Saturday, 17 March 2012

ዐቢይ ጾም

የደሃ ግድርድር ሀብታም ይጋብዛል! ብሎ ሀብታሙ ጓደኛዬ እኔን ለመተረብ ሲፍጨረጨር “ምክር ከድሃ ነበርሽ ማን ቢሰማሽ” ብዬ የደሃ ከረባቴን ከፍ ዝቅ ባደርጋት “ራቁቱን ለተወለደ ጥብቆ መች አነሰው” ብሎ በተውሶ የለበስኳትን ሱፌን ናቃት! “ልፋ ያለው በህልሙ ክብደት ይሸከማል” ብዬ የሚለውን ላለመስማት ጆሮዬን ይዤ ከአጠገቡ ጠፋሁና ይህችን ጥሑፍ ጣፍኩ፦

አንድ ሰው በአንድ ወቅት እንዲህ  ብሎ ፈጣሪውን ጠየቀ፤ “በቤትህ የቆምኩት ሰው ጠፋቶ ነውን? ከሰው ለይተህ የጠራኸኝስ ሰው ጠፍቶ ነውን? በዛች በአውደ ምህረት እንድቆም የፈቀድከውስ ሰው ጠፍቶ ነውን? እያለ ጥያቄዎችን አወጣ አወረደ፤ እንደ ቸርነትህ እንጂ እንደ በደሌ ያልከፈልከኝ እንደ ስራዬ እንደ ሀሳቤ ያልከፈልከኝ ቸርነትህ ብዙ ምህረትህ የበዛ ጌታ ሆይ ሁሉን የምታደርገው ሰው ጠፍቶ ነውን? እያለ ያ ሰው ፈጣሪውን ጠየቀ። ፈጣሪም እንዲህ ብሎ መለሰለት
“ሰው የማያውቃቸው በሰው ዓይን ያልገቡ ለአገልግሎት የተመረጡ ብዙ ሰዎች አሉ፤ መዝሙረኛው ዳዊት በ129ኛው መዝሙሩ ላይ አንተ ኃጢአትን ብትቆጣጠር በፊትህ ማን ይቆማል? እንዳለ ሁሉን አይቼ እንዳላየሁ ሆኜ በቤቴ እንዳቆምኩህ አንተም ታውቃለህ!  

“ከእንግዲህ የሰው ልጅ ሆይ ሰው ሁን!”


ዐብይ ጾም፦

እንደ ሰው ሆኖ ለመጾም በገዳም አደረ ፤
ከዲያቢሎስ ዘንድ ተፈተነ ፤
የጨለማን መኳንንት በአምላክነቱ ኃይል ሻረ።
 ጌታችን አርባ ቀንና አርባ ለሊት የጾመበት ገዳመ ቆሮንቶስ ይህን ይመስላል
እስራኤላዊያን በአንድ ወቅት ለምን ጾማችን በእግዚአብሔር አይሰማም? ብለው ይጠይቁ ነበር፤ በእውኑ ብዙ ግዜ ጾማችን የማይሰማው ለምን ይሆን? ለዚህ የእስራኤላዊያን ጥያቄ ነብዩ ኢሳይያስ ድምፁን ከፍ አድርጎ  ለእስራኤላዊያን  መለሰላቸው፤ እነሆ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእውኑ እኔ የመረጥኩት ፆም ይህ ነውን? ፆማችሁ በጥልና በክርክር የተከበበች ናት፤ የልባችሁን ሁሉ ትፈጽማላችሁ፤ በእውኑ እኔ የመረጥኩት ፆም ይህ ነውን? ኢሳ 58:5 ዛሬም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ እኛን ይጠይቀናል “በእውኑ እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነውን”? እኔ የመረጥኩት ጾም የሚለውን ስናሰምርበት እግዚአብሔር የመረጠው ጾም አለ ማለት ነው፤ እግዚአብሔር የመረጠው ጾም ምን አይነት ጾም ይሆን? መልሱን በወንጌል ላይ እንዲህ እናገኘዋለን፦
ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ ፊታችሁን በፍቅር ቅባት ተቀብታችሁ የምትጾሟት ጾም ታላቅ ዋጋ አላት [ማቴ. 6: 16] ስትጾሙ የሚለውን ቃል አሁንም ስናሰምርበት መጾም እንዳለብን ያስረዳናል።

ልበ አምክ ዳዊት ከመጾሙና ለመዘመር በገናውን ከመደርደሩ በፊት እንዲህ አለ፦
አቤቱ ንፁህ ልብን ፍጠርልኝ// ልበ ንጹኃ ፍጥር ሊተ እግዚኦ [መዝ. 50: 10] ዳዊት ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ ብሎ ከለመነ በኋላ በገናውን እየደረደረ ዘመረ ጾመ ፀለየ ፤ ጾምና ዝማሬውም በእግዚአብሔር ተሰማች! እኛም ለመዝሙር በገና ከመደርደራችን፤  ከመጸለያችንና ከመጾማችን በፊት አቤቱ ንፁህ ልብን ፍጠርልኝ ማለት እንዳለብን ልበ አምላክ ዳዊት አስተማረን።

ስለ ጾም በወንጌል ላይ እንዲህ ተጽፏል “ይህ ጋኔን ያለ ጾምና ፀሎት አይወጣም” // ዝንቱ ዘመድ እይወጽዕ ዘእንበለ ጾም ወበ ፀሎት [ማቴ. 17: 21] ጾም አጋንንትን እንዃን የማስወጣት ታላቅ ኃይል አለው!!!  ነገር ግን የመናፍቃኑን መፅሐፋ ቅዱስ ስንመለከት ይህን ቁጥር ዘለውታል!
ጾም አጋንንትን ለማውጣት ኃይል እንዳለው ስለሚናገር የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ቁጥር 21 የሚለው እንዳለ ተዘሏል!

