Friday, 3 February 2012

ነነዌ እና ዮናስ፦

ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ ፩
  
ለነብዩ ዮናስ የእግዚአብ ቃል መጣ
ነነዌን ለመስበክ ተነሳና ውጣ
በህዝቡ ኃጢአት ቁጣዬ እንዳይመጣ

ነብዩ ይህን ግዜ በልቡ አሰበ
የጌታ ባህሪው ይቅርታ እንደሆነ
ዮናስ ወደ ተርሴስ መኮብለል ወደደ
ወደ ከተማይቱ ምታልፍ መርከብ አየ
ዋጋም ከፈለና በመርከብ ተጓዘ።

ማን ይኮበልላል ከእግዚአብሄር መዳፍ
ወደ ጥልቁ ቢሄድ እንደንስር ቢመጥቅ
ጌታ ሁሉን ገዝቷል በኀይልና ክብሩ
ታላቅ ንፋስ መጣ ማዕበልን ይዞ
መርከቡን ቢያናውጥ ሁሉም እጅግ ፈሩ
እንዲቀልላቸው እቃቸውን ወደ ባህር ጣሉ
ወደ አምላካቸው አበርትተው ጮሁ
በጉዞው ከባድ እንቅልፍ ይዞት
ኮብላዮ ነብይ ይህን ሁሉ አላየም
የመርከቡ አለቃ ወደ ዮናስ ቀርቦ
ምነው ተኝተሃል ስንጠፋ ዝም አትበል
ሁሉ እንደለመነ ፈጣሪህን ለምን
ደግሞም ይህ ነገር በማን እንዳገኘን
በመካከላችን እጣ እንጣጣል
እጣውም ተጣለ በዮናስ ደረሰ
ማበሉ ፀጥ እንዲል ወደ ባህር ተጣለ።
በፈተና ግዜ መውጫው ይሰጠናል
ዮናስ በባህር ውስጥ አሳ ታዞለታል
በአሳ ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ጮኸ
በአምላኩም ተሰማ ባህር ተሻገረ
ወደ አምላካቹ ተመለሱ እያለ
ታላቋን ከተማ ነነዌን ሰበከ
ንጉስ ለአምላኩ ክብሩን አዋረደ
ትንሹም ትልቁም ወደ አምላኩ ጮኸ
ቀን በነነዌ ታላቅ ፆም ታወጀ
ጌታም ለዛች ሀገር ምህረትን ሰጠ።

ነብዮ ከፀሐይ ሊጠለል ወደደ
በ፩ ቀን ተክል እጅግ ተደሰተ
በንጋታው ቢያጣታ እጅግም አዘነ
ጌታም መለሰለት እንዴት እንደሆነ
አንተ ላልዘራኸው ምታዝን ከሆነ
እኔም ለህዝቤ አዘንኩ አይተህ ተማር አለ።

የዓሣ ሆድ ውስጥ ፀሎት”
ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ
ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ፀለየ፤ እንዲህም አለ፤
ተጨንቄ ሳለሁ ወደ እግዚአብሔር ተጣራሁ፤
እርሱም መለሰልኝ፤

ከመቃብሩም ጥልቅ እርዳታን ፈልጌ ጠራውህ፤
አንተም ጩኸቴን ሰማህ፤
ጥልቅ ወደ ሆነው ወደ ባህሩ መካከል ጣልኸኝ
ፈሳሾችም ዙሪያዬን ከበቡኝ፤
እኔም ወደ ቅዱስ መቅደስህ እመለከታለሁ አልኩ
አቤቱ ጸሎቴ ወደ መቅደስህ ትግባ

እግዚአብሔር ዓሣ አንበሪውን አዘዘው
እርሱም ዮናስን በየብሱ ላይ ተፋው!!!
    ትንቢተ ዮናስ ምዕ. [፪ -ፍ]

ለአጽዋማትና ለበአላት መሰረታቸው ነነዌ ነው፤
ጾመ ነነዌ ፣ ዐብይ ጾም ፣ ጾመ ሐዋርያት ሁል ግዜ በሰኞ ቀን ይጀምራሉ።
ደብረ ዘይት ፣ ሆሣዕና ፣ በዓለ ትንሣኤ ፣ በዓለ ሃምሳ ደግሞ ሁል ግዜ በእሁድ ይውላሉ።
ርክበ ካህናትና ጾመ ድህነት ሁል ግዜ ረቡዕ ቀን ይውላል። ስቅለት ሁል ግዜ በአርብ ቀን ፣ ዕርገት ደግሞ ሁል ግዜ በሐሙስ ቀን ይውላል። ጾመ ነነዌ የበረከት ጾም ይሁንልን ፤ አሜን።
     ወሥበሐት ለእግዚአብሔር [ተክለ መድህን]

Friday, 27 January 2012

             የእናታችን ወተት ያስፈልገናል በሉ”!

