Saturday, 11 August 2012




መሮጥ እንደዚህ ነው በአንድ ላይ ተባብሮ
ሰም እና ወርቁ በአንድ ተጨምሮ
ረጅም ሩጫን አየነው ዘንድሮ!
ትምህርትም ሆነን ለመስራት ተፋቅሮ

ደፋር ነች ጀግና ነች እውነትም ደፋር ነች
ፋታ አልሰጠችም ልክ እንዳሸነፈች
ርግብዬ ብላ እመቤቴን ያዘች!

እልል ይበሉ የወለዱ እናትሽ
ያኔ እንደተባለው አምጠው ሲወልዱሽ
ጋሻና ጦር ያዙ ፎክሩ በሏቸው
ዘራፍ! የጀግና ልጅ! ይበሉ ደፋሩ አባትሽ!!!













ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ አባትሽ
ደፋር ነው አባትዋ ልጅቱም ደፋር ናት
አሯሯጧን ያየ በአባትዋ የወጣች “ደፋር ናት” የሚላት

ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ እናትሽ

ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
ይህን ድንቅ ስምሽ ማን ይሆን የሰጠሽ!







ሱባኤውን ይዘሽ ፍልሰታንም ጾመሽ
ድንግል እናትሽን ከደረትሽ ይዘሽ
ወላዲተ አምላክ እርጂኝ ብለሽ ለመንሽ
እልልልል ይኸው ተሳካልሽ
ታላቅ እምነትሽን በዓለም ላይ ሰበክሽ!


ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
ድፍረት ከእምነት ጋር ፈጣሪ ለገሰሽ
መሰረት እስኪ ልጠይቅሽ
ምነው ቪቪያንን ጥለሽ ብቻሽን ገሠገሥሽ?
"
ብቻውን የሮጠ ማንንም አይቀድምም"
ብቻሽን ሮጠሽ ብቻሽን አልበላሽ
መሠረት ጥሩነሽ ገለቴ ምን ልበል በሞቴ?
ፍቅር አንድነትን ህብረት መቻቻልን
እስኪ አስተምሩን ለሀገር መስራትን
"
ብቻውን የሮጠ ማንንም አይቀድምም"
ብለው አስተማሩን ድንቅ ወርቆቻችን!







ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
ሩጫን አስተማርሽ አፈትልከሽ ሮጠሽ!
ነይ ተደሰቺ ባንዲራውን ይዘሽ
ሽልማትሽ ይህ ነው ለፈሰሰው ላብሽ!

እልል ይበሉ የወለዱ እናትሽ
ያኔ እንደተባለው አምጠው ሲወልዱሽ
ጋሻና ጦር ያዙ ፎክሩ በሏቸው
ዘራፍ! የጀግና ልጅ! ይበሉ ደፋሩ አባትሽ!!!










                                              
                                        
 ይድረስ ለታላቅዋ        


              የእምነት ሰው
     
          
                         መሠረት ደፋር!





ETV (DVD)

ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ አሪፍ ታሪክ ላውጋችኹ!

“ሹርባ ልትሰራ ሄዳ ጸጉሯን ተላጭታ መጣች” አሉና ”አምራለሁ ብላ ተኩላ ዓይኗን አጠፋችው ቸኩላ” አሉ እትዬ ጣይቱ ውብ ሴት ልጃቸውን እየመከሩ። ልጅቱም በእናትዋ ወጥታ ኖሯል “ጀንበር ካለች እሩት እናት ካለች አጊጥ” አለቻቸው።

የእለቱ ኢቲቪ ዝግጅቶቻችን እነዚህ ናቸው።

ዜና፦ ሲባዛ በመቶ (DVD)

ማስታወቂያ፦ ሲባዛ በመቶ (DVD)

ድራማ፦ሲባዛ በመቶ (DVD)

አጠር ብለው ረዘም ያሉ ንግግሮች፦ ሲባዛ በመቶ (DVD)

