Saturday, 26 November 2011

እንተዋወቅ // ስም፦ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ እባላለሁ



















 
                        እንተዋወቅ

                            ስም፦ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ እባላለሁ
                            ሀገር፦ መንግስተ ሰማያት
                            ዜግነት ፦ ክርስቲያን
                            ስራ፦ እግዚአብሔርን አመልካለሁ










+++ ቤተክርስቲያንና ቅ/ጳውሎስ፦ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ ለቤተክርስቲያን እጅግ ይቀና የነበረ ሐዋርያ ነው። ቅ/ጳውሎስና ቤተክርስቲያን የአንድ ዕርግብ ሁለት ክንፍ እንደማለት ናቸው!! ሁለቱም አይለያዩምና; በቀዝቃዛ እስር ቤት እያለ ቅ/ጳውሎስ ያስብ የነበረው ለቤታክርስቲያን ነበር። አብዛኛውን መልዕክታቱንም የፃፈው ከምድር በታች ባለች ቀዛቃዛ እስር ቤት ውስጥ ነበር።  2ኛው የጢሞቴዎስ መልዕክት የተፃፈውም በቀዛቃዛዋ እስር ቤት ነበር!!!









ቅዱስ ጳውሎስ መልእክታቱን የጻፈባቸው ቀዝቃዛ እስር ቤት ይህን ይመስላል;
 ልእ እንደ ለንደን ባቡር መሄጃ / /under ground/ ሲሆን ካታኮምቦ /ግበበ ምድር/ ይባላል።







+++ ሐዋርያዊ ስራዎቹ፦ ይህ ታላቅ ሐዋርያ ከሐዋርያት ሁሉ ብዙ መንገድ በእግሩና በባህር በመጓዝ የደከመና በጉዞው ህይወቱን ለአደጋ ያጋለጠ ሲሆን ለአህዛብ ወንጌልን ለመስበክ በመመረጡ 16 መልዕክታትን ጽፋል፤ ሁለቱ ጠፍተው በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው 14ቱ መልዕክታቱ ናቸው።

ታላቁ ሐዋርያ መልዕክታቱን እየፃፈ

+++   ዕውቀትን ከትህትና ጋር ደርቦ የያዘ ነበር፦ በእየሩሳሌም በሚገኘው በታላቁ የአይሁድ ት/ቤት ከሊቁ ከገማልያል እግር ስር ቁጭ ብሎ ብሉይን የተማረና አዲስ ኪዳንን አበጥሮ የሚያቃት ቢሆንም በእውቀቱ አልተመካም፤ እኔ ጭንጋፍ ነኝ እስከማለትም ደርሶ ነበር። 
1ቆሮ. 15:8

+++ ሥራ ወዳድ ነበር፦ ሌት ተቀን በወንጌል ቢደክምም ለምዕመናን እንዳይከብዳቸው ድንኳን እየሰፋ እራሱን ይችል ነበር!!!

+++ እጅግ ትዕግስተኛ ነበር፦ ብዙ ግዜ ቢታሰርም በረሃብ ቢደክምም መልዕክቱን በትዕግስት ሆኖ  በደስታ ይጽፍ ነበር፤ በጌታ ደስ ይበላቹ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላቹ እያለ በመልዕክቱ ያጽናና ነበር። 

+++ ተግባቢ ነበር፦ ቅ/ጳውሎስ ሰውን እንዴት መቅረብ እንዳለበት ያውቅ ነበር። ከተራ ሰዎች እስከ ነገስታት በፍቅር እየሳበ ክርስቲያን አድርጓል። በመልዕክቱ መጨረሻ የቤተክርስቲያንን ልጆች ስም እየጠራ ሰላምታ ማቅረብ የዘወትር ተግባሩ ነበር።

+++ ጥበበኛ ነበር፦ የቤተክርስቲያን አበው ቅ/ጳውሎስን መዶሻ ይሉታል። መዶሻ ማዕድናቱን ቀጥቅጦ አንድ እንደሚያደርግ ሐዋርያውም አህዛብንና ሕዝብን/እስራኤል ዘሥጋን/ አንድ ስላደረገ ነው።  በጉዞው ቲቶንና በርናባስን አስከትሎ ነበር; ቲቶ ግሪካዊ አህዛብ ሲሆን በርናባስ ደግሞ አይሁዳዊ ነበር። 

