Monday, 28 November 2011

ከዓባይ ጋር ኢንተርቪው

«ወይ ዓባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሕታዊ ነኝ ብለህ በረሃ ለበረሃ፣ ሸለቆ ለሸለቆ ስትመንን የኖርክ ወንዝ እዚህ ካይሮ መጥተህ ከተሜ ትሆን? እንዴው ምን ቢያቀምሱህ ነው እንዲህ የከተማ ወንዝ የሆንከው ጃል?» አልኩት ካይሮ ላይ ዓባይን ሳገኘው፡፡

«ከሀገሩ ሲወጣ ምናኔውን ብሕትውናውን ያልተወ ማን አለ? እህል አንቀምስም፣ ልብስ አንለብስም፣ ጫማ አናደርግም፣ ሬዲዮ አንሰማም፣ ሰዓት አናሥርም ሲሉ የነበሩት ሁሉ ውጭ ሀገር ወጥተው አይደለም እንዴ ከተሜ ሆነው የቀሩት? ምን በኔ የተጀመረ ታስመስላለህ?»

«ቆይ ግን አንተ ይህንን ያህል ዘመን ኖረህ ኖረህ ዛሬ ልትገደብ መሆኑን ስትሰማ ምን ተሰማህ?»

«በርግጥ ደስ ይላል፡፡ እነ ዐፄ ሐርቤ፣ እነ ዐፄ ዳዊት ያሰቡት ሲሳካ ማየት እንደገና መወለድ ነው፡፡ አይተህኛል ካይሮ ላይ፡፡ ወንዝ ሆኜ እገማደላለህ፣ ኩሬ ሆኜ ዕታቆራለሁ፣ የቦይ ውኃ ሆኜ መንደር ለመንደር እዞራለሁ፣ የመስኖ ውኃ ሆኜ ገጠር ለገጠር እንከራ ተታለሁ፡፡ የቧንቧ ውኃ ሆኜ ቤት ለቤት አዞራለሁ፡፡ የቆሻሻ መውሰጃ ሆኜ ቱቦ ለቱቦ እሰቃያለሁ፡፡ ምን ያልሆንኩት አለ፡፡»

«እናንተ ሀገርስ ዘፈን ብቻ ሆኜ ቀረሁ፡፡ ተረት ሆኜ ቀረሁ፡፡ አሁንም እንኳን ትተርቱብኛላችሁ አሉ፡፡»

«ምን ብለን የማይሆን ነገር ሰምተህ እንዳይሆን?»

«ዓባይ ማደርያ የለው ቦንድ ይዞ ይዞራል ትላላችሁ አሉ፡፡ ምናለ እንኳን ዓባይ ማደርያ ሊያገኝ ቦንድ ይዞ ይዞራል ብትሉት፡፡»

«አንተምኮ አበዛኸው፡፡ ገና ከጣና ከመውጣትህ እንዴው ገደል ለገደል ዝንጀሮ ይመስል ስትጓዝ ሰንብተህ ከሀገር ትወጣለህ፡፡»

«ሰው ለምን በረሃ እንደሚገባ፣ ለምን ገደል ለገደል እንደሚሸፍት ታውቃለህ? ሲከፋው እኮ ነው፡፡ አልመች ሲለው፡፡

ዓባይ ጉደል ጉደል ቀጭን መንገድ አውጣ
የከፋው ወንድ ልጅ ተሻግሮ እንዲመጣ
ትሉ የለም፡፡ እኔምኮ ከፋኝ፡፡

«ለምን?»
«ካይሮን አይተሃታል? እኔን ስንት ቦታ ነው የከፋፈሉኝ፡፡ ከኔ አጠገብ ቤት የሚሠሩኮ ሀብታሞች ናቸው፡፡ መርከቡ፣ ጀልባው፣ መዝናኛው፣ መናፈሻው ኧረ ስንቱ ሲገማሸልብኝ ይውላል ያመሻል፡፡ እስኪ ባሕርዳር ከተማን ሄደህ እያት፡፡ ለመሆኑ ዓባይ በዚያ የሚያልፍ ይመስላል፡፡ ገና ከጣና ስወጣ ፋብሪካ ገትራችሁ ቆሻሻ ትለቁብኛላችሁ፡፡ ደግ ነገር የጠፋ ይመስል ጅኒ፣ ዛር፣ ጋኔን የተሰበሰበብኝ አድርጋችሁ ነው የምታወሩት፡፡ እየዘለለ የገባውን ሁሉ ዓባይ ስቦት ነው ትላላችሁ፡፡