ፕሮግራሙ ሁሉ “በ DVD” ናቸው።

የሰለጠነው ዓለም ማንም የፈለገ ባለሥልጣን ቢሆን ከአጭር ደቂቃዎች በላይ የቴሌቭዥን የአየር ጊዜ አይሰጠውም። እኛ ቤት ግን አንድ የቀበሌ ኃላፊ አጠር ብላ ረዘም ያለች ታሪክ ይተርክልናል። ይህ እኛ ቤት ነው። በሰለጠነው ዓለም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን መግለጫ ቢሰጡ እንደ እኛ አጠር ብላ ረዘም ያለች ሳትኾን በቃ! አጠር ያለች ናት። “ትሻልን ትተሽ ትብስን አመጣሽ” አሉ እትዬ ጣይቱ! ይባስ ብለው የወንዶቹ አስር ሺህ ፍጻሜ ካለቀ በኋላ ኢቲቪ ስንከፍት “ክቡራን ተመልካቾቻችን ውድድሩ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ይጀመራል” አሉን። እስከ ዛሬ ድረስ ለካ DVD ነው የምናየው። በኢቲቪ DVD ማጫወቻ የተከተተው DVD ሲያልቅ ከእንደገና ሪዋይንድ አድርገን ጥንት ያለቀውን ሩጫ እንደ አዲስ ማየት እንችላለን። ምን ይህ ብቻ መቶ ጊዜ የሚደጋገመውም ለካ DVD ስለሆነ ነው! በጣም የሚገርመኝ ደግሞ ያቺ በዜና ላይ የምናያት የጋዜጠኞቹ ኮምፒተር ናት። እንደ አርቴፊሻል አበባ ለጌጥ የተቀመጠች ይመስለኛል። አንዳች ትኩስ ነገር ሳይነበብባት ለጌጥ የተቀመጠች አርቴፊሻል አበባ መሆንዋ እኔ ጣይቱ ገብቶኛል። ከትላንት በስቲያ በኦሎምፒክ ቻይና በዘጠኝ ወርቅ እየመራች በስድስት ወርቅ ትመራለች ተብሎ ተነግሮናል። ታዲያ ኮምፒተሩ ስራው ምንድን ነው? የኮምፒተሩ ስራማ DVD ማጫወት ስለሆነ የሚከፈትልንን እናያለን አሉ እትዬ ጣይቱ ገና በጠዋቱ!


እትዬ ጣይቱ ከአዲስ አበባ ለንደን የገቡት በቅርቡ ነበርና ለሳቸው ተብሎ ETV ዲሽ ተገጠመ። የእንግሊዘኛ ፕሮግራም ብዙም ስለማይገባቸው አይጥማቸውምና እስኪ ያችን “DVD” ክፈትልኝ አሉ እትዬ ጣይቱ ስልችት ብለው። እኔም በቅርብ ያገኘሁትን DVD ከፈትኩላቸው። እትዬ ጣይቱ ግን ፍግግ እያሉ እዲያ እኔ ያልኩት የኢቲቪን DVD ነው አሉ። እኔም ከትከት ብዬ ሳቅኩና ደግሞ የምን DVD ፕሮግራም ተጀመረ? አልኳቸው። እዲያ ያን የሀገሬን DVD ክፈት አሉኝ እትዬ ጣይቱ ሪሞቱን በእጃቸው እያሳዩኝ። ከዛች ቀን ጀምሮ እትዬ ጣይቱ ባወጡለት ስም መጥራት ጀመርን። ETV ሳይሆን “DVD” ብለነዋል።


እትዬ ጣይቱ ከዘራቸውን ደገፍ ብለው በሐሳብ ባቡር ተሳፈሩና እንዲህ እያሉ ታሪካቸውን አወጉኝ። ቢቢሲ ዘወትር ቅዳሜ ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ የሚያሳየው ድንቅ ፕሮግራም አለ። ፕሮግራሙ “ተፈጥሮ ድንቅ ናት” ይባላል። ተፈጥሮ ከነልጆችዋ ከነውበትዋ እጇን ይዘው ቤታችችሁ ድረስ የመጣች እስኪመስላችሁ ድረስ እጅግ ይመስጣል። የአናብስትና የአራዊቱ ልብ የሚመስጥ ፍጥጫ፣ የዝሆኖች ልፊያ ፣ የዓሦች አክሮባቲክ ድንቅ ችሎታ ልብና ዓይንን ገዝቶ አፍን አስከፍቶ ያስቀራል!


በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓሦች ሲዋኙ ግርማ ሞገሥ ያለው ሻርክ ይመጣና ይፎክርባቸዋል። ሻርክ በቀን 6 የሚያህሉ ዓሦችን መብላት አለበትና እንደ ጉድ ያራውጣቸዋል!


ዓሦቹም እንደ ጉድ ይራወጣሉ!

እንደ ጉድ በግሩፕ ይከፋፈላሉ!

እንደ ጉድ ነፍሴ አይጪኝ እያሉ ውር ውር ይላሉ!

ሻርኩም የኦሎምፒክ ጅምናስቲክ ውድድር ያለበት ይመስል ለአፌ ጅምናስቲክ የሚሆኑ ዓሦች ካላገኘሁ አላርፍም እያለ እንደ ጉድ ውኃውን በትጋት ይጋልባል! ይህ ሻርክ እንደ ዋና ብቃቱ ከሆነ በኦሎምፒክ ሪከርድ ይሰብራል ተብሎለታል! በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓሦች በሚሊዮን በሚቆጠሩ ግሩፕ ተከፋፍለው ቀስ በቀስ ብቸኛ ዓሣ ይኾናሉ። ሻርኩም ይህችን ብቸኛ ዓሣ የገባችበት ገብቶ እንደጎመጀው ለአፉ ጅምናስቲክ ያደርጋታል!  ይህች የዕለቱ የመጀመሪያ አፕታይዘር ናት። አቶ ሻርክ ቢያንስ 6 ዓሦችን ካላገኘ የበላ አይመስለውምና ይህን ሂደት እንደገና ይጀምራል……      “ዓሣ የጌቶች ምሳ የገረድ አበሳ” አሉ እትዬ ጣይቱ ፍግግ እያሉ! ወዲያው ፈገግታቸው ከፊታቸው ጠፍቶ እንዲህ እያሉ ብሶታቸውን ቀጠሉ። እነዚያ በተፈጥሮ ውበት ልባቸው የከነፈ ባለሙያዎችም የውኃ ውስጥ ካሜራቸውን ይዘው የውኃን ዓለም እንደ ጉድ ያሳዩናል። ይግረማችሁ ብለው ኢትዮጵያ ገቡና ግሩም ድንቅ ተፈጥሮን አሳዩን! አንድ ትልቅ ንሥር እጅግ ከፍ ካለ በሀገሬ ተራራ ላይ ወጣና በአፉ የያዘውን አጥንት ለቀቀው። ያ አጥንት እየተምዘገዘገ መጣና ዐለቱን መታ። አጥንቱም እዬዬ ብሎ ጮኸ! እንደ ጉድ ደቀቀ! ንሥሩ ክንፉን እያማታ እንደ ጉድ ወደ ታች ተምዘገዘገ! ከአጥንቱ የወጣውን ቦን ማሮው እንደ ጉድ በላ! ከዚያም እንደ ጉድ ክንፉን እያማታ በረረ!


ይህ ነው መዝናኛ ማለት!

ይህ ነው ሊታይ የሚገባው!

ይህን ነው ለማየት መጓጓት!