ዘና ብላችሁ ተቀመጡና እስኪ ገጠመኜን ላውጋችሁ፤
የዛሬው ገጠመኜ ካለሁበት ከተማ ከለንደን ነው ፤
ግዜው የፈረንጆቹ ሰመር ነበርና የጠዋቷ ፀሐይ ፈካ ብላ ወጥታለች። የከተማዋ ሰዎችም እድለኛ ናቸውና ብዙ የመዝናኛና የእስፖርት መለማመጃ ትላልቅ ፓርኮች አሏቸው። ብዙዎቹ የፀሐይ መከላከያ መነፅራቸውን በቄንጠኛው አድርገው በየሜዳው ተዘርረዋል፤


ከአጠገባችን የተቀመጡ ሰዎች በእጃቸው ላይ የያዙትን መፅሐፍ ቅዱስ ገልጠው ይወያያሉ፤ በተወሰኑ ወጣቶችም ተከበዋል። እኛም ለማየት ያህል ቀረብ አልን፤ በመጀመሪያ ጆሯችን የገባው “ወንጌል አንዲት ናት እናንተ ግን ገድል ተዓምር እያላችሁ ብዙ መፅሐፍ አላችሁ; ይህን ሁሉ ከየትኛው ወንጌል አምጥታችሁ ነው የፃፋችሁት” የሚል ነበር።
    


ከመካከላችን አንዱ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰላቸው፤
ጥያቄያችሁን ለመመለስ ያህል ወንጌላዊው ማቴዎስ እንዲህ ይልላችኋል አለና ከሞባይሉ ላይ የጫነውን ማስታወሻ አነበበላቸው፦ በነብያት ናዝራዊ ይባላል ተብሎ የተነገረው ይፈፀም ዘንድ ናዝሬት ወደ ምትባል ከተማ ገብቶ ኖረ” [ማቴ. 2: 23] ይህን ካነበበ በኋላ ቀና ብሎ አየና እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦

ናዝራዊ ይባላል ብሎ የተነበየው ነብይ ማን ነው? በየትኛው ትንቢት ላይስ ይገኛል?

ግሞሾቹ ዝም አሉ ሌሎቹም ከማስታወሻቸው ፈለጉ፤ አንዱ ግን ከኋላ ሆኖ መፅሐፍ ቅዱስ ሲያገላብጥ አየው።

ብዙ አትድከሙ ይህን ትንቢት በመፅሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ብትፈልጉት አታገኙትም! እነሆ ነብያቱ “ናዝራዊ ይባል ዘንድ ናዝሬት ወደ ምትባል ከተማ ገብቶ ኖረ ብለው ተንብየው ነበር፤ ይህ ትንቢት በነብያት ተነግሮ በምርኮ ግዜ በጠፉት መጻሕፍት የነበረ ሲሆን መጽሐፍቱ ቢጠፉም በቃል ለሐዋርያት ደርሷል። እነሆ ማቶዎስም በወንጌሉ ፃፈው!