እኛ ግን ከስራችን በፊት ሁሉ መጾም ይገባናል፤ ሐዋርያቱ ከአገልግሎታቸው በፊት ጾሙ ጌታም ተዓምራት ከማድረጉ በፊት እኛን ሊስተምረን ጾመ፤ እነ ዳዊት ንጉሥ ሆነው ሳለ ጾሙ፤ ነብያቱ ሁሉ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በተስፋ እየተጠባበቁ    ጾሙ! 

ጾምሰ እማ ለፀሎት ወእህታ ለአርምሞ ወነቃየ ለአንብዕ //
ጾም የጸሎት እናት የትዕግሥት እህት የንስኃ እንባ ምንጭ ናት!


እንደ ዳዊት በንጹህ ልብ የምትጾም ጾም ዋጋዋ ታላቅ ናት፤ ለዚህ ነው ዲያቆኑ በቅዳሴ እንዲህ የሚለው፦

ሰው በልቦናው ቂምን እና በቀልን ማንም በማንም ላይ ቢሆን አይያዝ // ትዕዛዝ አበዊነ  ሐዋርያት እያንብር ብዕሲ ውስጠ ልቡ ቂመ ወበቀለ በቅንአተ ላዕለ ቢፁ ወኢላዕለ መኑሂ። የተጣላን ታርቀን የበደልን ይቅርታ ጠይቀን ከኃጢአት ሁሉ ርቀን ዋጋ ያላት ደስ የምታሰኝ፤ የእግዚአብሔርን ፀጋ ፤ ምህረቱን፤ ቸርነት ደግነቱን የምንቀምስበት ጾም ትሁንልን ፤አሜን።

Friday, 9 March 2012

“የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና የምነቅፍብህ ነገር አለኝ!”


 “አምራለሁ ብላ ተኩላ አይኗን አጠፋችው ቸኩላ!" ብሎ ሲተርባት እሷም ቀበል አድርጋ “መከራው ያላለቀለት በሬ ቆዳው ለነጋሪት ይጠፈራል” ብላ አፉን አስያዛቸው። ከእኛ ሰፈር ሁለት ፍቅረኛሞች ከሚጎሻሸሙበት የቅኔ አዝመራ በመነሳት ይህ ጽሁፍ ተጀመረ።

“የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና የምነቅፍብህ ነገር አለኝ!”
ራዕይ 2:4

አንድ ወዳጄ የልብ የልቡን ሊያወጋኝ ነበር እንዲህ ብሎ ያጫወተኝ፤ እኔም የልብ የልቤን ስለነገረኝ የልብ የልቡን ሰማሁት፤

እህህህ ……. አያያያያያ…..
እያለ መጣና ንግግሩን ቀጠለ፤ አገልግሎት ቀላል አይደለችም ለካ ጃል! ታንገዳግዳለች ለካ! አለ እራሱን እያንገዳገደ። ኧረ እንዲያውም ታጎብጣለች አለና እራሱ እንደ መጉበጥ አለ፤ ሆዴ በጀርባዬ ቢሆን ገፍቶ ገደል በጣለኝ ነበር ሲል አነጋገሩ አሳቀኝ። ይህ ወዳጄ ወትረ ነገረ ስራው ሁሉ ያስቃል፤ ቀልድ አሳምሮ ስለሚችልበት በንግግሩ ሁሌ እንደሳቅን ነው፤ ካሳቀን በኋላ ወዲያው ቁም ነገር ጣል ያደርጋል፤ ዛሬም እንደለመደው ትንሽ  ቀልዶቹን ከለቀቀ በኋላ ወዳጄ የልቡን ቀጠለ፤

እኔ የምልህ እኔ ብቻ ነኝ እንዲህ የሚሰማኝ ወይስ ሁላችሁም ይሰማችኋል? ለምን? እንዴት? እያለ ጥያቄውን አንጎደጎደው። የልቡን ለሚነግርህ ልብህን ስጠው! የሚለውን አባባል ለመጠቀም ልቤን ሰጥቼው ሰማሁት። ወዳጄ ይህ በአንተ የተጀመረ አይደለም፤ ሁሉም የሚሰማው ነውና ብዙ ራስህን አትረብሽ ብዬ ለማረጋጋትም ሞከርኩ።