«አየህ ካይሮ ላይ የምጓዝበትን መንገድ ግራ ቀኙን አስተካክለው ጥልቀት እንዲኖረው አደረጉና መርከብ ነዱበት፡፡ አሁን ባሕርዳር ላይ እንዲህ ቢደረግ ምን ነበረበት? ጣናን አንድ ነገር ሳትሠሩ ከጥግ እስከ ጥግ ሻሂ ቤት አድርጋችሁት ቀራችሁ፡፡ እስኪ አንድ የመርከብ ላይ መዝናኛ አለ? እስኪ ምናለ ከተማዋን ወደ ምዕራብ ከመለጠጥ ወደ ምሥራቅ ወስዶ እኔን መካከል ብታደርጉኝ?

«እናም ከፋኝ ጥዬ ሄድኩ፡፡ ምን ታደርጉ ዋናው ከተማ አዲስ አበባ ውስጥ ከአሥር በላይ ወንዞች ነበሩ፡፡ ግን ምን ሆኑ? የቆሻሻ መጣያ ሆነው ነው የቀሩት፡፡ እኔኮ ምን ሆናችሁ ነው ከውኃ ጋር የተጣላችሁት? የተከራዩን ቧንቧ መዝጋት ነው እንዴ ለእናንተ የውኃ ልማት? ወንዙን አታለሙም? አፍሪካ ውስጥ እንኳን የኒጀር ወንዝ፣ የኮንጎ ወንዝ፣ የዛምቤዚ ወንዝ ያገኙትን ወግ መዓርግ እኔ መች አገኘሁ፡፡ ተወኝ ተወኝ ባክህ ክፉ አታናግረኝ፡፡»

«ይኼው ከትናንት ብንዘገይ ከነገ እንቀድማለን ብለን ተነሣንኮ»

«ባክህ እናንተ ውጭ የሄደ ስለምትወድዱ ነው?»

«እንዴት ባክህ?»

«ነዋ እናንተ ሀገር ከውስጥ ይልቅ የውጭ ስለሚከበር ነው፡፡ ምነው ለአዋሽ አትዘፍኑ? አሁን ከእኔ በላይ አዋሽ አላገለገላችሁም? ከእኔ በላይ ለሀገሩ አዋሽ አልሠራም? ችግሩ አዋሽ እና ዋልያ ከሀገር አይወጡም፡፡ እናንተ ደግሞ ሀገር ውስጥ ያለ ነገር አትወድዱም፡፡»

«ኧረ እባክህ የማይሆን ወሬ እየሰማህ አትማረር»

«ነው እንጂ እስኪ አንተ አዲስ ላፕ ቶፕ ይዘህ ግባ? አይቀርጡህም?»

«ይቀርጡኛል፡፡»

«ግሪን ካርድ ወይንም የውጭ ሀገር ፓስፖርት ያለውን ኢትዮጵያዊስ?»

«እርሱማ አንድ ከያዘ አይቀረጥም፡፡»

«ለምን?»

«እንግዳ ተቀባይ ስለሆን ነዋ»

«እንደገና ሞክር»

«ሕጉ ይሆናላ»

«ሕጉ አይደለም አስተሳሰባችሁ ነው፡፡ እዚያው ሀገር ውስጥ ሆኖ ለሀገሩ አስፈላጊውን ሁሉ እየከፈለ ከሚኖረው ይልቅ ከዕለታት አንድ ቀን ብቅ የሚለው ዲያስጶራ ይከበራል፡፡ ከጋምቤላ ከምትመጣ ከካምፓላ ብትመጣ ትከበራለህ፡፡»

«እይውልህ ዓባይ፣ አሁን ሁሉም ነገር አልፎ ሀገር ተነቃንቋል፡፡ ወሬውኮ ዓባይ ዓባይ ብቻ ሆኗል፡፡ ግብፆችን እንኳን አታያቸውም፡፡ ኢትዮጵያን እንጎብኝ ብለው የማያውቁት እንደ ጥንቱ የሕዝብ መዝሙር ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ብለው ሊሞቱኮ ነው፡፡»

«እሱ እሱንስ ሳይ አንጀቴ ይርሳል፡፡ እዚህኮ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አያውቁም ነበር፡፡ የመማርያ መጽሐፋቸው ላይኮ ዓባይ መነሻው ግብጽ ነው ብለው የሚጽፉ ደፋሮችኮ ናቸው፡፡ እዚህ ያሉ አበሾች አልነገሩህም»

«ምን?»