“ዓይን ካላዩበት ግንባር ነው” አሉ እትዬ ጣይቱ ዓይናቸውን ጨፍነው ግንባራቸውን አንዴ ኮስተር አንዴ ፈታ እያደረጉ! እትዬ ጣይቱ ጨዋታ አሳምረው ከማወቃቸውም በላይ ንግግራቸው ሁሉ በእንቅስቃሴ የታጀበ ስለሆነ ነገረ ስራቸው ሁሉ ያስቀናል። የእትዬ ጣይቱ እሮሮ ቀጠለ።  ልብ በሉ ነጮቹ ይህችን እይታ ለሕዝባቸው ለማሳየት ነው ይህን ሁሉ ባሕር አቋርጠው ኢትዮጵያ የመጡት። እኛስ? ኢቲቪዬዋ እንደምን አሉልኝ? እምዬ ኢቲቪ እንዲህ ቢያዝናኑን አሁን ምን ነበረበት? “ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል” አሉ እትዬ ጣይቱ ሆዳቸውን በእጃቸው እየዳሰሱ። በእትዬ ጣይቱ ንግግር ኢቲቪ ክፉኛ አኮረፉ። “ሆደ ሰፊ ይሻላል ከአኩራፊ ሲባል አልሰሙም እንዴ?” አሉ እትዬ ጣይቱ የተፈጥሮ ሆዳቸውን አየር ምገው ሰፊ እያደረጉ። በቃ! ሆደ ሰፊ ሆነው ስሙኝ። ምን መሰሎት አሁን እሺ እኛ ቤት ስንመጣስ ምን እናያለን? የባለሥልጣናትን አጠር ብለው ረዘም ያሉ ንግግሮችን? አጠር ብለው ረዘም ያሉ ማሳሰቢያዎችን? አጠር ብለው ረዘም ያሉ ውይይቶችን? ለሁሉ ጊዜ አለው አለ ጠቢቡ። አዎ ለሁሉም ቦታና ጊዜ አለው። ለእነዚህ ሁሉ ራሳቸውን የቻሉ ቦታ አላቸው አሉ እትዬ ጣይቱ ገና በጠዋቱ። “መናገር መልካም ነው ማዳመጥ ይበልጣል” ብለህ ነው መሰል ዝም ብለህ ትሰማኛለህ፤ በል ተናገር “ብዙ ዝምታ ይሆናል በሽታ” ብለው እንደለመዱት በአባባላቸው ወጋ አደረጉኝ። እኔም በንግግራቸው ስለተወጋሁ ሌላ ሳይጨመርብኝ መናገር ጀመርኩ።


 እትዬ ጣይቱ በእርግጥ እርሶ ያሉት  ትክክል ነው። 24 ሰአት የሚተላለፍ የፓርላማ ንግግር ያለበት ራሱን የቻለ ቻናል አለ። ያን የወደደ ያያል። 24 ሰአት የሚተላለፍ የዜና ቻናል አለ። ያን የወደደ ያያል። 24 ሰአት የሚተላለፍ የፊልም ቻናል አለ። ያን የወደደ ያያል። ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ አንጋፋ ብሔራዊ ድራማ አላቸው። ያን የወደደ ያያል።

ይህ ነው ምርጫ!
ይህ ነው መዝናኛ!

ዘወትር ቅዳሜና እሑድ ማታ “የቀኑ ጨዋታ” እያሉ የእግር ኳስ ፍቅር ላለን ሰዎች ፕሪሚየር ሊጉን ያሳዩናል።

ይህ ነው መዝናኛ!
ይህ ነው እይታ!

ይህ ሁሉ እኛ ቤት ቢሆን እንዴት ውብ ነበር? እኔ ኳስ ከልቤ ብወድም አንዳቸውንም የኢትዮጲያ ተጫዋቾችን በቴሌቭዥን መስኮት አይቼያቸው አላውቅም። እዚህ ግን እነ አሌክስ ፈርጉሰን በጋዜጠኞች ይፋጠጣሉ። እነ ሩኒ እየመጡ ካሸነፉ ደረታቸውን እየነፉ ከተሸነፉ ራሳቸውን እያከኩ ይናገራሉ። አሁን ማን ይሙት እኛ ቤት ይህ እንዳይሆን ምን ይከብድ ይሆን? አልኳቸው። እትዬ ጣይቱም እሱስ ምንም አይከብድም “ልፋ ያለው በሕልሙ ሸክም ይሸከማል” የሚለው ተረት ብቻ ነው የሚከብደው አሉኝ። እኔም ሳላስበው ድንገት ብሶቴ ከእትዬ ጣይቱ ብሶት ጋር ተደመረ። የቴዲ አፍሮ ዘፈን እንዳይተላለፍ ታገደ ሲባል ሰማሁ። እትዬ ጣይቱ እርሶ ምን ይላሉ? ብዬ ጠየኳቸው። እትዬ ጣይቱ ትንሽ ፍግግ እያሉ “የተከለከሉ ነገሮችን የማወቅ ጉጉት የሰው ተፈጥሮ ነውና እገዳው ብዙዎች ጆሮ ሰጥተው እንዲሰሙት ያደርጋል” አሉኝ። እባባላቸው ገረመኝ። እዚህ ጋ የምንነጋገረው ዘፈን ጠምቶን ሳይሆን ስለ ብሮድካስት ነፃነት ነው።

ይህችን ጥሑፍ ጥፌ ልጨርስ ስል እትዬ ጣይቱ ሲባዛ ፕሮግራም ጀምሯል በል ክፈትልኝ አሉ። ኧረ ለመሆኑ አዘጋጆቹ ማባዛት ብቻ ነው እንዴ የተማሩት? መደመር የሚባል ሒሳብም አለኮ። ዝግጅቶችን ብትደምሩልን አንከፋባችሁም። መቀነስም የሂሳብ  ሕግ ነው። ረዘም ረዘም ያሉ ወሬዎችን ብትቀንሱ ከቶ አንከፋም። ኧረ ማካፈልም ሒሳብ ነው። ፕሮግራሞቹን እጥር ምጥን ያለች ዝግጅት ብታደርጉ ማን ይሙት እንዴት ደስ ባለን ነበር። እድለኛ አይደለንምና ማባዛት ብቻ ሆነብን። አንዷን የተቀረፀች ፕሮግራም በመቶ ተባዝቶ መቶ ጊዜ ይቀርባል። የአየር ጊዜኮ ውድ ነው። መቶ ጊዜ በተደጋገሙት ፕሮግራማችሁ ምክንያት ቴሌቭዥኖቻችን የተመጣጠነ ምግብ አጥተው እንዳይከሱ እፈራለሁ! አዬ ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል አሉ እትዬ ጣይቱ ምርር ብለው እንደለመዱት ሆዳቸውን በእጃቸው እየዳሰሱ።


መቼስ በእኔና በእትዬ ጣይቱ የብሶት ንግግር እምዬ ኢቲቪ ሳይቀየሙን አልቀረም። ክፉኛ አዝነውብን ፊታቸውን እንደ ፎጣ አጣጠፉት። በመጨረሻም ኢቲቪ ይህን አባባል ደረደሩ።




“ዕርቅ የፈለገ ንጉሥ ገበሬ ያስታርቀዋል ዕርቅ ያልፈለገን ገበሬ ንጉሥ አያስታርቀውም”


ኩርፊያውም ቀረ። እኔም ዕርቅ ያልፈለገውን ገበሬ እንዳልሆን ፈራሁና ስለ ኢቲቪያችን በልቤ ይህን አልኹ።

“የልብ ሳይደርስ እድሜ ይደርስ! አሉ እትዬ ጣይቱ።



Saturday, 4 August 2012

“እውነትም ጥሩነሽ”


ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
ሩጫን አስተማርሽ አፈትልከሽ ሮጠሽ!
ነይ ተደሰቺ ባንዲራውን ይዘሽ
ሽልማትሽ ይህ ነው ለፈሰሰው ላብሽ!

ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ እናትሽ!
ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
ይህን ድንቅ ስምሽ ማን ይሆን የሰጠሽ!

ጥሩነሽ እስኪ ልጠይቅሽ
ምነው ቪቪያን ጥለሽ ብቻሽን ገሠገሥሽ!?
እልልልል እኛን ደስ ብሎናል
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ አባትሽ!
ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
ወርቅ ይዘሽ መጣሽ ለእናት ሀገርሽ!!


“የዕንባ ሳቅ”

“ላይፈሩ ቁጣ ከእብደት አንድ ነው” ትል ነበር ንግሥት ጥሩነሽ! ቪቪያን “ጥሩነሽን አልፈራትም ወርቁም የኛ ነው ጨፍሩ” ብላ ሳይኮሎጂ ተጠቅማ ነበር። “ለአፍ ዳገት የለውም” አሉ እትዬ ጣይቱ። ንግሥት ጥሩነሽ ግን ሩጫ የአፍ ስፖርት ሳይሆን የሜዳ ላይ ፍልሚያ መሆኑ ስለገባት ብዙ ኃይል አላባከነችም። 

ቪቪያን “ጥሩነሽን አልፈራትም” ስትል ንግሥት ጥሩነሽ ከትከት ብላ ሳቀችና “ድብድብ አይደለም በሜዳ ላይ እናያለን” ብላ በሜዳ ላይ ንግሥትነቷን አሳየችን! ብዙ የፎከረችው ቪቪያን አፍዋ ጀግና ቢሆንም እግሯ ከዳት። አፍና እግር አልጣጣም አሉ። ይህን ጊዜ ንግሥት ጥሩነሽ “ከአፍ ወለምታ የእግር ወለምታ ይሻላል” አለችና ከአጠገብዋ አፈትልካ ገሠገሠች። ቪቪያን አንዳች ማድረግ አትችል ነገር ንግሥቷን ከሩቅ እያየች “አይ አፌ ጉድ ሰራኝ የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም“ አለች። ንግሥት ጥሩነሽም ቀበል አድርጋ “ልጅ ለእናትዋ ምጥ አስተማረቻት” ብላ ሩጫን ለቪቪያን ጥሩ አድርጋ አስተማረቻት!

ይድረስ ለንግሥት ጥሩነሽ፦ ሩጫው ሲጀመር ልቤም በፍርሃት ይመታ ጀመር። “ወርቁ በእጃችን ገብቷልና መጨፈር ትችላላችሁ” ብላ እኮ ነበር ኬንያዊቷ ቪቪያን። ይህ ደግሞ ፍራቻውን ጨመረ። ኢትዮጲያዊያን በሙሉ ልባቸው በያሉበት ይመታ ነበር። ንግሥት ጥሩነሽ እግሮቿ ሲፈተልኩ ልቧ ሲመታ እኛም በያለንበት ልባችን ይመታ ነበር። መቀመጥ አቅቶኝ ቆሜ አብሬያት በመንፈስ እሮጥ ነበር። ሳይታሰብ አፈትልከሽ ስትቀድሚ ዕንባዬም ሳላስበው ቀደመኝ። በእውነት እየዘለልኩ በዕንባ አሳቅሽኝ። “የዕንባ ሳቅ” ልበለው። አዎ! ንግሥት ጥሩነሽ ዲባባ ይህ ይገባሻል።

“ወርቅ ለማግኘት ወርቅ ይዞ መነሳት” ትል ነበር ንግሥት ጥሩነሽ። እውነትም ወርቅ የሆነችውን “ንግሥት ወርቅነሽን” ይዛ ተነሳች። “ንግሥት ወርቅነሽ ኪዳኔ” እውነትም ወርቅ ናት። ጥርሷን ነክሳ ለሀገርዋ የተፋለመች ታላቅ ወርቃችን ወርቅነሽ ኪዳኔ ናት። አደራ በሰማይ በምድር ዋናው ሞተር ንግሥት ወርቅነሽ እንዳትረሳብን። ወርቅነሽ ወርቁ የአንቺና የሀገርሽ ልጅ የጥሩነሽ ዲባባ ነው!


አማትባ ተነሳች ወርቅ ይዛ ንግሥት ሆነች። ንግሥት ጥሩነሽ ጥሩ አድርጋ የከፈተችው በር ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ ማነቃቂያ ነው። አሁንም እንደተለመደው ቆሜ ንጉሥ ቀነኒሳን አያለሁ። ሌሎቹም እንዲሁ በዕንባ ያስቁናል! “የዕንባ ሳቅ!!”