አንድም ሙሴን የተቃወሙትን ጠንቋዮች ስማቸውን አልነገረንም፤ ቅ/ጳውሎስ ግን ኢያኔስና ኢያንበሬስ” ብሎ ስማቸውንም ጭምር ተናግሯል [2ኛ ጢሞ. 3: 8] ማን ነገረው? እነሆ በትውፊት ያገኘውን ተጠቅሞ ታላቁ ሐዋርያ በመልዕክቱ ላይ ጽፎታል።

አንድም ቅ/ጳውሎስ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ለተግሳጽና ለምክር ያስፈልጋሉ ብሎ ለጢሞቴዎስ አስተምሮታል [2ኛ ጢሞ. 3: 15] ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ አንዴ በተግባር አንዴ በመልዕክቱ እየፃፈ ስለ አዋልድ መፅሐፍት ጢሞቴዎስን አስተምሮታል።

አንድም ሐዋርያው ይሁዳ ስለ ቅ/ሚካኤልና ስለዲያቢሎስ ክርክር በመልዕክቱ ላይ ይነግረናል [ይሁዳ 1:8] ይህ ክርክር ግን በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ አልተፃፈም ፤ ታዲያ ሐዋርያው ይሁዳ ይህን ታሪክ ከየት አምጥቶ ነው የፃፈው?

እነሆ ታሪኩ እንዲህ ነው፦  ሊቀ ነብያት ሙሴ እጅግ ታዛዥና የዋህ ስለነበር ሀገረ ከንዓንን ለማየት ወደ ናባው ተራራ በወጣ ግዜ ሁለት መላዕክት በአረጋውያን ተመስለው መቃብር ሲቆፍሩ ሲያይ ላግዛቹ ብሎ መቆፈሪያውን ተቀበላቸው፤ እነሱም በመጨረሻ “ሰውየው በአንተ ልክ ነውና እስቲ ገብተህ ለካልን አሉት  እሱም በየዋህነቱ ጉድጓዱ ውስጥ ገብቶ እንደተኛ እንደ እንቅልፍ አሸልቦት በዚያው ዐረፈ; መላዕክትም ቀበሩት። እስራኤላዊያን ሙሴን እጅግ ስለሚወዱት የሙሴን መቃብር እንደ ጣዖት እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን መቃብር ሰወረው፤ ነገር ግን ጠላት ዲያቢሎስ ሊያሳያቸው በመነሳቱ ቅዱስ ሚካኤል ተቃወመው; በመጨረሻም ቅዱስ ሚካኤል ዲያቢሎስን እግዚአብሔር ይገስጽህ ብሎ ከራሱም ሰወረበት።

ሐዋርያው ይሁዳ ይህን ታሪክ ያገኘው እርገተ ሙሴ ከሚባለው የትውፊት መፅሐፍ ነው።
Source፦ the Assumption of Moses
የሐዋርያው ይሁዳ መልዕክት
ቁጥር 8

እነሆ ቤተክርስቲያንም ሐዋርያት እንዳስተማሯት እኛን ታስተምረናለች! አለንና ወደ ኋላው ዞር እያለ “ታዲያ በዚህች ቤተክርስቲያን አትኮሩም እንዴ”? ብሎ ጠቀየቀን፤ ሁላችንም ኧረ እንኮራለን” ብለን መለስንለት። የደስታ ስሜት ተነበበበትና እኔን የሚገርመኝ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? አለን ጓደኛችን፤

ምን ገረመህ”? አልነው በልባችን፤
እንዲህ ብሎ ቀጠለልን፤

እኔን በጣም የሚገርመኝ ባሕረ ጥበብ የሆነችው ቤተክርስቲያን እያንዳንዱ ሥርዓትዋ በሚስጢር የተዋቡ መሆናቸው ነው! ኧረ ሰዎች ይህችን ጥበበኛ እናት በደንብ እንወቃት፤ ከጣራ እስከ ግድግዳዋ ያስተምረናል። እኛ ለማወቅ እንፈልግ እንጂ ይህች እናት እንደዘመኑ ሴቶች የተፈጥሮ ወተትን ነፍጋን አርቴፊሻል ወተት አትግተንም!

ከላም ወይም ከሌሎች የወተት አይነቶች ይልቅ የእናት ወተት ለህፃኑ ጠቃሚ ነው፤ በተለይ እናትየው በመጀመሪያ የምታጠባው ወተት ማለትም እንገር /colostrums/ የሚባለው ለህፃኑ ጤንነትና እድገት እጅግ ወሳኝ ነው። እኛም ከእናታችን ቤተክርስቲያን የመጀመሪያውን ወተት በጥምቀት አማካኝነት ተመግበናል። ይህ ልክ እንደ ህፃኑ ለጤንነታችንና ለእድገታችን እጅግ ወሳኝ ነው!