«እዚህ ያሉ ሰዎች ኢትዮጵያን አያውቁም፡፡ ደግሞ ጠባያቸው ሆኖ መንገድ ላይ ሲያገኙህ ሀገርህ የት ነው? ማለት ይወዳሉ፡፡ እና ሐበሾቹ ኢትዮጵያ ነው ሲሏቸው የት ነው? እያሉ ልባቸውን ያወልቁታል፡፡

«እሺ»

«እናም ሲሰለቻቸው ምን እንደሚሏቸው ታውቃለህ?»

«ከየት ነው የመጣህው»

«ከሽንኩርት፡፡»

«ሽንኩርት የት ነው?»

«ከድንች አጠገብ»

«ድንችስ የት ነው?»

«ከቃርያ አጠገብ»

«ቃርያስ?»

«ከዝንጅብል አጠገብ»

«ዝንጅብልስ?»

«ከጥቁር አዝሙድ አጠገብ»

ሁሉም ነገር አልገባው ሲል «አይ ዋ፣ አይ ዋ ዐወቅኩት፣ ዐወቅኩት» ይልና አንገቱን ነቅንቆ ያበቃል፡፡

«ዛሬማ አወቋትኮ ኢትዮጵያን፡፡ ጋዜጦቻቸው ያነሡት ጀመርኮ፡፡ መንገድ ላይ ሲያገኙህ ሐበሻ መሆንክን ሲያውቁ ይጠይቁሃል፡፡ ውኃ ልትዘጉብን ነው አሉ? ይሉሃል፡፡ ኮራሁኮ አሁንማ ሀገሬ ታወቀ፡፡»

«ያ ሁሉ ሕዝብ ግለበጥ ብሎ ደመወዙን ያወጣውኮ ይህንን ሀገራዊ ኩራት ለማምጣት ነው፡፡»

«የሕዝቡ መነሣሣት፣ አንድ ልብ መሆን፣ ቁጭት ልቤን ነካው፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው፡፡»

«ደግሞ ምን ልታመጣ ነው?»

«እይውልህ አንድ አባት ነበረ አሉ፡፡ ለልጆቹ ሀብቱን ለማውረስ ሽር ጉድ ይላል፡፡ ልጆቹ ደግሞ ከአባታቸው ሀብቱን ለመንጠቅ ሽር ጉድ ይላሉ፡፡ አንድ ቀን ለልቅሶ ሌላ ሀገር በሄደ ጊዜ ራሳቸው ቤቱን ሰብረው ሀብቱን በሙሉ ነጠቁና ለሦስት ተካፈሉት፡፡ አባትዬው ሲመጣ ሀብት ንብረቱ የለም፡፡

«በኋላ በአውጫጭኝ ሲጣራ ለካስ ልጆቹ ናቸው የወሰዱት፡፡ አባት ይህንን ሲሰማ እንዲህ አለ ይባላል «መውሰዱንስ ውሰዱት፣ ሀብታችሁ ነው፡፡ ያስቀመጥኩትም ለእናንተ ነው፡፡ የሚያሳዝነኝ ግን መርቄያችሁ ልትወስዱት ስትችሉ ረግሜያችሁ መውሰዳችሁ ብቻ ነው» አለ አሉ፡፡

«ይህ ከአንተ ግድብ ጋር ምን አገናኘው ታድያ?»