Thursday, 2 August 2012

==>“ጾመ ፍልሰታ”<==



  
በደገኛዋ በዘመነ ሐዋርያት ጊዜ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለአገልግሎት የሚመላለሱት በደመና ተጭነው ነበር። በአንድ ወቅት ከደገኞቹ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅ/ቶማስ በደመና ተጭኖ ከሀገረ ስብከቱ ከሕንድ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዝ ነበር። በዚህ የደመና ጉዞ ላይ እመቤታችን ወደ ገነት ስታርግ አገኛት። ቶማስ “ከዚህ በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ተጠራጣሪ ሆንኩ፤ ያንቺንም ትንሣኤ ላላይ ነበር” ብሎ በጣም አዝኖ ከደመናው ላይ ሊወድቅ ፈለገ። እመቤታችንም ከአንተ በቀር ማንም ዕርገቴን አላየም ብላ አጽናናችውና የተገነዘችበትን የወርቅ ጨርቅ ወይም ሰበናዋን ሰጠችው። ቶማስም የእመቤታችንን ሰበና ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ገሠገሠ። የእመቤታችንን ሰበና ለደገኞቹ ሐዋርያት አሳያቸው። ሐዋርያቱም ለቶማስ እንደታየሽ ለእኛም ተገለጪ ብለው ጾመው ሱባኤ  ይዘው እመቤታችን ለደገኞቹ ሐዋርያት ተገልጣላቸዋለች። ይህም “ፍልሰታ” ብለን የምንጾመው ልጅ አዋቂው የሚወዳት ጾም ናት።

   
እንኳን “ለጾመ ፍልሰታ” በሰላም አደረሳችሁ።


“ፍልሰታ” ማለት ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡


የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማዕታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ፡፡ /መዝ 44:9/

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ። የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፦ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና በጽኑ ምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡

የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታው ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን /መግነዟን/   ሰጥታው ዐረገች፡፡

ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት። እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ “አንተ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን?” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም። ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሰበኗን /መግነዟን/ ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡ (ዲያቆኑ ከመስቀሉ ጋር የሚይዘው ጨርቅ የእመቤታችን ሰበና ምሳሌ ነው)

ሐዋርያትም ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ /ረዳት/ ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ /ዋና/ ዲያቆን አድርጐ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን ዕርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡

ቤተክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዓበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም እንድንጾም አድርጋናለች፡፡ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሳኤና ዕርገት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ልጆቼ” ይላቸው ለነበሩ ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች፣ አረጋውያንም የጾመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል፡፡

የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ /በጾመ ፍልሰታ/ ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው፤ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ በሰሙነ ፍልሰታ ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡

ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጅዋ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡

እመቤታችን ጥር 21 ቀን ዕረፍት በሆነበት ዕለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ ዕረፍት /የመቃብር ቦታ/ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው “ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል። እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች ዐረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን፤ ኑ ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው “ታውፋኒያ” የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በኅቡዕ ተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች።

እመቤታችን ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣ መድኃኔዓለምን በማህጸንዋ ጸንሳ ዘጠኝ ወር ፤ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ ነቢያት አስቀድመው ስለ እመቤታችን እረፍትና ትንሳኤ በምሥጢር ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር /መዝ 131:8/ “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ብሎአል፡፡ ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡



ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሐ ምጡቀ ፤

በአእባነ ባህርይ ዘተነድቀ፤

ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደኒ ሠቀ  ፤                         


ትርጉም፦ እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል። ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል (መልክአ ማርያም)

ለደገኞቹ ሐዋርያት ለደገኞቹ አባቶቻችን ለአባ ሕርያቆስ ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች እመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን። ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን። ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ጾመ መድኃኒት ያድርግልን- አሜን ፡፡