ደግ የሆነች እናት ቤተክርስቲያን አለን፤ ወተትዋን ለማጥባት የማትሰለች ደግ እናት! ጥምቀቱ ወተት ነው ልጅነትን ያሰጣልና፤ ቁርባኑ ወተት ነው ከኃጢአት ያነፃናልና፤ ተክሊሉ ወተት ነው የትዳራችን ውበት ነውና፤
ትምሕርቷ ሁሉ ግሩም ወተት ነው ያውም ለጤንነትና ለእድገት ወሳኝ የሆነ ጣፋጭ የእናት ወተት።

የእናታችን ወተት ያስፈልገናል በሉ”!































Thursday, 19 January 2012

“ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ”

“Epiphany
God Holy might, Holy living, immortal who was baptized in the Jordan & crucified on the cross have mercy up on us.

ባሕር አየች ሸሸችም፤
ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፤
ተራሮች እንደ አውራ በግ፤ ኮረብቶችም እንደ ጠቦት ዘለሉ፤
በእንስሳት በረት ተጨመረ ፤
የንጉሥንም እጅ መንሻ ተቀበለ ፤
ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕፃናት አለቀሰ።
በግልጥ ተመላለሰ፤ እንደ ሰውም ታየ፤
በየጥቂቱ አደገ በሠላሳ ዘመን በዮርዳኖስ ተጠመቀ”
 ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ወመዝሙረ ዳዊት [መዝ 113: 3]

v  በሃገራችን ጥምቀት በግሩም ሁኔታ ይከበራል፤
ታቦታቱ ከመንበራቸው ወተው ውሃ ወዳለበት ሄደው ያድሩና ወደ መንበራቸው ይመለሳሉ። ይህ ለምን ይሆን? ቢሉ ምሳሌው ግሩም ነው፤ ይህም ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ የመጠመቁ ምሳሌ ነው ይህ በየትኛውም አለም የሌለ በሃገራችን ብቻ ያለ ድንቅ ሥርአት ነው።
v  ማየ ገቦ፦ ሀብተ ንጽህ ሀብተ ክቡር የሚሆን ቅዱስ
ሥጋውን ከኃጢአት የምንድንበትን ማየ ገቦን /ከጎኑ የፈሰሰውን ውሃ/ ሰጠን።
vጌታችን በእደ ዩሐንስ በባህረ ዩርዳኖስ ከለሊቱ በ10 ሰዓት
ተጠመቀ። ለምን ተጠመቀ ቢሉ ዲያቢሎስ አዳም ገብሩ ለዳያቢሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያቢሎስ ብሎ በሁለት ጽላት የእዳ ደብዳቤ ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል አስቀምጦት ነበረና ጌታችን በዮርዳኖስ ተጠምቆ ያንን የእዳ ደብዳቤውን ደመሰሰው። በሲኦል የነበረውን ደግሞ በእለተ አርብ ደምስሶታል፤ [በእኛ ላይ የነበረውን የእዳ ጽህፈት ደመሰሰው እንደሚል ቆላስይስ 2:11]

v                   ለመጀመሪያ ግዜ በዓለም ላይ ጥምቀትን የተጠመቀ ኢትጲያዊው ጃንደረባ [ባኮስ] ሲሆን ለመጀመሪያ ግዜ በዓለም ላይ ያጠመቀ ደግሞ ሐዋርያው ፊሊጶስ ይሆናል ማለት ነው።
      የአመነ የተጠመቀ ይድናል ማር16:16    ባኮስ ሲጠመቅ                                        
v  ጌታችን ስለምን ተጠመቀ ቢሉ አንድም ለቀድሶተ ማይ
/ውሃን ለመቀደስና/ ለቀድሶተ ጥምቀት ጥምቀትን ቀድሶ ለመስጠት ነው። አንድም ለምሳሌነት ነው፤ አንድም ዮርዳኖስ ወደ ሗላዋ ሸሸች የተባለው ትንቢት ለመፈጸም ነው። አንድም ለምን በ30 ዓመቱ ተጠመቀ ቢሉ አዳም የ30 አመት ጉልማሳ ሆኖ ተፈጠረና ገነት ርስቱን አጣት; በ30 አመቱ ያጣትን ገነትን ለመመለስ ጌታችን በ30 ዓመቱ ተጠመቀ። አንድም ስለምን ወንድ በ40 ቀን ሴት በ80 ቀን ይጠመቃሉ ቢሉ አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀኗ ገነትን አግኝተዋልና እኛም መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ በ40ና 80 ቀናችን እንጠመቃለን። 
vAnna Baptist [ዳግም አጥማቂዎች]
እነዚህ የፕሮቴስታንት ክፍሎች ሲሆኑ በሥላሴ አንድነትና ሶስትነት ስለማያምኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ከተጠመቅን በሗላ ዳግም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ አለብን የሚሉ ናቸው፤ ጥምቀት ግን አትደገምም አትከለስምም
አንድ ጌታ አንዲት ጥምቀት” እንዲል ኤፌሶን [4:4]
 


ጾመ ገሃድ፦ በጥምቀት ቀን ጾም ፈጽሞ አይጾምም፤ ጥምቀት እሮብና አርብ ቢውል እንኳን አይጾምም፤

ጥምቀት እሮብ ቢውል ማክሰኞ፤ አርብ ቢውል ሐሙስ ይጾማል።

ሐሙስ ቢውል ማክሰኞ፤ ቅዳሜ ቢውል ሐሙስ ይጾማል። ይህም የገሃድ ጾም ይባላል።

ጥያቄና መልስ፦

ለመዳን የግድ መጠመቅ ያስፈልጋል፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ስለሚል ማር16:16፤ ይህ ከሆነ ፈያታዊ ዘየማን ተጠምቆ ነው ወይስ እንዴት ነው ገነት የገባው?


መልስ

የድሮ ክርስቲያኖች ለጥምቀት በሚሄዱበት ግዜ ገና በመንገድ ላይ እያሉ ሰማዕትነት ይቀበሉና በደማቸው ይጠመቁ ነበር፤ እነዚህ ደመ ሰማዕታት ሲባሉ ዋጋውም ከፍተኛ ነው 1ኛ ዩሐ. 5:6


ፈያታዊው ዘየማን የጌታ ደም ደመ ጥምቀት” ሆኖለት
ወደ ገነት ለመግባት
የመጀመሪያው ሰው ሆኗል!!

                        
[ተክለ መድህን]


Monday, 16 January 2012

“Epiphany”



v     ደውል ተደወለ!

         ካህናቱ ተሰበሰቡ!

         መሪ ጌቶችም ለማህሌት ተነሱ!

         የሰ/ት/ቤት መዘምራን ለመዝሙር ከበሮውን አነሱ!

         ሕዝበ እግዚአብሔርም ተጠራ!

         እነሆ ጥምቀትበከተማችን በለንደን ለመጀመሪያ ግዜ  እጅግ ለየት ባለ ሁኔታ ሊከበር ነው!

         ቅ/ሥላሴ ፣ ጽ/ጽዮን ፣ ቅ/ገብርኤል ቤተክ በአንድነት በመሆን በአውሮፓ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቅ     
         በዓል ያከብራሉ፤


v     ቀንና አድራሻ፦

ከአርብ 20 Jan 7pm – ቅዳሜ 21 Jan 12 pm

St Pancras church;


Euston RD
London
NW1 2BA

Nearest station Euston /northern & Victoria line/


v     ይህ ሥርአት ግሩም ነው! እስራኤል አታውቀው አሜሪካም የላት እንግሊዝም አላወቀችው፤ እነሆ አያምልጦት! ከወገናችሁ ጋር በዓሉን ያሳልፉ፤ ኑ በአንድነትም እናክብር !!! ልጆቻችሁን አምጡና የሃገራቸውን ሐይማኖትና ባህላቸውን አሳውቁ! ካሜራችሁም በዛች ቀን ውብ የሆኑ ፎቶዎችንና ቪዲዮችን ለማንሳት እነሆ ብዙ ስራ ይጠበቅበታል!

v     በዚህ በዓል ላይ BBC እና የተለያዩ የእንግሊዝ ባለስልጣኖች ፣ የሃገሪቱ ነዋሪዎች ይገኛሉና ሃገራችንን በመልካም ጎኑ እናስተዋውቅ።

v     በለንደን የምትኖሩ ሁላችሁም ባህላዊ ነጭ ልብሳችሁን ለብሳችሁ ኑ ብላ ቤተክርስቲያን ትጣራለች!
          ከለንደን ውጪ የምትኖሩ ደግሞ ይህን ታላቅ በአል በቅርቡ you Tube ላይ ይጠብቁ!







Friday, 13 January 2012

”ጥርስና ምላስ”

አንድ ቀን ነው አሉ አቶ ጥርስ ልክ እንደ ወፍጮ ያገኘውን ሁሉ ይፈጫል ያደቃል ይከካል፤

ይህም የአቶ ጥርስ መደበኛ ሥራ ሆኖ ቀረ አሉ። ጉረቤቶቹ እነ ጨጓራና ትርፍ አንጀት “አድቃቂው” የሚል የማዕረግ ስም እስከሚሰጡት ድረስ ስሙ ከፍ ከፍ አለ። አቶ ጥርስም ስራው ፍሬያማ በመሆኑ እነሆ ደስተኛ ሆነ።

ከእለታት በአንደኛው ቀን ግን ችግር ተፈጠረ፤ አቶ ጥርስ እንደለመደው ያገኘውን ሁሉ ሲፈጭ ሲያደቅ ሲከካ ሳያስበው እትዬ ምላስን ቀረጠፋት!

ምላስም እስከምትቆስል ድረስ እጅግ ተጎዳች። እትዬ ምላስ አቶ ጥርስን እየተቆጣች “ትንሽ ምላስ ጫካን ታቃጥላለች የተባለልኝ እኔ እንዴት እደፈራለሁ” እያለች እሪሪሪ ብላ ጮኸች፤  ጮኻም አልቀረች የሰውነት ክፍሎችን ሁሉ እነ ዓይን ፣ አፍንጫ፣ ጨጓራ፤ ትርፍ አንጀትማንንም ሳታስቀር ሰበሰበችና ከዛሬ ጀምሮ ጥርስ የሚባል ነገር አያስፈልገንም! ፀባዩም ከእኛ ለየት ይላል፤ እስኪ እዩት እኛ ስስ እሱ ጠንካራ፤ እኛ ሥጋ እሱ… አለችና ከምን እንደተሰራ ሲጠፋት በቃ እሱ ሁሉ ነገሩ ከእኛ ይለያል፤ “በቃ ይወገድልን አለች እትዬ ምላስ ምርር ብላ! ሁሉም እጃቸው እስከሚላጥ አጨበጨቡ፤ ልክ ነው አቶ ጥርስ ይወገድልን እያሉም ጮኹ! ………..
መቼም አስተዋይ ሽማግሌ አያሳጣንና የተከበሩት ሽማግሌው ጨጓራ ተነሱና እስኪ እስከ አሁን ድረስ ዝም ያሉት እነ ዓይን የሚሉትን እንስማ” አሉ፤ ዓይንም ማወቅ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” ብላ እጥር ያለች መልስ ሰጠችና ተቀመጠች! አቶ ጨጓራ በዓይን መልስ ተገረሙና የራሳቸውን ሃሳብ ሰጡ፤ “የምትናገሩትን አስተውሉ! በአንድ ወቅት አይሁድ ሆሳዕና እያሉ እንዳልዘመሩና እንዳላመሰገኑ በሳምንቱ  ግን ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ! ሽባን ቢፈውስ ለምፅን ቢያነፃ አጋንንትን ቢያስወጣላቸው በቸርነት ፋንታ ይሰቀል ይሰቀል እያሉ ጮኹ!” …..