«ሕዝቡኮ ልጆቹን «ይገደብ ዓባይ» እያለ ስም ሲሰጥ የኖረ ነው፡፡ መሪ አጥቶ ኖረ እንጂ ገንዘብ አልሰጥም አላለም ነበር፡፡ አሁንም ዓባይ ሊገደብ ነው ሲባል በደስታ ነው የተነሣው፡፡ ታድያ አንዳንዶቹ በፈቃዱ መስጠት የሚችለውን በግዳጅ አደረጉትና ምርቃቱን ወደ ርግማን ቀየሩት፡፡

«እንዴት ዝቅ ብሎ የግማሽ ወር፣ ከፍ ብሎ የሁለት ወር የሚሰጥ ይጠፋል? እንዴት ሁሉም እንደ ኮካ ኮላ ጠርሙስ አንድ ይሆናል? ሕዝቡኮ ሀገሩ ነው፡፡ ይሰጣል፡፡ በራሳችን ገንዘብ እንገንባው መባሉም ልብ የሚያሞቅ ነው፡፡ ግን እወደድ ባዮች ፈቃዱን ወደ ግዳጅ፣ ምርቃቱን ወደ ርግማን እንዳይቀይሩት እፈራለሁ፡፡

« እሷኛዋ በቄላ በጊዜ ካልተከካች ልክነህ አትቆረጠምም፡፡ ግን አንተ ስታስበው ይሄ አንተን የመገደቡ ጉዳይ ጦርነት አያስነሣም ትላለሀ»
«የናንተ ሀገር ካህናት ምን እንደሚሉ ታውቃለህ?»

«ብዙ ነገር ይላሉ»

«ጅብ ከሚበላህ በልተህው ተቀደስ»

ቅዱስ ያሬድ ማነው?

 




ቅዱስ ያሬድ ማነው?
 የቅዳስ ያሬድ አባቱ አብድዩ /ይስሐቅ/ እናቱ ክርስቲና /ታውክልያ/  ይባላሉ /በሌላም በኩል አባቱ እንበረም እናቱ ትውልያ ይባላሉ የሚል ታሪክም አለ፡፡/ የትውልድ ሥፍራው አከሱም ነው፡፡ የተወለደው በ505 ዓ.ም/  ሚያዝያ 5 ቀን የሚል አለ/ ሲሆን በተወለደ በ7 ዓመቱ ወላጅ አባቱ ስለሞተ እናቱ የአክሱም ጽዮን መምህር ለነበረው ለአጎቱ ለጌዴዎን እያስተማረ እንዲያሳድገው ሰጠችው፡፡ ከአባ ጌዴዎንም ዘንድ እየተማረ ለ25 ዓመት ተቀመጠ፡፡

ሆኖም ቃለ እግዚአብሔር የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለሆነ በጣም ያዝን ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከትምህርት ድክመቱ የተነሣ አጎቱ በጨንገር ቢገርፈው በዚህ ተበሳጭቶ ትምህርቱን ትቶ ሄደ፡፡ በመንገድም ሲጓዝ ውሎ በቀትር ደክሞት ከዛፍ ሥር ዐረፈ፡፡ በዚያ ጊዜ አንድ ትል ከዛፉ ላይ ያለውን ፍሬ ለመብላት ስድስት ጊዜ በመውደቅና በመነሣት ዛፉ ላይ ለመውጣት ሞክሮ በሰባተኛው ሰተት ብሎ ወጥቶ ሲበላ ተመለከተ፡፡ እርሱም በፈጸመው የብስጭት ተግባር በመጸጸት ተመልሶና አጎቱን ይቅርታ ጠይቆ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ አጎቱም ተደስቶ ዓይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ እያለቀሰ ፈጣሪውን ለመነለት፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለቅዱስ ያሬድ ዕውቀትን ገልጾለት መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ዐወቀ፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን በተመለከተ

ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ
እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ
ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ
በብዙኀ ፃማ ዘአልቦ ሐጻጼ
መልዕልተ ዕፅ /ኮሞ/ ነጸሮ እንዘ የዐርግ ዕጼ