+++ በመጀመሪያ የቤተክርስቲያን አሳዳጅ ነበር፦ ቅ/ጳውሎስ በ32 አመቱ ክርስቲያንን ለማጥፋት ከሊቀ ካህናቱ ቀርቦ የፍቃድ ደብዳቤ ከተቀበለ በሗላ የሶርያ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ደማስቆ ሊደርስ ጥቂት ሲቀረው ነበር ከሰማይ የወረደው ብርሃን አካባቢውን ሞላውና “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ የሚል ድምጽ የሰማው። በመቀጠልም ለሐዋርያነት ተጠራ።

     +++ ታላቅ ሰማዕትነትን ተቀብሏል፦ በዘመኑ የነበረው ጨካኙ ንጉስ ኔሮን በጥጋቡ የሮማ ከተማ ስትቃጠል ማየት እፈልጋለሁ ብሎ አቃጠላት; የሮም ሕዝብ በክርስቲያን ላይ አሳበቡ፤ በዚህም ክርስቲያኖች ሰማዕት መሆን ግድ ሆነባቸው። ቅ/ጳውሎስም ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር በጨለማ እስር ቤት ታስሮ ከቆየ በሗላ በ74 ዓመቱ በሮማ ከተማ በኦስትያ መንገድ አንገቱን ተሠይፎ ሐምሌ 5 67 ዓ.ም በሰማዕትነት ዐረፈ።
   

“ሩጫዬን ፈጽሜያለሁ ሐይማኖቴን ጠብቄያለሁ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” 2ኛ ጢሞቴዎስ 3:4


የእግዚአብሔርን ቃል የተናገራችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ; የእምነታቸውንም ፍሬ እየተመለከታቹ በህይወታቸው ምሰሏቸው ዕብራዊያን 13:7። ታላቁ ሐዋርያ ቅ/ጳውሎስ እንዲህ እንዳለው መላው ህይወቱ ትምህርት ትሁነን፤ አሜን።

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሌላ ሐዋርያ በቅርቡ ሊተዋወቀን ይችላል!!  ማን ይሆን? ቅ/ ጴጥሮስ ወይስ ቅዱስ ዩሐንስ ወይስ ማን?  ይቆየን
ወ   ሥ   በ   ሐ   ት   ለ   እ   ግ   ዚ   አ   ብ   ሔ   ር

/ተክለ መድህን/


“The Honour & the Gifts of Righteous in the Bible” // “ክብረ ቅዱሳን በመፅሐፍ ቅዱስ”

“The Honour & the Gifts of Righteous in the Bible”

“ክብረ ቅዱሳን በመፅሐፍ ቅዱስ”



በመፅሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ስለ ፃድቃን እየደጋገመ ይመሰክራል እነሆ ለበረከት፦

v   ነብዩ ኤልያስና ኤልሳዕ፦  ታላቁ ነብይ ኤልያስና
    ደቀመዝሙሩ ኤልሳዕ እግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ሰቷቸው ታላቅ ተዓምራትን ይሰሩ ነበር ፤ ኤልያስ የሰራብታዋን ልጅ ከሞት ሲያስነሳ ኤልሳዕ ደግሞ የሱናማዊቷን ልጅ ከሞት አስነሳ       በመፅሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ግዜ የሞተን ያስነሳው ታላቁ ነብይ ኤልያስ ነው። ነብዩ ኤልሳዕ ደግሞ በህይወት እያለ የሱናማዊቷን ልጅ ከሞት አስነሳ; ከሞተ በሗላ ዓፅሙ የሞተውን ቢነካው የሞተው ተነሳ! 2ኛ ነገስት 13:21 
“ጻድቃን ሰማዕታት በሙሉ; በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉ; ከፈጣሪ አማልደው ምህረት ያሰጣሉ”



v   ደጉ አብርሐምና ፃድቃን፦ ደጉ አብርሐም ሰዶም እንድትማር ለመነ፤ 50
ጻድቃን በፊትህ ቢገኙ ስለፃድቃን ስትል ለከተማይቱ ምህረት ታደርጋለህን? ብሎ ተማጸነ; ጌታም ምህረት እንደሚያደርግ ነገረው፤ ከተማይቱ በጻድቃን ደህይታ እንዃን 50 ቀርቶ 5 ጻድቅ ታጣ። የጻድቃን ደሃ ሃገርም አገኛታ መከራ። ዘፍ 18:22
* ስለ አብርሐም የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሐም እሰውራለሁን?” ዘፍ. 18:17
* ንጉስ አቤሜሌክ የአብርሐምን ሚስት ሲወስድ ከጥፋትህ ተመለስ እኔም እምርሃለሁ ማለት ሲችል ለአቤሜሌክ እግዚአብሔር እንዲህ አለው ነብይ ነውና ይጸልይልሃል አንተም ትድናለህ ዘፍ20:7; ኢዮብን ጓደኞቹ ቢያሳዝኑት እግዚአብሔር ለኢዮብ ጓደኞች /በልዳር ሳፎርና ኤልፋዝ ለተባሉት ጓደኞቹ / እንዲህ አላቸው ነብይ ነውና ይጸልያል እኔም ጸሎቱን እቀበላለሁ ኢዮብ42:7። ባለቤቱ እግዚአብሔር ጸሎቱን እቀበላለሁ እያለ መናፍቃኑ አትቀበልም ካሉ ከሰው ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር መከራከር ይሆንባቸዋል።  

v   ነብዩ ሙሴና ጻድቃን፦ ነብዩ ሙሴ ከሲና ተራራ ላይ የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዞ
ሲወርድ እስራኤላዊያን ጣኦትን ያመልኩ ነበር; እስራኤል ዘሥጋ ፍቁረ ጣኦት ብዙ ግዜ ስላሸነፋቸው እግዚአብሔር ለሙሴ ይህ ህዝብ አንገተ ደንዳና ነውና አንተን በሌላ ሕዝብ ላይ እሾምሃለሁ አለው; ሙሴ ምን አለ “ሕዝቡን ከምታጠፋ ስሜን ከህይወት መጽሐፍ ደምስስ” [ዘፀ 32:32] ዳዊትም በመዝሙሩ “የተመረጠው ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባይቆም ኖሮ እስራኤላዊያንን ባጠፈቸው ነበር አለ” መዝ 105:23። በፊቱ ባይቆም ኖሮ ማለቱ ቀጥ ብሎ መቆም ሳይሆን የሙሴን ታላቅ ልመና ለመግለጽ ነው። እግዚአብሔርም ለህዝቡ ምህረት አድርጎ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈበት ታቦት ለሙሴ በድጋሚ ተሰጠው።
* ሙሴንና አሮንን ተቃወመው ራሳቸውን እንደካህን የቆጠሩ ቆሬና 250 ሰዎች በአንድ ቀን በእሳት ተቃጥለው ሞቱ; እነሱን የተባበሩ ዳታንና አቤሮን ደግሞ ምድር ተከፍታ ዋጠቻቸው። ዘሁልቅ 16:31-36 ፤ ሲነጋም እስራኤላዊያን ህዝቡን አስገደላቹ ብለው በድንጋይ ሊወግሯቸው ተነሱ; ሙሴና አሮን ወደ ደብተራ ኦሪት ሸሹ። እግዚአብሔርም አምደ ብርሐን ከልሎ አዳናቸውና ሁለቱን ወንድማማቾች ከእስራኤላዊያን ማህበር ፈቀቅ በሉ; በቅስፈት አጠፋቸዋለሁ ብሎ በአንድ ቀን 14ሺ 700 ሰዎች ሞቱ። አሮን ልብሰ ተክህኖ ለብሶ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ ቢጸልያላቸው መቅሰፍቱ ተወገደ ዘሁ.16:41
*የተመረጠው ሙሴ በፊቱ ባይቆም ኖሮ በመቅሰፍቱ ባጠፋቸው ነበር ይላል; መዝ 105:23።
(ማክበር ለበረከት አለማክበርም ለመቅሰፍት ነውና)
/ቀጣዩን ገጽ ይመልከቱ/
*ነብዩ ኤልያስን አላከብር ያሉት ሁለት የ50 አለቆች በነብዩ ጸሎት ከሰማይ በወረደች እሳት ተቃጥለው ሞቱ። 2ኛ ነገ. 1:9

* የሙሴ ወንድም አሮንና እህቱ ማርያም ሙሴን ሲቃወሙ ማርያም በለምጽ ተመታች ሙሴ ቢጸልይ ዳነች። ዘሁ. 12:10

+++ ክቡር ዳዊትና ጻድቃን፦ ዳዊት በገናውን እየደረደረ እንዲህ አለ፦ የእግዚአብሔር አይኖቹ ወደ ጻድቃን ጆሮዎቹም ወደ ልመናቸው ናቸው። ዳዊት እንዲህ ብሎ የዘመረውን እኛ ባንሰማ እንዃን ዳዊት የዘመረባት በገናም ትታዘበናለች; የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከመረጥኩት ጋር ኪዳን ገብቻለሁ ፤ ኪዳኔን አላፈርስም ከአፌ የወጣውንም አላጥፍም መዝ88:3 ፤ 88:34 ፤ ስለ ራሴና ስለባሪያዬ ስለዳዊት ስል ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ 2ኛ ነገስት 19:34 ፣ 20:6

+++ ጠቢቡ ሰለሞንና ፃድቃን ፦ አባት “የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል” ሲል ልጅ ደግሞ “በረከት በፃድቅ ራስ ላይ ነው” እያሉ አባትና ልጅ መሰከሩ ፤ ጌታችንም ቀዝቃዛ ውሃ በፃድቅ ስም የሚያጠጣ ቢኖር ዋጋው አይጠፋበትም እንዳለ
መዝ 111 ፣ ምሳሌ 10:6 ማቴ 10:40

+++ ነብዩ ኢሳያስና ፃድቃን፦ ኢሳያስ ከ700 መቶ አመት በፊት ድንግል በድንግልና ትጸንሳለች ብሎ ቢተነብይ የዘመኑ ሰዎች ሥጋውን በመጋዝ ለሁለት ሰንጥቀው ሰማዕትነትን ተቀበለ ፤ ስለ ጻድቃን በታላቁ ነብይ ትንቢት እንዲህ ይላል፦    ቃልኪዳኔን ለሚጠብቁ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከሴቶችና ከወንዶች የሚበልጥ
ዘላለማዊ ስም እሰጣቸዋለሁ; ኢሳ. 56:4 ቤተክርስቲያን በጻድቃን ስም የምትሰየመውም በዚሁ ምክንያት ነው።   
+++ ሐዋርያው ጴጥሮስና ጻድቃን ፦ እግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ ለቅዱሳኑ ሰቷቸው ድንቅ ተዓምራትን ይሰሩ ነበር። ቅ/ጴጥሮስ ጥላው ድውያንን ሲፈውስ ቅ/ጳውሎስ ደግሞ የልብሱ ቁጨት አጋንንትን አወጣ የሐዋ.5:15 ፤ 19:12
የጌታ አይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ ጆሮዎቹም ወደ ልመናቸው ናቸው። 1ኛ ጴጥ 3:12

“በሐዋርያት ሥራ 19:14 ያለውን ግሩም ታሪክ እንዴት ይገርማል!”

+++ ሐዋርያው ዩሐንስና ጻድቃን፦ የሮማ ወታደሮች ፖሊካርፐስ የተባለ የሐዋርያው ዩሐንስ ደቀመዝሙርን አምላኩንና ሐይማኖቱን እንዲክድ አስገደዱት; ይህን የሰሙ ክርስቲያኖች በአፍህ ብቻ ካድ እኛ ለምን እንደዚህ እንደምትል እናውቃለን ብለው ፖሊካርፐስን መከሩት፤ ፖሊካርፐስ ግን ጌታዬ አንድም ቀን አልካደኝም እኔስ ለምን እክደዋለሁ ብሎ መለሰላቸው; የሮማ ወታደሮችም ፖሊካርፐስን በእሳት አቃጥለው ሰማዕትነትን ተቀበለ።
በእስያ የመጀመሪያው ሰማዕት የሆነው አንቲጳስ ደጎሞ በነድምጥያኖስ ዘመነ መንግስ በነሃስ መጥበሻ ተጠብሶ ሰማዕትነትን ተቀበለ። ራዕ 2:13 

+++ ሐዋርያው ያዕቆብና ፃድቃን፦ ያዘነ ቢያር ይጸልይ; ደስም ያለው ይዘምር ፤ የታመመ ቢኖር የቤተክርስቲያንን ቀሳውስት ይጥራና ዘይት
 /ቀንዲል; ቅብዐ ፈውስ/ ቀብተው ይጸልዩለት የእምነት ጸሎት ድውዩን ይፈውሳል
“የፃድቅ ሰው ጸሎት ሐይልን ታደርጋለች ግዳጅንም ትፈጽማለችና” ያዕቆብ 5: 13-16
/ቀጣዩን ገጽ ይመልከቱ/
+++ ሐዋርያው ጳውሎስና ጻድቃን፦ ስለ ፃድቃን ሰማእታት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእብራዊያን መልእክቱ በተከታታይ ምዕራፍ ላይ ይናገራል። /እብራዊያን ምዕራፍ 11; 12 እና 13/

+++ እብራዊያን 11:34፦ አለም ለነሱ አልተገባቸውምና በየበረሀው በየዋሻው ተንከራተቱ።

ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ ጻድቃን በየበረሃው ተንከራተው እንዳለፉ ነገረን; አሁንም በሀገራችን በየገዳሙና በበረሐው ጤዛ ልሰው ዳዋ ጥሰ ዋእይ ቁሩንም ታግሰው ለሃገር ለህዝብ የሚፀልዩ አበው አሉን። ሃገራችን ብትታረስ ብዙ ጻድቃን የሚበቅሉባት ቅድስት ሃገር ናትና። መናፍቃን ግን ገዳማዊ ህይወትን ይቃወማሉ; ታላቁ ሐዋርያ ግን በመልክቱ አለም ለፃዳቃን እንዳልሆነች ነግሮናል።
+++ እብራዊያን 12:1፦ ብዙ ምስክሮች በዙሪያችን አሉን።
ሐዋርያው ሰማእታትን ምስክሮች አላቸው; ሰማ መሰከረ ሰማእትነት ምስክርነት ማለት ነው።
በእብራዊያን 11:37 ላይ እነ ነብዩ ኢሳያስ በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቀው ሰማእትነት እንደተቀበሉ ገለጸና እነዚህ ሁሉ ምስክሮች /ሰማእታት/ በዙሪያችን አሉ አለን።
በነፍሳቹ ዝላቹ እንዳትወድቁ የጸናውን አስቡ; እብራዊያን 12:3; ሐዋርያው የጸኑትን ሰማእታትን እንድናስብ ይመክረናል።

የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፤
   የእምነታቸውንም ፍሬ እየተመለከታቹ በሕይወትቸው ምሰሏቸው። እብራዊያን 13:7
                                   
 ብዙ ግዜ የወደቀውን ነው የምንመስለው ነገር ግን የጸኑትን እነ ነብዩ ኢሳያስን እነ
አባ ተክለ ሐይማኖትን; አቡነ አረጋዊንና ሰማእቱን ቅዱስ ጊዮርጊስን እያሰብን በተጋድሎዋቸው መምሰል ቢሳነን የእምነታቸው ፍሬ እየተመለከትን የጸኑትን መምሰል እንዳለብን ይመክረናል።
“አስቀድሞ የመረጣቸውን ጠራቸው የጠራቸውንም አከበራቸው” ሮሜ 8:30 ፤
 እኛም ያከበራቸውን ክብር ሰጠናቸው። እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስ ማን ነው? ሮሜ 8:33