አዬ ዬ… ላይኛው ከንፈር ለክርክር ታችኛው ከንፈር ለምስክር!” እናንተም እኮ ከእነርሱ ምንም አልተማራችሁም፤ አንድ ሰሞን አድቃቂው ብላችሁ እንዳላሞገሳችሁት በሳምንቱ ይወገድልን እያላችሁ ጮኻችሁ! ይህ እኮ ነው ተረፈ አይሁድ መሆን፤ አቶ ጥርስን አመድ አፋሽ አደረጋችሁት! ጥርስ ባደቀቀው እናንተ ያለችግር ትጠቀማላችሁና አስተውሉ! እኛ እኮ ኑሯችን እንደ ሠንሰለት ነው፤ “ልብ ያሰበውን አፍ ይናገራል ዓይን ያየውን እጅ ይሰራል! አለች ሴትዮዋ እውነቷን እኮ ነው፤ አንድነት መልካም ነው! መፅሐፉም በሶስት የተገመደ ገመድ በቀላሉ አይበጠስም! ስለሚል በአንድነታችን እንበርታ! ለላም ቀንዷ አይከብዳትም” ሲባል አልሰማችሁምን? እኛ የራሳችን ቀንድ እየከበደን እኮ ነው! አሉና በልባቸው መናገር መልካም ነው ማዳመጥ ይበልጣል!” ብለው የተከበሩት ጨጓራ ዝም አሉ።

ወዲያው ግን የእነ ምላስ ጩኸት ቀጠለ፤ ልፋ ያለው በህልሙ ሸክም ይሸከማል” እንዲሉ ያ ሁሉ የአቶ ጨጓራ ንግግር ከንቱ ኾነ።
የእትዬ ምላስንና የአቶ እጅን ከንቱ ወሬ አስቀድመው የሰሙት እነ ዓይንም በጩኸቱ ተባበሩ! እንዲያውም በእነሱ ብሶ እኛ ብዙ ማውራት አንፈልግም፤ ብቻ አቶ ጥርስ ይወገድልን! አሉ፤ ለእባብ እግር የለው ለሞኝ መላ የለው” እንዲሉ መላ ከመፈለግ ይልቅ በችግር ላይ ተደመሩ! መጀመሪያ ጆሮ የገባን ከንቱ ወሬ የ10 አመት ትምህርት አይለውጠውም የሚባለው ለዚሁ ነው፤ ለማርያም መግደላዊት ፣ ለእነ ሉቃስና ቀልዩጳ ጌታችን ዳግም እንደሚነሣ 3 አመት ከ3 ወር አስተምሯቸው ነበርኮ፤ ሐሰቱ ሲበዛ እውነት ሆነ ዋዛ!” እንዲሉ የአንድ ቀን የአይሁድ ተሰርቋል” የሚለው ከንቱ ወሬ ግን ትምህርቱን በረዘባቸውና ጌታዬን ወስደኸው እንደሆነ አሳየኝ እያሉ አስቀድማ ትንሣኤውን ያየችው ማርያም መግደላዊት ተናገረች። አዬ መጀመሪያ የተሰማች ከንቱ ወሬ! መጥፎ ወሬ ይበራል መልካሙ ይተኛል” ይባል የለ፤ መጥፎ ወሬ ክንፍ አለው ይበራል፤ መልካሙ ወሬ ግን እንቅልፋም ነውና ይተኛል።

አቶ እጅም ተነሳና “ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” ይላል ሰው የተባለ ፍጡር፤ እናም አቶ ጥርስ እጅ የተባልኩትን እኔን ስለነከሰኝና ስራው ያገኘውን ሁሉ መክተፍ ብቻ ስለሆነ ምርር ብሎኛል! ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል” አለና እኔም እትዬ ምላስን እደግፋታለሁ! ብሎ ለራሱ አጨበጨበ! 
እጅ ነውና ለእራሱ ቢያጨበጭብ ማንንም አላስገረመም!

“መከራው ያላለቀለት በሬ ቆዳው ለነጋሪት ይጠፈራል” እንዲሉ የአቶ ጥርስ መከራም እንዲሁ በዛ። በዚህ ሁኔታም አቶ ጥርስ ከሰውነት ክፍል ተነቀሉና ተወገዱ፤ እነ ምላስና እጅም በሁኔታው ተደሰቱ  .   .     .      .

ብዙም ሳይቆይ ጨጓራ መጮ ጀመረ፤ “የደቀቀውን ምግብ አምጡልኝ እንጂ” እያለ ይጮኽ ጀመር። አቶ ጥርስ ተወግዷልና ምላስ ለጨጓራ የምትልከውን አጣች። አቶ እጅም ጥርስ ይወገድ! እያለ ለራሱ ያጨበጨበውን በሳምንቱ እረሳና ምን የሚያክል አጥንት ይዞ የሚግጥለትን የሚዘነጥልለትን የሚያደቅለትን መፈለግ ጀመረ፤ ለመስራት ያፈረ ለመብላት ደፈረ!

ችግሩ እንዲህ እያለ ተባባሰ፤ የጨጓራ ጩኸትም ቀጠለ…… እትዬ ምላስና አቶ እጅም እዬዬ እያሉ ምርር ብለው ማልቀስ ጀመሩ፤ ሆድ ሲሞላ ፍቅሩ ሌላ ሆድ ሲጎድል ሰው ያጋድል” እንዲሉ እርስ በእርሳቸው ተጣሉ; ሽማግሌው ጨጓራም እንዲህ ብሎ ገጠመባቸው፦

በፊት ነበረ እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ፤

የሚያደቀውንም ፈልጋችሁ ፉከራውንም ወደዳችሁ፤ ሁለት ወዳችሁ እንዴት ይኾናል? ሁለት አይወዱ ከመነኮሱ አይወልዱ” አለና መናገር ብር ነው ዝምታ ወርቅ ነው”    አለ እንደለመደው በልቡ!

አቶ ጥርስ ይህን ችግራቸውን ሁሉ አየና አዘነላቸው፤ ለረዥም መንገድ አትሩጥበት ለረዥም ነገር አትቸኩልበት!” እንዲሉ ምን ማድረግ እንዳለበት ለራሱ ግዜ ሰጥቶ አሰበበት፤ ወዲያው ፩ መፍትሄ መጣለት፤ እንዲህም አላቸው ምንም ብትበድሉኝ አብረን ሰርተናል፣ ብዙ ትዝታዎችን አሳልፈናል ሆደ ሰፊ  ይሻላል ከአኩራፊ” ስለሚባል በስራችሁ አልቀየምም አብሮ የበላና የጠጣ ሰው እስከ መጨረሻው አይቀያየምም” ሲባል ሰምቻለሁ፤ አሁንም
አብረን እጅና ጓንት ሆነን መስራት አለብን” ሲል አቶ እጅ ስሙ ስለተነሳ ደስ አለውና በረጅሙ አጨበጨበ…..      አዬ የእጅ ነገር እንዲያው በተገኘው ነገር ሁሉ ማጨብጨብ…  እራሱ ተናግሮ ለእራሱ ያጨበጭባል፤ ሌላውም ሲናገር እንዲሁ፤ እሱ እቴ ምን አለበት ሰው ግራ ይግባው ቀኝ ይግባው አይመለከተውም በቃ ማጨብጨብ ብቻ …

አቶ ጥርስ በእጅ ባህሪ ቢገረምም “አብሬያችሁ ልሰራ ፈቃደኛ ነኝ ሁለተኛ ጥፋት ቆሞ ማንቀላፋት” ስለሚባል አስቀድመን ግን ውል መፈራረም አለብን አላቸው፤ እነሱም “አንተ የፈለከውን አድርግ አጥንቱም ሥጋውም ያንተ፤ ሁሉ ተፈቅዶልሃል” አሉት። አቶ ጥርስም እነሆ ውሉ ይህ ነው “ሁላችሁም እድሜ ልካችሁን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ትሰራላችሁ እኔ ግን የአገልግሎት ዘመኔ ሲፈፀም ጡረታ መውጣት እችላለሁ” አላቸው። ግዜያዊ ችግራቸው ብቻ ስለታያቸው “ይሁን ይደረግ” ብለው ተስማሙ። አቶ ጥርስም በሉ ከዛሬ ጀምሮ ጡረታ እስከምወጣበት ቀን ድረስ አብረን “እናደቃለን እንፈጫለን እንከካለን” ብሎ በሞራል ተናገረ፤

ጭብጨባው ቀለጠ ከሁሉም ጭብጨባ ግን የአቶ እጅ ለረጅም ግዜ ሳያቋርጥ ቀጠለ ….

ለተወሰኑ አመታት አቶ ጥርስ ፣ እጅና እትዬ ምላስ አብረው ሰሩ፤ አቶ ጥርስ ጡረታ መውጫው ግዜ ደረሰ፤

እነሆ ሰው ሲያረጅ ጥርሱ የሚያልቀው ከዛሬ ብዙ አመታት በፊት በተደረገው የውል ስምምነት ነው!