   መኑ ይኅድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ?
በእርግጥ አገልግሎት ታንገዳግዳለች፤ እንደ ወዳጄ እኔም እየተንገዳገድኩ እንዳላሳያችሁ ለጊዜው መተያየት አንችልም! የሆነው ይሁንና የፈለገ ብንንገዳገድ የት እንሄዳለን? መኑ ይኅድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ? ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ርሃብ ነውን? ስደት ነውን? ግርፋት ነውን? እያለ ታላቁ ሐዋርያ የደረሰበትን ሁሉ እያነሳ ያስብና ይህ ሁሉ ግን ከክርስቶስ ፍቅር፣ ከአገልግሎት ፍቅር እንደማይለየው ይነግረናል። “እናቱ የሞተችበትና ውሀ ልትቀዳ የወረደችበት እኩል ያለቅሳሉ” እንዲል እኛ ይህን ያህል ባንፈተንም እንደ ሐዋርያው የተፈተነ ያህል እንሆናለን። “እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች” አሉ፤ አንዘንጋ ይህ እኮ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው! ታዲያ እንዴት ያለ ፈተና አገልግሎትን እንጠብቃለን? “የሰይጣንን አመጣት የማያውቅ አይመንኩስ” እንዲል አገልግሎትን ያልተረዳም እንዲሁ ነው።


ብልጥ የሆነ ሰው ግን በዚህ መረበሽ የለበትም። “ለላም ቀንዷ አይከብዳትም” ይባላል እኮ ሰዎች! ኧረ አይክበደን። እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ፤ 

ከአገልግሎት ፍቅር የሚለየን ማን ነው?

ይህ መልስ የሌለው ጥያቄ ነው። በቃ መልስ የለውማ። ለምን ታስባላችሁ? አልኳችሁ እኮ መልስ የለውም። ከአገልግሎት ፍቅር የሚለየን ማንም የለማ። 



ማን ነው ደስ ደስ እያለው አንዳች ሳይፈተን ያገለገለው?
ሐዋርያት ናቸውን? ካህናት ናቸውን? ሐዋርያው “መልካም ገድል ተጋድያለሁ ሩጫዬን ፈጽሜያለሁ ሐይማኖቴን ጠብቄያለሁ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” ብሎናል፤ በመንፈሳዊ ህይወት ለጽድቅ አክሊል መጋደል ያስፈልጋል፣ በአለማዊ ህይወት የጀግንነት ጎፈሬ ለማግኘት መጋደል ያስፈልጋል! አንድ አገልጋይ ያለፈተና የአገልግሎት የጽድቅ አክሊልን ማግኘት ፈለገ ማለት “ሳይዋጉ ጎፈሬ” እንደ ማለት ይሆንበታል!

“እርሻው ሲያምር ዳቦው ያምር” አለች ሴትዮዋ እውነቷን እኮ ነው፤ ይህን አባባሏን ስታስረዳም “እርሻ የተባልነው እኛ ነን፤ ይህ እርሻ ሲያምር ለአገልግሎት የሚጋገረው ዳቦም ያምራል” ብላ አስረድታለች። “አንድነት ያገባል ገነት” ይባላል እኮ ሰዎች! “አንድ ጣት ቁንጫ አይገድልም” ይላል የሀገራችን ገበሬ! ኧረ ምን የመሳሰሉ ምርጥ ምርጥ የአንድነት ተረቶች አሉን መሰላችሁ፤ “እርስ በእርሱ ያልተደጋገፈ ግድግዳ አይቆምም” ይልሃል የሀገርህ አባባል። በአንድ ወቅት ጀግናው ቀነኒሳ “ብቻውን የሚሮጥ አይቀድምም” ብሏል። እውነት ነው ብቻውን የሚሮጥ አይቀድምምና እስኪ ከሰው ጋር አብረን እንሩጥ፤ እናንተዬዋ ነገር ነገርን ይወልዳል፤ ሩጫ ሲባል በቅርቡ በከተማችን ለንደን የሚጀመረው ኦሎንፒክ ትዝ አለኝ። ሁሉም ይለማመድና እስኪ ሁሉም ይሩጥ፤ ሁሉም መንፈሳዊ ሩጫን ይሩጥ። ሩጫዬን ፈጽሜያለሁ አለ ሐዋርያው! ይህች ሩጫ በእርግጥ ታደክማለች! ሩጠህ ሩጠህ ሩጠህ መጨረሻ ላይ የምታገኛት የድካም ውጤት ግን እንዴት ትጥማለች መሰለህ! እንዴት የመንፈስ ደስታ ትሰጣለች መሰለህ! “ከባለቤቱ እጅ የዋለ እንቁላል አይሰበርም” እንዲል በጥንቃቄ የያዙት አገልግሎት ብዙዎች አጣጥመውታል፤ “በጅብ ችኩልነት ከምግብ ጣፋጭነት ሳይተዋወቁ ይኖራሉ” እንዲል የምንመገበውን እያጣጣምን ከሆነ በእርግጥ መጣፈጡ አይቀርም። ችግሩ በችኩልነታችን ሳንቀምሰው መቅረታችን ነው፤ እስኪ እንቅመሰው፣ እስኪ በአገልግሎትም እንበርታ።
ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋታችሁ ወደ ኋላ አትበሉ [ሮሜ 12:11]