“የዚህን ዓለም ተውና መላዕክትን እንኳን እንድንገዛ አታውቁምን?”[1ኛ ቆሮ. 6:3]

“ተክለሐይማኖት ፀሎቱ ወበረከቱ የሃሉ ምስሌነ ለዓለም ዓለም አሜን”


+++ ብርሐንና ጻድቃን፦

እኔ የአለም ብርሐን ነኝ ያለው ጌታ ጻድቃንንም አንትሙ ብርሐኑ ለዓለም/እናንተ የአለም ብርሐን ናችሁ አላቸው/ እስቲ ጥያቄ እናንሳ በሳይንሱ ጨራቃ የራሱ የሆነ ብርሃን አለው እንዴ? የለውም ነገር ግን ከፀሐይ reflect ወይም አንጸባርቆ በለሊት ያበራልናል፤ ፃድቃንም ፀሐይ ከሆነው ጌታ ለጨለማዋ አለም ያበራሉ ማለት ነው። በጨለማ ክፍል ያለን ሻማ ብርሃን እንደሚሰጠን እያወቅን ግን ብናጠፋው ጨለማ የሚበረታብን በኛ ላይ ነው ፤ መናፍቃንም ጻድቃንን ቢቃወሙ ጨለማው የሚበረታው ባጠፉት በራሳቸው ላይ ይሆናል ማለት ነው። 

/ቀጣዩን ገጽ ይመልከቱ/
“9ኙ ቅዱሳን”


አባ አረጋዊ                 አባ አፍፂ
   አባ አሌፍ                  አባ ሊቃኖስ
አባ ፅህማ                  አባ ገሪማ
               አባ ይምዓት               አባ ጰንጠሌዎን ናቸው።
                    አባ ጉባ



+++ የመናፍቃኑ ጥያቄ ስለ ፃድቃን፦ መናፍቃኑ ጻድቃን በአካለ ሥጋ እያሉ ያማልዳሉ መፅሐፍ ቅዱስ መስክሯልና ለመካድም አይመችም ነገር ግን እንዴት በአካለ ነፍስ ሆነው ያማልዳሉ ብለው ይጠይቃሉ፤ የኤላሳዕ ዐጽም የሞተን እንዳስነሳ አይተናል ይህ ብቻ በቂ ነበር፤ ለሚጠይቁን ግን ቤተክርስቲያን ሃገረ ጥበብ ናትና ብዙ መልስ አላት። ጌታችን ለፈያታዊ ዘየማን እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከእኔ ጋር “በገነት ትኖራለህ” አለው [ሉቃስ 23:43] በገነት ትኖራለህ የሚለው ቃል ፃድቃን በገነት ሕያው ሆነው ዓለምንና እኛን ስለሚመለከቱ ነው፤ ለምኑልን ስንላቸውም ስለ እኛ ይለምናሉ። እንዴት እንደሚለምኑ ማየት ትፈልጋለህ?  በጣም ይገርምሃል መፅሐፍ ቅዱስ ላይ በገነት ያሉት ፃድቃን ቀርተው በሲኦል ያለ የሃጥዕ ነፍስ እንዃን በምድር ላሉት ወንድሞቹ ሲለምን እናገኛለን። በሲኦል ያለው ሃጥኡ ነዌ በምድር 5 ወንድሞች አሉኝና እባክህን ወደዚህ እንዳይመጡ አላዛርን ላክልኝ እያለ ለመነ [ሉቃስ 16:19] በሲኦል ያለው ሃጥኡ ነዌ ስለወንድሞቹ ከለመነ በገነት ያሉት ፃድቃንማ እንዴት ስለእኛ አብልጠው አይለምኑ? እኛስ በወንጌሉ የተፃፈውን አምነን እናነባለን እንጂ አንብበን አንክድም። 

