፍስ አሁንም የሞት ሞትዋን ታግላ ተነሳች።

ማን ያሸንፍ ይኾን? 




No comments: