“ሽሮን ሲሸውዷት ፕሮቲን ነሽ አሏት!”
ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ ታሪክ ላውጋችሁ!
አንዲት የሰፈር ጓደኛዬ ፀጉሯን ምን ውስጥ እንደምትነክረው አላውቅም ብቻ ዘመናዊ ነኝ ለማለት እንደ ቀስተደመና በየቀኑ የፀጉሯን ቀለም ትቀያይረዋለች፤ ሰኞን ስለማትወደው ጥቁር ቀለም፣ ማክሰኞን አረንጓዴ፣ እሁድን ሰማያዊ ቀለም እያለች ትዘምንብን ጀመር። ከፀጉር ቀለሟ ጋር የሚሄድ ጥብቅብቅ ያለ ሱሪ ትለብስና ጫማዋዋን ትጫማና ከላይ የልጅነቷ የሚመስለውን ጃኬት ጣል ታደርግና በቃ! ከተሜውን ታዳርሳለች!
የሰፈራችን የአቶቢስ ተራ እማ ወራዎችም እንዲህ የሚል ግጥም ገጠሙላት፦
አየን አወራነው የፀጉርሽን ነገር
ትንሿን ኮትሽን ለትንሿ ልጄ ብትሰጪያት ትፀድቂ እኮ ነበር!
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
ይህች አንዲት ፍሬ ልጅ በፈረንጅ ተገዝታ ትዝናናብን ወይ!
ከዚህች የልጅነት አብሮ አደጌ ጋር አፈር ፈጭተን ውኃ ተራጭተን ነውና ያደግነው የሆድ የሆዳችንን ሳንደባበቅ እንጨዋወት ነበር። እሺ…… ግጥም ተገጠመልሽ አሉ! አልኳት ነገር ፈልጌ። ይኹና! አለች አንገቷን ሰበቅ አድርጋ። ለምን እንዲህ እንደምሆን ታውቃላችሁ? አለች እያፈጠጠችብኝ። ኧረ አናውቅም አልኳት ወደ ኋላዬ እያፈገፈኩ። ለምን መሰለህ? እኔ ፍቅር ይዞኛል! በቃ ልሙት እንዴ? አለችና የፍቅር ዕንባዋን አወረደችው! አለቀሰች። ከቦርሳዋ ውስጥም ወደድኩት ያለችውን ሰው ፎቶውን አሳየችኝ። ወዲያው በአንድ መፅሐፍ ውስጥ የልጁን ፎቶ አድርጋ ሰጠችኝ። እኔም በጣም ከረጅም ጊዜ በኋላ ያንን መፅሐፍ ዛሬ ከልብሴ ሻንጣ ውስጥ አገኘሁትና በማስታወሻዬ ላይ ፃፍኩት! የልጅነት ጉደኛዬ የሰጠችኝ መፅሐፍ ርዕሱ “የፍቅር ዓይነቶች” የሚል ነበር።
“የፍቅር ዓይነቶች” (types of Love)
/1/ “ሮማንቲክ ላቭ” /Romantic Love/
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ሄሮድስ ነው። ሄሮድስ የወንድሙን የፊሊጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ያፈቀራት ስትደንስ አይቷትና ዳንሷም ስለማረከው ብቻ ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር “ሄሮድሳዊ ፍቅር” ይባላል። ይሄኛው የፍቅር ዓይነት የሚይዛቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ የሰውነትን ቅርጽ ብቻ አይተው የሚያፈቅሩ ሰዎች ናቸው። ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን ለምሳሌ ሃይማኖት ፣ ባሕርይ ፣ አስተሳሰብ ወዘተ ተረፈዎችን ከቁም ነገር አይቆጥሩትም። ሮማንቲክ አፍቃሪዎች ብዙን ጊዜ ቀናተኛ ናቸው። ያፈቀሩት ሰው ከማንኛውም ሰው ጋር እንዲያዩት አይፈልጉም።
/2/ “ፓሽኔት ላቭ” passionate Love
ስሜታዊ ፍቅር! ይህ ፍቅር ስሜታዊ ፍቅር ነው። ስሜታዊ ፍቅር passionate Love በጣም አስቸጋሪ የፍቅር አይነት ነው። ሕሊናን ረፍት ከመንሳቱ በላይ ሕይወትን የመመሰቃቀልና በጣም የማጨናነቅ ባህርይ አለው። ለምሳሌ ትምርትና ስራ መጥላት ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ የመሳሰሉት ይገኙበታል። ስሜታዊ ፍቅር የሚቆየው ስሜቱ እስኪሳካ ሩካቤ ሥጋ እስኪፈፅም ድረስ ብቻ ነው።
ከዚያ በኋላ ግን መጀመሪያ ከወደደው ውድ ይልቅ በኋላ የሚጠላው ጥል ይበልጣል! ይህን የመሰለው ፍቅር በመፅሐፍ ቅዱስ የአምኖን ፍቅር /አምኖናዊ ፍቅር/ ይባላል።
/3/ “ሎጂካል ላቭ” Logical Love
ይህ ፍቅር ጣራና መሰረቱ “መመሳሰል” የሚለው ቃል ነው።
እነዚህ ፍቅረኛሞች የሚመሩት በሎጂክ ነው። ለምሳሌ እሷ ድግሪ ካላት የምትመርጠው ድግሪ ያለውን ሰው ነው። ወንዱም እንደዚሁ።
/4/ “ፍሬንድ ሺፕ” /Casual friendship/
ይሄኛው ፍቅር ብዙም አያስቸግርም። ሁለቱ ፍቅረኛሞች ሚስጢር ይለዋወጣሉ ፣ የሚያስደስታቸውም ጥምረታቸው ብቻ ነው።
/5/ “ፉሊሽ ላቭ” foolish Love
“የጅል ፍቅር” አንዳንዶች በሞኝነት ራሳቸውን የሚያታልሉበት የፍቅር ዓይነት ነው። ለምሳሌ ምንነቱን ሳታውቅ ፎቶውን ብቻ አይታ ከነፍኩ በረርኩ የምትል ሴት አጋጥሟችሁ አያውቅም? ፎቶውን ብቻ አይታ ወደደችው! በቃ! ቆረጠች። ይህ አይነቱ ፍቅር በምሁራን አገላለፅ “የጅል ፍቅር” foolish Love ይባላል።
/6/ “ፖሰሲቭ ላቭ” /possessive Love/
ይህ ዓይነቱ ደግሞ ዝነኛ ሰውን የራስ ለማድረግ የሚደረገው የፍቅር ግብግብ ነው። ወንድ ስለሆንክ ለራስህ አዳላህ አትበሉኝ እንጂ ጥናቱ እንደሚያሳየው ብዙውን ጊዜ ይህ አይነት ፍቅር የሚይዛቸው ሴቶች ናቸው። እንደዚህ ዓይነቶቹ የእገሌ ባል መባልን ይፈልጋሉ።
/7/ “አንሰልፊሽ ላቭ” unselfish Love
ይህ እሷ ከምትጎዳ እኔው ልቸገር ዓይነት ፍቅር ነው።
ፍቅር ግን መዋደድ እንጂ ውለታ መዋዋል አይደለም።
/8/ “ጌም ፕሌይንግ ላቭ” Game playing Love
ይህ ዕይነቱ ፍቅር የያዛቸው ዓላማቸው አንድ ብቻ ነው። የሩካቤ ሥጋ ጥማቸውን ማርካት ብቻ። ይህ ብዙውን ጊዜ በወንዶች የሚበረታ የፍቅር ዓይነት ነው።
/9/ “ኢምፒቲ ላቭ” Empty Love
ባዶ ፍቅር! ይህ ዓይነቱ ፍቅር በአጋጣሚ ተገናይተው ወደድኩሽ ፣ ከነፍኩልሽ ፣ አበድኩልህ ፣ ክንፍንፍ አልኩልህ የሚያሰኘው ነው።
/10/ “ሰልፊሽ ላቭ” selfish Love