መላዕክትን በአርያም; ሐዋርያትን በአጽናፈ ዓለም  

ጻድቃንን በገዳም; ሰማዕታትን በደም ያጸና

 እኛንም በቀናችው በተዋሕዶ ኦሮቶዶክስ እምነታችን ያጽናን

ወ   ሥ   በ   ሐ   ት   ለ   እ   ግ   ዚ   አ   ብ   ሔ   ር

ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፤ አሜን
የእግዚአብሔር ቸርነት
 ከሃገራችን “ከኢትዮጲያና - ኤርትራ” አይለይ አሜን!
[ተክለ መድህን]



















“ማዕርጋተ ቅዱሳን”

“ማዕርጋተ    ቅዱሳን”





ቅዱሳን በተጋድሎ የሚያገኙት ማዓረጋት አሉ፤ እነሱም አሥሩ ማዕርጋተ ቅዱሳን በመባል ይታወቃሉ። ከወጣንያን እስከ ፍፁማን በቅደም ተከተል እነሆ ለበረከት ፦ 


[1ኛ] ጽማዌ፦ ጽማዌ ማለት ሕሊናን ለእግዚአብሔር ብቻ ለማስገዛት ዝም ማለት ነው። አንደበት እሣት ነው ስለሚል እነ አጋቶን ከአፋቸው ክፉ እንዳይወጣ ድንጋይ ጎርሰው ዝም ብለው ነበር [ያዕቆብ 3:6] አባቶችን ስናይ የሰላምና የፀጥታ መንፈስ የምናይባቸው በዚህ መዓረጋቸው ነው።  


[2ኛ] ልባዌ ፦ ልባዌ ማለት ማስተዋል ማለት ነው። በዚህ መዓረግ የደረሱ አባቶች መላዕክት ሲወጡና ሲወርዱ ያያሉ።


[3ኛ] ጣዕመ ዝማሬ፦ የሚዘምሩትንና የሚፀልዩትን ማር ማር እያላቸው በማጣጣም የሚያመሰግኑበት መዓረግ ነው። ሲዘምሩ እንደ ዳዊት የንግስና ካባቸው እየወለቀ ይዘምራሉ፤ እኛስ? ብዙ ፀሎት ቢፀልዩም በእግዚአብሔር ፊት እንደቆሙ ስለሚያውቁ በእሣት ዳር እንደቆመ ሰው ሕሊናቸው አይባዝንም፤ እኛ አንድ አባታችን ሆይ ስንፀልይ ሕሊናችን ስንት ግዜ ይባዝን ይሆን? አንድ ታላቅ ባህታዊ አቡነ ዘበሰማያት ብቻ እያለ ለብዙ ዘመናት ይጸልይ ነበር፤ መልዐክ ተገልጦ ይትቀደስ ስምከ በል እንጂ አለው፤ ባሕታዊውም አባታችን ሆይ የሚለውን ቃል ጣዕሙን እንደ ማር መቼ በአፌ ጠገብኩት አለ ይባላል።


[ቀጣዩን ገጽ ይመልከቱ]
[4ኛ] አንብዕ፦ ስለ ራሳቸው ሃጢአትና ጌታችን ስለተቀበለው መከራ፤ ስለ እመቤታችን ስደት እያሰቡ እንደ ሰን ውሃ የሚያለቅሱ ቅዱሳን ናቸው። ሐዋርያው ዩሐንስ ጌታን በመስቀል ላይ ካየበት ቀን ጀምሮ ያለቅስ ነበር፤ ፊቱ በሃዘን የተሞላ በመሆኑ ስሙ “ቅዱረ ገጽ ሐዋርያ” ተብሏል። ቅ/አርሳንዩስ አብዝቶ በማልቀሱ በፊቱ ላይ የእንባ መውረጃ ምልክት ነበረው። ዳዊት አልጋዬን በእንባዬ አጥባለሁ ማለቱ የእንባውን ብዛት ሲነግረን ነው [መዝ 6:6]