አገልግሎታችን ለብ ያለ መሆኑን ቅ/ጳውሎስ አይቷል መሰል
“ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋታችሁ ወደ ኋላ አትበሉ” ይለናል። ጌታችንም ለብ ያለውን አገልግሎታችንን አይቷል እኮ፤ ለብ ስላልን እንዲህ ብሎናል “በራድ ወይም ትኩስ እንዳልሆንክ አውቃለሁ፤ በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ ከአፌ ልተፋህ ነው” ራዕ [3:13] ይህ ራዕይ ከጅምሩ እንዲህ ነበር፦ ሎዶቂያ የምትባል አንዲት ከተማ ከነበረባት የውሀ አቅርቦት ችግር የተነሳ ከአካባቢዋ ከሚገኙ ፍል ውሀዎች በቦይ ተስበው  ለከተማዋ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። ውሀው ወደ ከተማው ሲደርስ ለብ ይላል፤ ይህ ውሀ በብዙ ሚኒራሎች የተሞላ contaminated ስለሆነ ለመጠጣት በጣም አስቸጋሪ ነበር። ለቤተክርስቲያኑ መሪ እንደ ከተማው የውሀ ባህርይ እንዲህ የሚል መልዕክት ተጻፈለት፦ “በራድ ወይም ትኩስ እንዳልሆንክ አውቃለሁ፤ በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ ከአፌ ልተፋህ ነው” በአገልግሎታችን ለብ ያልን ሳይሆን ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ! ተብለናል።

“እሳት መጣብህ ቢሉት እሳር ውስጥ ገብቻለሁ አለ ሞኙ!” ፈተና ሲመጣ  ወደ ኋላ ማለት የለብንም፤ ይህ እራስን ለፈተናው ማመቻቸት ነውና።

“ወጣት የነብር ጣት” ነውና ነገሩ ወደ ኋላ ያላችሁ ሁሉ እንደ ቀደመው ኑ ፣ እንደ መጀመሪያው በርቱ ፣ እንደ በፊቱ በፍቅር አገልግሉ ይለናል ታላቁ ሐዋርያ! “የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና የምነቅፍብህ ነገር አለኝ!” ራዕይ 2:4 ይህ መልዕክትም ታላቅ ነው፤

“ሲበላ ለሚከሳ ሲነግሩት ለሚረሳ ለዚያም ምግብ ለዚህም ነገር ንሳ” እንዲል እስኪ ልብ ብለን እንስማ፤ “መናገር መልካም ነው ማዳመጥ ይበልጣል” እንዲል እስኪ እኛም ሐዋርያቱ የሚሉትን እናዳምጥ። አበው የዝሆን ጆሮ ይስጥ ይላሉ።
የአገልግሎት መሰረት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ምንድን ናቸው?

አንድ አገልጋይ ይህን ካላወቀ በእውኑ በአገልግሎቱ ሲናወጥ ይኖራል! ይህ የአንድ አገልጋይ የባንኩ የምስጢር ኮድ እንደ ማለት ነው፤ እነዚህም ፍቅር፣ ትዕግስት፣ ትህትና ናቸው።

v                       አገልግሎት ያለ ፍቅር ከንቱ ነው! 

v                       አገልግሎት ያለ ትዕግስት ከቶ አይቻልም!

v                       አገልግሎት ያለ ትህትና ፍሬ ቢስ ነው!

አገልግሎቱን የሚወድ ጆሮ ያለው ይስማ!
የቀደሙት አባቶች በአገልግሎት ያለፉበትን የአገልግሎት ሚስጢር በነጻ ይግዛ! ቅ/ጳውሎስ ለዚህ ነው የአገልግሎት መሰረት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን ፍቅርን፣ ትዕግስትን፣ ትህትናን እንድንገዛ የሚነግረን። ገላትያ 5:21    

አገልግሎት ጨለም ሲል ማማረር የለብንም፤ “ጨለማውን ከምታማርር ሻማውን አብራ” ይባላልና ሻማውን ግዛና አብራ! የፍቅርን ሻማ! የትዕግስትን ሻማ! የትህትናን ሻማ ግዛና አብራ፤ ይህን ግዜ ጨለማው ብርኃን ይሆናል።

የፍቅር ሻማ! ፍቅር ማለት የሚወዱንን ብቻ መውደድ ማለት ሳይሆን የሚጠሉንንም መውደድ ማለት ነው!

የትዕግስት ሻማ! የካህናቱ ልብሰ ተክህኖ ሰፊና የተንዠረገገ የሚሆነው ትዕግስታቸው እንደ ልብሳቸው ሰፊ መሆኑን ለማመልከት ነው፤ የመዘምራን ልብስ ግን እንደምናውቀው ጠባብ ነው፤ ትዕግስታችን ሰፊ ሲሆን ምን አልባት ልብሱም ሰፊ ይሆን ይሆናል!

የትህትና ሻማ! ያለ ትህትናማ ማንን ልናገለግል ነው? ታላላቅ አገልጋይ የሚባሉትን እስቲ እንያቸው፤ ከሁሉ ዝቅ ዝቅ ይላሉ። እውቀት ጥበብ ችሎታ ወዘተዎች ለእነሱ አይታሰባቸውም። ሰዎች ከፍ ሲያደርጓቸው ከልባቸው ይጠሉታል ዝቅ ሲሉ ደስ ይላቸዋል።
አገልግሎት በዲያቢሎስ ጥቁር መነጽር

የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው ዲያቢሎስ እነሆ በየዕለቱ ሐሜትንና ወሬዎችን ሊያቀርብላችሁ ዝግጁ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ጥሎችንና ችግሮችን መከራዎችን ያቀርብላችኋል፤ ኧረ ጆሮ ከሰጣችሁትማ ምርጥ ምርጥ ወሬ ሊያዋራችሁ ሁሌ ዝግጁ ነው! የሰዎችን ሚስጢርና አስተሳሰብ ሳይበርድ በትኩሱ ያቀርብላችኋል። በልባችሁ ቦታ ስትሰጡትም ትበሳጫላችሁ ትጨናነቃላችሁ። ብልጥ የሆነ ግን የጆሮውን በር ከእነዚህ ከንቱ ነገሮች ሁሉ ይዘጋል! ይገርማል! የማይጠቅም ነገር ሰምቶ የውስጥ ሠላምን ማጣት ምንኛ ያላስተዋልነው ነገር ነው!

ቢቻላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሠላም ኑሩ! የምትለዋን የሐዋርያውን መልዕክት እወዳታለሁ፤ ሮሜ 12:18
ዮሐንስ አፈወር ምን አለ መሰላችሁ፤ “አስተዋይ በየቀኑ ጠላቱን ወዳጁ ሲያደርግ ሌላው ግን በየቀኑ የልብ ወዳጁን ያጣል!” ብሏል። እነዚህ ሁሉ ቢደመሩ ግን ፍቅር ትዕግስት ትህትና ናቸው! 

አንድ አገልጋይ በአገልግሎት እያደገ ሲሄድ ተካፋይ የሚሆንባቸው ነገሮች እያደጉ ስለሚሄዱ ስህተቶችም እያደጉ ይሄዳሉ። ኃላፊነቱ እየጨመሩ ሲመጡ ሙሉ ግዜው ይዋጣል፤ ራሱንም ይረሳል። ለነፍሱ የሚያስፈልጋትን ምግብ ስለማያቀርብላት ቁልቁል ይወድቃል። እንደዚህ አይነቱ ሰው እሱ ራሱ ሳይሻገር ሌሎች ሰዎችን ከአንዱ ወደብ ወደ ሌላኛው ወደብ የሚያሻግር ድልድይን ይመስላል፤ ወይም ደግሞ እሱ ወደ ቤተ መቅደስ ሳይገባ ሰዎች እንዲገቡ የሚጣራ ደወልን ይመስላል! ለዚህ እኮ ነው ሐዋርያው “ለሌሎች ከሰበኩ በኋላ ራሴ የተጣልኩ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምኩ አስገዛዋለሁ” ያለው። [1ኛ ቆሮ 9:27]
“አገልጋይ” የሚለው ስም ለመላዕክት የተሰጠ ድንቅ ስም እንደሆነ ታውቃላችሁ! መላዕክት ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ የሚያገለግሉ መናፍስት አይደሉምን? ፤ መላዕክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል፤
ዕብ 1:14 መዝ 103:4 ይህን ድንቅ ስም በድንቅ አያያዝ ያዘው።

በአገልግሎት ማንኛውም አይነት ፈተና ሲገጥመን እግዚአብሔር ከፍ ላለ ተልዕኮ እያዘጋጀን እንደሆነ ታውቃላችሁ!? ቅ/ጴጥሮስን ያዘጋጀው ሥጋዊ ድካሙን እንዲያውቅና ከሌሎች ሐዋርያት በላይ ራሱን ከፍ አድርጎ እንዳያይ ነበር። ዮሴፍን በታላቅ ፈተና ውስጥ ለታላቅ ተልዕኮ አዘጋጀው፤ ነነዌን የሰበካት ነቢይን በማዕበል በወጀቡ ቢያልፍም ለካ ይህ ሁሉ ለተልዕኮ የሚያዘጋጁ ነበሩ!

አንተ ዓሣ አጥማጅ አገልጋይ ሆይ!
ይህች ጽሁፍ ለአገልግሎትህ እንደምትጠቅምህ ይታመናል።

“የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ!”
ይህች ጽሁፍ በአገልግሎታችን የቆምን የመሰለን እንዳንወድቅ፣ የወደቅን እንድንቆም ታስባ የተጻፈች ናት።
1ኛ ቆሮ [10:12]

በዐቢይ ጾም ገብር ኄር /ታማኝ አገልጋይ/ የሚላከው ኢሜልም እጅግ ይጠቅማልና ከወዲሁ አያምልጦ!

አንተ ዓሣ አጥማጅ አገልጋይ ሆይ!
መረቡን ወርውሮ በተገኘው ዘዴ ሁሉ የበዙ ዓሦችን የሚያወጣ ዓሣ አጥማጅ ምንኛ ብልኅ ነው!








Saturday, 3 March 2012




ሐዋርያዊት // ቤተክርስቲያን


የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል
“ወደ ተራራ ውጡ እንጨትም አምጡ ቤቱን ስሩ እኔም በሱ ደስ ይለኛል እከበርበታለሁም ፤
ዘሩባቤል ሆይ በርታ ህዝቤ ሆይ በርታ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ቤተ መቅደሴን ስሩ”
ትንቢተ ሐጌ 1: 7

+++ ስለ ቤተክርስቲያን አበው ብዙ ሰርተው አለፈዋል፤ ብርሐነ አለም ቅ/ጳውሎስም ስለ ቤተክርስቲያን ያልሆነው ነገር የለም ነበር። ይህች የቀደመችው እነ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ የደከሙላት ፤ ይህች ኖህ ከጥፋት ውሃ የዳነባት ከአለም ወጀብ መጠለያ መርከባቻን ፤ ይህች እነ ዳዊት ሊጠለሉባት የበረጧት መልካም ማረፊያችን ሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያን ናት።


“ከቤተመንግስቴ ከአእላፈት ቀን ይልቅ በቤትህ ልጣል ወደድኩ”
መዝ 83(84) ቁጥር 10



+++ ስለ ሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያን በደንብ ጠንቅቀን እንድናውቅ ግዜው ግድ ይለናል፤ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት  ትባላለች ምክንያቱም ከሐዋርያት ተያይዞ የመጣ ሥርዓቷን ጠብቃ ስለምትገኝ ነው። እስቲ በቅዳሴው ስለ ሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያን ዲያቆኑ የሚያዜመውን ውብ ዜማ በማስተዋል እንየው፤ ዲያቆኑ እንዲህ ይላል ፦


“ፀልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን አሐቲ ቅድት ጉባኤ እንተ ሐዋርያት ርትዕት”


[Pray for the peace of the one holy apostolic church orthodox in the Lord]
{ ሐዋርያት ለሰበሰቧት ክብርት ስለምትሆን አንዲት ቤተክርስቲያን ጸልዩ}


ከዜማው እንደምንረዳው አንዲት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ለመሆን 4 ነገሮችን
ማሟላት አለባት፤ የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ላዕለ ኩሉ /ከሁሉ በላይ ናት/ የቤተክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ነውና። ኤፌሶን 1:22፤ እስቲ 3ቱን ቀሪዎች ከዜማው በመነሳት አንድ በአንድ እንያቸው፦

1)      አሐቲ፦ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን አሐቲ ወይም አንዲት ናት። በከተማ ትሁን በገጠር; ከአፈር ትሰራ ከወርቅ ፤ በአውሮፓ ይሁን በአሜሪካ; ይህች ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ከሆነች አሐቲ ናት ወይም አንዲት ናት። በጸሎተ ሐይማኖት ላይም ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን ብለን እንደምንጸልየው ማለት ነው።


“አንድ ጌታ አንዲት ጥምቀት አንዲት ቤተክርስቲያን እንደሚል”
ኤፌ 4:4










2)    ቅድስት፦ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር በደሙ ያጸናት ቅድስት ናት።
“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ጠብቁ እንደሚል” የሐዋ. 20:28
ቤተክርስቲያን ቅድስናዋን ማንም ሊያስቀርባት ወይም ሊያረክስባት አይችልም፤ ለምሳሌ በቤተክርስቲያን የሚቀድሰው ካህን ሰይጣን አስቶት የማይገባ ባሕርይ ቢኖረውና ወደ ቤተክርስቲያን ቢመጣ በካህኑ ምክንያት የሚሰጠው መንፈሳው አገልግሎት ዋጋውን
ሊቀንስው አይችልም፤ ያ ካህን ልክ ቤተክርስቲያን ሲገባ አብሮት የነበረው ዲያቢሎስ ከውጭ ሆኖ ይጠብቀዋል እንጂ ወደ ውስጥ አይገባም፤ ልክ አገልግሎቱን ፈጽሞ ሲወጣ በዛ ባሕርይው ከቀጠለ ያም ዲያቢሎስ አብሮት ይቀጥላል ማለት ነው። ካህኑ ልክ እንደ ስልክ አገናኝ operator ነው፤ ስልክ የምታገናኘን ሴት ባሕሪዋ መልካም ባይሆን እንደምንም ታግሰን አላማችንን እንደምንፈጽመው ማለት ነው። ካህን ዘር እንደሚዘራ ገበሬ ነው ፤ ገበሬ በተበላሸ እጁ ዘር ቢዘራ የዘራው ዘር መብቀሉ አይቀርምና። ወደ ሃሳባችን ስንመለስ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር በደሙ ያጸናት ቅድስት ናት ብለናል; ልብ ብለን ካስተዋልነው ቅዱስ ደሙን በላዕለ መስቀል ላይ ያፈሰሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቅ/ጳውሎስም ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ስለሚያውቅ  “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ጠብቁ ብሎ በሐዋ. 20:28 ተናግሯል።
  
3)     እንተ ሐዋርያት፦
ይህ ክፍል ዋናው የቤተክርስቲያን መሰረት ነው፤ ሐዋርያዊት የሆነች ቤተክርስቲያን ከሐርያቱ ጀምሮ እዚህ የደረሰችበት አመጣጧ እነሆ እንዲህ ነው፦

+++ ጌታ ለሐዋርያት አለቃ እንዲህ አለው; አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚህ ዐለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራለሁ…ማቴ 16:18፤ ቅ/ ጴጥሮስም ወንጌላዊው ማርቆስን አስተማረው; ቅ/ማርቆስም በግብፅ መንበሩን መሰረተ። ከማርቆስ ቀጥሎ አንያኖስ ከአንያኖስ 20 ፓትርያርክ ቀጥሎም አትናቴዎስ ተተካ፤ ይህ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ወደ ሃገራችን የመጣው በፍሬምናጦስ ወይም በከሣቴ ብርሐን አባ ሠላማ አማካኝነት ነበር።  

+ የፍሬምናጦስ ታሪክ እነሆ፦ ፍሬምናጦስ ኢትዮጲያዊ አልነበረም ፤ ጌታ ባረገ በ357 ዘመን አንድ ነጋዴ ከኢየሩሳሌም ፍሬምናጦስና ሲድራኮስ የተባሉ ሁለት ልጆችን ይዞ መጣና እንባቆም በተባለ አንድ ገበሬ ቤት ገብተው አደሩ። ከጥቂት ቀናት በሗላ አባታቸው ሞተ፤ ልጆቹም በእንባቆም ቤት መኖር ጀመሩ። ከእለታት በአንድ ቀን ፍሬምናጦስ የኢትዮጲያን ሰዎች ባህልና ሐይማኖታቸውን አደንቃለሁ; ነገር ግን ሥጋ ወደሙን ለምን አትቀበሉም? ብሎ ገበሬውን ጠየቀው; ያም ገበሬ ስንቅ አስይዞ በንጉስ ኢዛና ፈቃድ እስክንድርያ ሄዶ በሊቀጳጳሱ በአትናቴዎስ ተሹሞ ፓፓስ ሆነ። ስሙንም ከሣቴ ብርሃን አባ ሠላማ አለው /ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ማለት ነው/ ፍሬምናጦስም በእንዲህ ባለ መንገድ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን ወደ ሃገራችን አምጥቷላ ማለት ነው።

“ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ” // Apostolic Succession”


ጌታ      ቅ/ ጴጥሮስ        ቅ/ማርቆስ       አንያኖስ        አትናቴዎስ
ፍሬምናጦስ /ከሣቴ ብርሐን አባ ሠላማ/

ለማየት እንደሞከርነው ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት የምትባለው ከጌታ ጀምሮ በሐዋርያቱ ቅብብሎሽ ስለምትመራ ነው። ይህም በእንግሊዘኛው Apostolic Succession ወይም ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ በመባል ይታወቃል።

+++ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ በቅዳሴ፦ እስቲ በሚመጣው እሁድ ወንጌል ከመነበቡ በፊት ካህናቱን ልብ ብለን እንስማ; እንዲህ ይላሉ፤ ገባሬ ሠናዩ ካህን ወይም ዋናው ካህን አስቀድሞ እንዲህ ይላል፦

 His kingdom & his righteousness which he delivers to me I deliver to you
 [ዘአወፈየኒ አወፈይኩከ] ወይም የሰጠኸኝን ሰጠሁህ  

ካህኑ የሰጠኸኝን ሰጠሁህ ብሎ ወንጌሉን ለንፍቅ ካህን ወይም ለሁለተኛው ካህን ይሰጠዋል ፤ ሁለተኛው ካህንም ለዲያቆኑ ይሰጠዋል; ይህ ነው ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የሚባለው; ዋናው ካህን የጌታ ምሳሌ ሲሆን ሁለተኛው ካህን ደግሞ የቅ/ጴጥሮስ ምሳሌ ነው፤ ዲያቆኑም የምዕመናን ሁሉ ምሳሌ ነው ማለት ነው!! ወርቅ የሆኑ አበው ወርቅ የሆነ ሥርአትን ከተግባር ጋር አወረሱን!

+++ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የቤተክርስቲያን ዋና መሰረቷ ነው። ለምሳሌ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይህ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ስለሌላቸው ጥምቀቱም ሆነ ሌላው አገልግሎት ሐዋርያዊ አይደለም ማለት ነው። መንፈሳዊ አገልግሎትን ልንፈጽም የምንችልባቸው ሐዋርያዊት የሆኑ 5 እህትማማቾች ቤ/ተ/ክ ሲኖሩ ከምዕራቡ አለም በሐዋርያዊ ሥርአት ስለሚለዩ ኦሬንታል ወይም ምስራቃዊ ይባላሉ።


        5ቱ ሐዋርያዊት ኦሬንታል ቤተክርስቲያኖች
(በነዚህ ቤተክርስቲያናት መቁረብና መጠመቅ ይቻላል)
 ሐዋርያዊት “ኢትዮጲያና ኤርትራ”
      ሐዋርያዊት ግብጽ
      ሐዋርያዊት ሶርያ
      ሐዋርያዊት አርመንያ
      ሐዋርያዊት ህንድ

“በድንዃንህ ለዘላለም ልኑር በክንፍህም ልጠለል”
መዝ 60: 4



 ቤተክርስቲያንና // ፈተናዎቿ

+++ የመናፍቃኑ ፈተና፦ መናፍቃኑ ቤተክርስቲያን አያስፈልግም የእኛ ሰውነት ራሱ  ቤተክርስቲያን ነው ይላሉ። ነገር ግን ጌታ በወንጌል ላይ እንዲህ አለ፤
ቤትየ ቤተ ጸሎት ትሰመይ // ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ማቴ 21:13

+++ የምንደኛ ልጆቿ ፈተና፦ ምንደኛ የሚባሉት ለቤተክርስቲያን ታምኝ ያልሆኑ ልጆቿ ናቸው፤ ሰው እናቱን በገንዘብ ይሸጣል እንዴ? እስከ ዛሬ አልተሰማም; ይሁዳ ብቻ ጌታውን በገንዘብ እንደለወጠ ተጽፏል። ይሁዳ ማለት ታማኝ ማለት ነበር; ነገር ግን እንደስሙ አልታመነም፤ እናቱን ቤተክርስቲያንን በገንዘብ የሚለውጥም ዳግማዊ ይሁዳ ይባላል። አንዳንዶቹ እኛ በሰለጠ አለም ነውና ያለነው ቤተክርስቲያን ትታደስ ይላሉ; በራዕ 15:3 ላይ የሰማይ መላእክት ሱራፌል የዘመሩበት በገና ይቅርና ኦርጋን ይሁን ይላሉ; በውጭው አለም ያሉ አንዳንድ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያንም ግማሹ ባለማወቅ ሌላውም እያወቀ አሜን ብለው ተቀብለዋል፤ መንፈስ ቅዱስ ይታደሳል እንዴ ቤተክርስቲያንን እናድሳት የሚሉት? የተፈጥሮ ሳይንስ dynamic ነው ይሻሻላል; ቤተክርስቲያን ግን ትላንትም ዛሬም ነገም አንዲትና ሐዋርያዊት ናት!!!