ራስ ወዳድ ፍቅር! እነዚህኞቹ ደግሞ ፍቅርን “ሀ” ብለው የሚጀምሩት የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ነው። ለዚህኛው ፍቅር መሰረቱ ገንዘብ ነው። ገንዘቡ እስካለ ድረስ ሆዴ! አንጀቴ! ሞትኩልህ! አበድኩልሽ! ይባባላሉ። ገንዘቡ የጠፋ ዕለትስ? ያኔማ ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ዓይናቸውንም አያሹም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነን የኢዮብ ሚስት ናት። ኢዮብ ሐብት ንብረቱ ሲያልቅ የሚስቱ ፍቅርም አለቀ፤ ኧረ እንዲያው ለመሆኑ ፍቅር በአንድ ጊዜ የሚለቅ የጥፍር ቀለም ነው እንዴ? ይህ ዓይነቱ ፍቅር ገንዘቡ ሲጠፋ ፍቅሩም ድርግም የሚል “የኢዮባዊ ሚስት ፍቅር” ይባላል።
/11/ “ኮምፓኒየን ላቭ” companion Love
ይህ እድሜያቸው ከትዳር ክልል ውጪ ወጣ ያለባቸው ሰዎች የሚጀምሩት ውጥን ነው። ከእድሜያቸው ጋር ግብግብ ስለሚይዙ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ያገባሉ። ምክንያቱም ፊታቸው ያለው የልጅ አምሮት ፣ ልጅ ማሳደግ አብሮ መኖር …… ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻ ትዳራዊ ፍቅር companion Love ይባላል።
/12/ “ኮንሲዮሜት ላቭ” consummate Love
እውነተኛ ፍቅር! ይህ ዘለቄታ ያለው የአባ ወራ እና የእማ ወራዎቻችን ፍቅር ነው። ይህም “እውነተኛ ፍቅር ነው!”
ፍቅርን ፍቅር ነው የሚያሰኙት 3 ነገሮች ሲሟሉ ነው።
ስሜት /passion/
ቅርበት /intimacy/
ቁርጠኝነት Commitment
መግባባት ሳይኖር መጋባት ግራ መጋባት ነው! እንዲሉ መግባባት ያስፈልጋል። ሁለቱ ፍቅረኛሞች በስሜትና በአስተሳሰብ መግባባት አለባቸው። በአስተሳሰብ መቀራረብ ያስፈልጋል። በችግርና በኀዘን ለመረዳዳት ቁርጠኝነትም ያስፈልጋል።
ራስን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ማንም ራሱን ፈልጎ ማግኘት አለበት! እኛ የቱ ጋር ነው ያለነው?
*************
ይህችን ፅሑፍ ከጨረስኩ በኋላ ወዲያው የልጅነቴን ጓደኛ ደወልኩላት። ሔርሜላዬ እንደምን አለሽ? አልኳት ተጣድፌ። ሰላም ነኝ ….. በቃ የሆድ የሆዳችንን ተጨዋወትን። የሰጠሽኝን መፅሀፍ በድጋሚ ሳነበው ትዝ ብለሽኝ ደወልኩልሽ፤ አሁንም ፍቅር እንደያዘሽ ነው? አልኳት ድሮ እንደምቀልድባት ፍግግ እያልኩ።
“የሰጠውህን ፎቶህንስ ጣልከው እንዴ?” አለችኝ።
ከላይ ሳልነግራችሁ፤ ለካ ወደዱኩት ብላ የሰጠችኝ የራሴን ፎቶ ነበር!
“እንዴታ አለ አልጣልኩትም” አልኳት።
ሔርሜላዬ ከ2 ወር በኋላ እንደምታገባና በሠርጓ ላይ መገኘት እንዳለብኝ ነገረችኝ። በደስታ እንደምገኝ ነገርኳት። ጓደኛዬን ይዜ መምጣት እችላለሁ? ስላት “ለጓደኛህ ቦታ የለንም” አለች ድሮ እንደምትጫወትብኝ እየቀለደችብኝ። ጓደኛ ስለመያዜም ወተወተችኝ፤ ማን ናት ወዴት ናት ….. አይ አብሮ ማደግ! ታላቅ ነው ለካ!
ጊዜውም ነጎደ! ለውዷ ጓደኛዬ ውድ ስጦታ መግዛት አለብኝ። ታላቁ ስጦታዬ ግን የዛሬ 11 ዓመት የሰጠችን “የፍቅር ዓይነቶች” የምትለዋ መፅሐፍ ናት!
No comments:
Post a Comment