የሚል ዐርኬ ደርሰውለታል፡፡ ይህን አርኬ የድጓ መምህራን ጠዋት ጉባኤ ሲዘረጉ ተማሪዎቻቸውን ያስደርሷቸዋል፡፡

ከዚያም በኋላ ወደ መምህሩ ተመልሶ ትምህርቱን ቀጠለና ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ አጠና፡፡ ሢመተ ዲቁናን ቀጥሎም ሢመተ ቅስናን ተቀበለ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግእዝ፣ እዝልና አራራይን ከሦስት ወፎች/መላእክት በወፎች ተመስለው/ መማሩን ሊቃውንት ይገልጣሉ፡፡ እነዚህ በወፍ የተመሰሉ መላእክት እየመሩት ወደ አርአያም አርጎ የ24ቱን ካህናተ ሰማይ ዜማ ከተማረ በኋላ ጠዋት በ3 ሰዓት በአክሱም ቤተ ክርስቲያን «ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሣረረ ወበዳግመ አረአዮ ለሙሴ ዘከመ ይግበር ግብራ ለደብተራ» ብሎ አዜመ፡፡ ይህን ዜማ የደረሰበት ወሩ ታኅሳስ ቀኑም ዕለተ ሰኞ ነው ይባላል፡፡ የቅዱስ ያሬድ የመጀመሪያ ዜማው «አርያም» በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘ መሆኑን ለማጠየቅ የተሰጠው ስም ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ይህንን ዜማ በተመስጦ ሲያዜም ንጉሡ፣ንግሥቲቱ፣ ጳጳሱ መኳንንቱና ካህናቱ ወደ አኩስም ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው መጥተው በአድናቆት ያዳምጡት ነበር፡፡ ምክንያቱም ገደለ ቅዱስ ያሬድ እንደሚገልጥልን ከዚያ በፊት በውርድ ንባብ ከሚደረግ ጸሎትና መንፈሳዊ አገልገሎት በቀር ይህን የመሰለ ዜማ አልነበረምና፡፡

የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ብሉይን ከሐዲስ ያስማማ፣የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ የያዘ፣ እንዲሁም ለልዑል እግዚአብሔር፣ለእመቤታችን፣ለቅዱሳን መላእክት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታት ተገቢ የሆነውን ምስጋና የያዘ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ለአራቱ የዓመቱ ወቅቶች እንዲስማማ አድርጎ ለበጋ፣ ለክረምት፣ ለመጸውና ለጸደይ እንደሚሆን አድርጎ ከፋፍሏቸዋል፡፡ ለየበዓላቱም ተስማሚ ድርሰት መድቦላቸዋል፡፡ ይህንን ድርሰቱን በግእዝ፣ በእዝልና በአራራይ ዜማ ያዘጋጀው ሲሆን ለነዚህም ስምንት የዜማ ምልክቶች ሠርቶላቸዋል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማ አንዴት ሁሉንም ይመስጥና ወደ አርያም በመንፈስ ይወስድ እንደ ነበር ለማስረዳት በገድሉም በሌሎችም መጻሕፍት የተመዘገቡ ታሪኮች አሉ፡፡ አንድ ቀን ንጉሥ ገብረ መስቀል፣ንግሥቲቱ፣ ጳጳሱ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በተሰባሰቡበት ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ሲያዜም ንጉሡ በመመሰጡ የተነሣ በመሰቀል ተሰላጢኑ ጫፍ የቅዱስ ያሬድን እግር ወጋው፡፡ ነገር ግን ማንም አላወቀም ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ መዝሙሩን ሲፈጽም ንጉሡ መስቀል ተሰላጢኑን ቢያነሳው የቅዱስ ያሬድ ደሙ ፈሰሰ፡፡ ንጉሡ በዚህ ደንግጦ ለዚህ ካሣ ይሆን ዘንድ የፈለግከውን ጠይቀኝ እሰጥሃለሁ ብሎ ቃል ገባለት፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግን ከዚህ ዓለም ተለይቶ በምናኔ መኖርና መዝሙሩንም በሚገባ ማዘጋጀት እንደሚፈልግ ገለጠ፡፡ ምንም እንኳን አኩስምን ለቅቆ መውጣቱ ንጉሡን ቅር ቢያሰኘውም ቃሉን አንድ ጊዜ በመስጠቱ ምንም ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ቅዱስ ያሬድም ከዚህ በኋላ አኩስምን ለቅቆ ወደ ስሜን ተራራ ጸለምት መጓዙ ይነገራል፡፡