+++ ቤተክርስቲያንን መሳለም፦ አንዳንድ ሰዎች ቤተክርስቲያንን በእጃችን እያበስን ስንሳለም ሊገርማቸውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ እንደሆነ አድርገው ሊቆጥሩ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከድንኳኑ ጀምረህ በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳትን በሙሉ ቅብዓ ቅዱስ ወይም ሜሮን ቀባና ቀድሳቸው እነሱን የነካም ቅዱስ ይሆናል። ዘጸ 30:22 እኛም የቤተክርስቲያንን ዘርፍ በእምነት የምንዳስሰው በዚህ ምክንያት ነው። 12 አመት ሙሉ ትደክም የነበረችው ሴት እምከመ ገሰስኩ ጽንፈ ልብሱ አሀዩ /በእምነት ሆኜ የልብሱን ዘርፍ ብዳስስ እፈወሳለሁ/ ብላ እንደዳነችው እኛም በእምነት የቤተክርስቲያንን ዘርፍ ብንዳስስ እንፈወሳለን። ጌታ የቤተክርስቲያን ራስ ነውና የልብሱ ዘርፍም ቤተክርስቲያን ናትና!!! ኤፌሶን 1:22

+++ ቤተክርስቲያን ከሙሴ እስከ አዲስ ኪዳን፦ በነሙሴ ዘመን ህንጻ ቤ/ተ/ክ ስላልነበረ ህዝቡ ይገናኝ የነበረው በድንኳን ውስጥ ነበርና የመገናኛ ድንኳን ይባል ነበር። ለመጀመሪያ ግዜ ህንጻ ቤተክርስቲያንን የሰራው ንጉስ ሰለሞን ሲሆን ይህ 46 አመት የፈጀው ቤ/ተ/ክ በአሁኑ ግዜ መስጊድ ተሰርቶበታል!! ከሰለሞን በመቀጠል ዘሩባቤልና ንጉስ ሄሮድስ ሰርተዋል። ከስደት መልስ እነ ሰለሞንንና ዘሩባቤልን ቤቱን እንዲሰሩ የረዳ እኛንም በስደት ሃገር ቤተ መቅደሱን እንድንሰራ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን ፤ አሜን



እኔ ከዝግባ በተሰሩ ቤተመንግስቴ እየኖርኩ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል። 2ኛ ሳሙኤል 7:2 ፤ ዳዊት ስለእኛ የተናገረው አይመስላችሁም? ምን አልባት እኛ በተመቸ ቤት እንኖር ይሆናል; የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል።

ህዝቤ ሆይ በርታ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ቤተ መቅደሴን ስሩ”
ትንቢተ ሐጌ 1: 7


ስሜ ለዘለአለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጫለሁ ቀድሻለሁም፤ በቤቴ የሚጸለየውን ጸሎት ዓይኖቼ ያያሉ ጆሮዬም ያደምጣሉ።

2ኛ ዜና 7: 15
በቅድስናው ስፋራ ለእግዚአብሔር ስገዱ
መዝ 28:2
አንተን በመፍራት በመቅደስህ እሰግዳለሁ
መዝ 5:7
ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንሂድ ሲሉኝ ደስ አለኝ
መዝ 121(122):1
እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት
መዝ 150:1
ከተቀደሰው መቅደስህ በረከትን እንጠግባለን
መዝ 64(65):4
ለአይኖቼ መኝታ ለሽፋሽፍቴም ረፍት አልሰጥም ለእግዚአብሔር ስፍራ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ብዬ
መዝ 131:3
የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ መቅደሱ አምጥታቹ ቤተ መቅደሱን ስሩ

1ኛ ዜና 22:19
እግዚአብሔር ለዘላለም ወደ ቀደሰው መቅደሱ ኑ
2ኛ ዜና 30:8
አቤቱ በተቀደሰው መቅደስህ የልመናን ከንፈር ስማ የንስሐን እንባንም ተቀበል
2ኛ ዜና 6:36

ቤቴ ለህዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል

ኢሳ 56:7

እለት እለት የሚያስጨንቀኝ የቤተክርስቲያን  ጉዳይ ነው

2ኛ ቆሮ 11:28
ዋዕናቅጸ ሲኦል እይሔይልዋ //
የሲኦል ደጆች አይችሏትም

ማቴ 16:18


+++ መዝሙር እንዘምር፦
ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሠላም ላንቺ ይሁን
ሐዋርያዊት የወደዱሽ ጴጥሮስ ወጳውሎስ (2)
ሥብሐት ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ
እናመስግን በአንድነት በቤቱ ሆነን
እንፀልይ በአንድነት ለቤተክርስቲያን

ወ    ሥ    በ    ሐ    ት     ለ    እ    ግ    ዚ    አ    ብ    ሔ    ር

/ተክለ መድህን/