[5ኛ] ኩነኔ፦ በማዕርጋት ሂደት ኩነኔ ማለት ሥጋን ለነፍስ ማስገዛት ማለት ነው።   ሰው ሥጋና ነፍስ የሚዋጉበት የውጊያ ከተማ ነው፤ ሥጋ ሲያሸንፍ ነፍሰ ገዳይነት; ዘማነት; ጥላቻ; ቅናት; ስካር ይነግሳሉ። ነፍስ ስታሸንፍ ሥጋን ታዘዋለች፤ ስገድ ፁም ፀልይ ስትለው ይታዘዛል። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ፍቅር ሰላም ትዕግስት ሁሉ ገንዘብ ይኾናሉ[ገላትያ 5:22] 


 [6ኛ] ፍቅር፦ ፍቅር ማለት እግዚአብሔር ሊፈጥር ያልናቀውን ፍጥረት ሁሉ መውደድ ፤ የሚወዱንን መውደድ ብቻ ሳይሆን የሚጠሉንንም መውደድ መቻል ማለት ነው። ቅዱሳን መናፍቅ ክርስቲያን ሳይሉ ሰውን ሁሉ ይወዳሉ፤ ይህም “ፍቅረ ቢጽ” ይባላል። ዘር ተራራ ሸለቆ በቅዱሳኑ ዘንድ ቦታ የለውም፤ በዓለም ዘንድ ሗላ ቀርነት ነው፤ በክርስቲያን ዘንድ ደግሞ የሗላ ቀርነት መጨረሻ ነው። ሃገራችን በሰማይ ነው እንዳለ [ፊሊጲስዩስ 3:20]


[7ኛ] ሑሰት፦ ቅዱሳን በአንድ ሃገር ሆነው በሌላ ሃገር የሚደረገውን የማወቃቸው ማዕረግ ሑሰት ይባላል። ለምሳሌ ኤልሳዕ በኢየሩሳሌም እያለ የሶርያው ንጉስ ወልደ አዴር በቤተ መንግስቱ ምን እንደሚማከር ያውቅ ነበር።
 [2ኛ ነገ. 6:8]  [ቀጣዩን ገጽ ይመልከቱ]


[8ኛ] ንጻሬ መላዕክት፦ ቅዱሳን በዓለም ላይ ሆነው በሶስቱ የመላዕክት ከተሞች [በኤረር በራማ በኢዮር] መላዕክትን የማየታቸው ማዕረግ ነው።  


[9ኛ] ተሠጥሞ ብርሃን፦ የብርሃኑ መዓዛና ጣዕም ነፍስን ከሥጋ እለይ እለይ በሚያሰኝ በብርሃን ባህር ሲዋኑ ማደር ማለት ነው።


 [10ኛ] ከዊነ እሣት፦ ከዊነ እሣት የማዕረጋት መጨረሻ ነው፤ በዚህ ማዕረግ የደረሱ ቅዱሳን  ሰውነታቸው አጋንንትን እንደ እሣት የሚያቃጥልና የማያስቀርብ ይሆናል።  በአንድ ወቅት ቅ/ጳኩሚስ በአንዲት ሴት ላይ ብዙ አጋንንት ሰፍሮባት አየ፤ ይህን ግዜ ጌታዬ  ሆይ ይህን ሁሉ አጋንንት እንዴት ትችለዋለች ብሎ አጋንንቱ ወደ እሱ እንዲተላለፉ ለመነ፤ ይህን ግዜ አጋንንቱ ወደ እሱ ገቡ፤ ቅ/ጳኩሚስ በፀሎቱ ብዛት መቀመጫ ቢያሳጣጨው በእሳት ተቃጠልን እያሉ እየጮሁ ወተዋል። ቅ/ ባስልዮስም ለዚህ ማዕረግ በመድረሱ ተዋስያን በሰውነቱ ላይ ሲያርፉ እሳት ውስጥ እንደገቡ ተቃጥለው ሲወድቁ ቅ/ኤፍሬም አይቷል።


የእነ ተክለሐይማኖት ገድል ሲነበብ አጋንንቱ የሚጮሁት በዚህ ከዊነ እሣት ማዕረጋቸው ነው።
                                    

ወ  ሥ  በ  ሐ  ት  ለ  እ  ግ  ዚ  አ  ብ  ሔ  ር

 [ተክለ መድህን]