በጐንደር ፎገራ በሚባል ሥፍራ ቅዱስ ያሬድ ጣዕም ያለው ዜማውን ሲዘምር ተጠምደው የሚያርሱ በሬዎች ድምፁን እየሰሙ ገበሬውን ሥራ ስለ አስፈቱት በዚህ ተናዶ ቅዱስ ያሬድን በጅራፍ እንደ ገረፈው ይነገራል፡፡ ቦታውም «ወርቀ ደም´ እየተባለ እስከ ዛሬ ይጠራል፡፡ ወርቃማና ንጹሕ ደሙ የፈሰሰበት ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540-560 ዓ.ም. ባለው ጊዜ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዜማውን ካዘጋጀ በኋላ 11 ዓመት አስተምሯል፡፡ በእርሱ ዘመን ተሰዓቱ ቅዱሳን በሃይማኖት ችግር ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው መጥተው ስለ ነበር ቅዱስ ያሬድ ከአንዱ ከአባ ጰንጠሌዎን የውጭውን ሀገር ቤተ ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ይጠይቅ ነበር፡፡ በጆሮ የሰማውንም በዓይን ለማየት ሁለት ጊዜ ሮም የተባለችውን የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ጐበኘሁ ይላል፡፡ «ወሪድየ ብሔረ ሮሜ ለቤተ ክርስቲያን ርዒክዋ» እንዲል፡፡ የታሪክ ምሁሩ ሥርግው ሀብለ ሥላሴ ለቁስጥንጥንያ ዜማ መነሻው ቅዱስ ያሬድ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚያደርጉት የቁስጥንጥንያን ዜማ የደረሰው ሊቅ ዜማውን አገኘው የሚባለው የቅድስት ሶፍያን ቤተ ክርስቲያን ሲዞር ከሰማው ዜማ ነው፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ከተነሣበትና ወደ ሮሜ ሄድኩ ካለበት ዘመን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እናም ምናልባት ያ ሰው ዜማውን የሰማው የቅድስት ሶፍያ ቤተ ክርስቲያንን እየዞረ ሲዘምር ከነበረው ከቅዱስ ያሬድ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡ Ancient and medival Ethiopian History/

ቅዱስ ያሬድ ማትያስና ዮሴፍ በተባሉ የአቡነ አረጋዊ ደቀ መዛሙርት መሪነት ወደ ደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ወጥቶ ከጻድቁ ጋር በመገናኘትና የቤተ ክርስቲያኑን ሥራ እያደነቀ ዙሪያውን ከዞረ በኋላ «ዖድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፃሃ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን» ሲል ዘመረ፡፡ በዚያም ለአንድ ሳምንት ሰንብቶ ሄዷል፡፡

ቅዱስ ያሬደ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ጋር በመሆን በወሎ፣ በጎንደር፣ በሸዋ እና እስከ ጋሞጎፋ ብርብር ማርያም ድረስ በመሄድ አስተምሯል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች የዐርባ ምንጭን ታሪክ ከቅዱስ ያሬድ፣ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ታሪክ ጋር ያያይዙታል፡፡ ሦስቱም ብርብር ማርያምን ለማየት ሄደው በነበረ ጊዜ በዛሬው ዐርባ ምንሥ አካባቢ ሠፍረው ነበር፡፡ በዚያ ቦታ ለወታደሩ የሚበቃ የሚጠጣ ውኃ በመጥፋቱ አቡነ አረጋዊ ጸልየው መሬቱን በመስቀል ቢመቱት ዐርባ ውኃዎች ፈለቁ ይባላል፡፡

ዐፄ ገብረ መስቀል የጣና ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያንን በሚያሠራ ጊዜ በዚያ ቦታ ለሁለት ዓመት ተቀምጦ ድጓውን በማስተማሩ ምልክት የሌለው ድጓው እስከ ዛሬ በገዳሙ ይገኛል፡፡ ቀጥሎም የዙር አባን ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ወደ ጋይንት በተጓዙ ጊዜም በዚያ ሁለት ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት የተባለ ድርሰቱን አስተምሯል፡፡ ይህ ቦታ እስከ ዛሬ የዚህ ትምህርት ማስመስከሪያ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከዚያ በኋላ ወደ አከሱም ተመልሶ በመደባይ ታብር በተባለ ቦታ ቅዳሴያትን በዜማ አዘጋጅቷል፡፡ ይህ ቦታ ከአከሱም 15 ኪ.ሜትር ርቆ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ አኩስምን ተሰናብቶ ለመሄድ ወደ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ገባና «ቅድስት ወብጽዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን ማዕርገ ሕይወት» እያለ አንቀጸ ብርሃን የተባለውን ድርሰቱን ሰተት አድርጎ አዘጋጀው፡፡ ይህንን ድርሰት ሲያዜም አንድ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ብሎ ይታይ ነበር ይባላል፡፡




                                                                   ከአበው አንደበት           















                  

ገና ጥንት ያኔ . . . . . . .
ሰውም ሳይሰፍርባት አሜሪካ ታውቃ፣
ገና ጥንት ያኔ . . . . . . . . .
እንዲህ ሳትሠለጥን አውሮፓም ተራቅቃ፣

ገና ጥንት ያኔ . . . . . . . .
ዓለም፣ ከእንቅልፏ ሳትነቃ፣
እነ ሞዛርት እና እነ ቤት ሆቨን፣
የዜማን ምልክት ገና ሳይነግሩን፣
ያሬድ አንተ ነበርክ
የዜማን ቅማሬ የሠራህልን፣
                          . . . . . . . . . . . . . . . . . . . .
መንኮራኩር ሠርተው
ጨረቃ ላይ ወጥተው፣
አፈር ስላመጡ ዓለም ተደነቀ፣
ወሬው ተሟሟቀ፣
ከምዕራብ ተነሥቶ ከምሥራቅ ዘለቀ፣

ከሺ ዓመት በፊት ግን
ያሬድ የተባለ አንደ ሊቅ ነበረ፣
ጨረቃንም አልፎ ጠፈር ተሻገረ፣
 ሐኖስን ሰንጥቆ ሰማያት ውስጥ ገብቶ፣
አስደናቂ ዜማ ከመላእክት ሰምቶ፣
 አኩስም ላይ አዜመው
ከጽናጽል እና ከመቋሚያ አስማምቶ፣

ግና ምን ያደርጋል . . . . . . .
 ከጨረቃ አፈር የሚበልጥ ነገር፣
 ጨረቃም ላይ ካለው የሚበልጥ ምሥጢር፣
 ያሬድ ይዞ መጥቶ፣
 የሚናገር እና የሚያደንቅ ጠፍቶ፣
 ዓለም አያውቀውም አልሰማውም ከቶ፣

ያሬድ ግን ቅዱስ ነው
 ያሬድ ምሁር ሊቅ፣
 ያሬድ መተርጉም ነው
 ምሥጢር የሚያረቅቅ፣
 ያሬድ ፈላስፋ ነው
ያሬድ ባለ ቅኔ፣
ያሬድ ባለ ዜማ
የዜማው መጣኔ፣
ያሬድ ሐጋጊ ነው
ሥርዓት የሠራ፣
 ያሬድ መምህር ነው
ዕውቀትን ያበራ፣
ያሬድ ቀማሚ ነው
ብሉይ ከሐዲስ፣
ያሬድ ሰባኪ ነው
ነፍስ የሚመልስ፣
 ያሬድ አመልካች ነው
 ኖታን የፈጠረ፣
 ያሬድ መናኒ ነው
 በጸሎት የኖረ፣
       እነ ቸርችል፣ ፑሽኪን እነ ካኒንግሃም
      አደባባይ መንገድ ሲሰየምላቸው፣
      ያሬድን ስላጡት አዘነ ልባቸው፣
      ነቢይ በሀገሩ አይከብርም እንዲሉ፣
      እኒህ ኢትዮጵያውያን እጅግ ይሞኛሉ፣
     የእጃቸውን ንቀው ሌላ ያከብራሉ፣
     ብለው አዘኑብን በፈጸምነው ግፍ፣
     ያሬድን ረስተን ሌላውን ስናቅፍ፣

                                       አይበቃም ወይ ታድያ የሞኝነት ኑሮ፣
                                       መቅረት አለበት ወይ ታሪኩ ተቀብሮ፣
                                       ይተረክ ታሪኩ ይነገር ዝናው፣
                                       ይጠና ይመርመር ይታወቅ ሥራው፣
                                       መወያያ ይሁን በየሚዲያው፣
                                       መማማርያ ይሁን ትውልድ ያድንቀው፣