Saturday, 11 August 2012




ሮጥ እንደዚህ ነው በአንድ ላይ ተባብሮ
ም እና ወርቁ በአንድ ተጨምሮ
ጅም ሩጫን አየነው ዘንድሮ!
ምህርትም ሆነን ለመስራት ተፋቅሮ

ፋር ነች ጀግና ነች እውነትም ደፋር ነች
ታ አልሰጠችም ልክ እንዳሸነፈች
ግብዬ ብላ እመቤቴን ያዘች!

እልል ይበሉ የወለዱ እናትሽ
ያኔ እንደተባለው አምጠው ሲወልዱሽ
ጋሻና ጦር ያዙ ፎክሩ በሏቸው
ዘራፍ! የጀግና ልጅ! ይበሉ ደፋሩ አባትሽ!!!













ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ አባትሽ
ደፋር ነው አባትዋ ልጅቱም ደፋር ናት
አሯሯጧን ያየ በአባትዋ የወጣች “ደፋር ናት” የሚላት

ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ እናትሽ

ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
ይህን ድንቅ ስምሽ ማን ይሆን የሰጠሽ!







ሱባኤውን ይዘሽ ፍልሰታንም ጾመሽ
ድንግል እናትሽን ከደረትሽ ይዘሽ
ወላዲተ አምላክ እርጂኝ ብለሽ ለመንሽ
እልልልል ይኸው ተሳካልሽ
ታላቅ እምነትሽን በዓለም ላይ ሰበክሽ!


ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
ድፍረት ከእምነት ጋር ፈጣሪ ለገሰሽ
መሰረት እስኪ ልጠይቅሽ
ምነው ቪቪያንን ጥለሽ ብቻሽን ገሠገሥሽ?
"
ብቻውን የሮጠ ማንንም አይቀድምም"
ብቻሽን ሮጠሽ ብቻሽን አልበላሽ
መሠረት ጥሩነሽ ገለቴ ምን ልበል በሞቴ?
ፍቅር አንድነትን ህብረት መቻቻልን
እስኪ አስተምሩን ለሀገር መስራትን
"
ብቻውን የሮጠ ማንንም አይቀድምም"
ብለው አስተማሩን ድንቅ ወርቆቻችን!







ደፋር ነሽ ጀግና ነሽ እውነትም ደፋር ነሽ
ሩጫን አስተማርሽ አፈትልከሽ ሮጠሽ!
ነይ ተደሰቺ ባንዲራውን ይዘሽ
ሽልማትሽ ይህ ነው ለፈሰሰው ላብሽ!

እልል ይበሉ የወለዱ እናትሽ
ያኔ እንደተባለው አምጠው ሲወልዱሽ
ጋሻና ጦር ያዙ ፎክሩ በሏቸው
ዘራፍ! የጀግና ልጅ! ይበሉ ደፋሩ አባትሽ!!!










                                              
                                        
 ይድረስ ለታላቅዋ        


              የእምነት ሰው
     
          
                         መሠረት ደፋር!





ETV (DVD)

ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ አሪፍ ታሪክ ላውጋችኹ!

ሹርባ ልትሰራ ሄዳ ጸጉሯን ተላጭታ መጣች” አሉና ”አምራለሁ ብላ ተኩላ ዓይኗን አጠፋችው ቸኩላ” አሉ እትዬ ጣይቱ ውብ ሴት ልጃቸውን እየመከሩ። ልጅቱም በእናትዋ ወጥታ ኖሯል ጀንበር ካለች እሩት እናት ካለች አጊጥ” አለቻቸው።

የእለቱ ኢቲቪ ዝግጅቶቻችን እነዚህ ናቸው።

ዜና፦ ሲባዛ በመቶ (DVD)

ማስታወቂያ፦ ሲባዛ በመቶ (DVD)

ድራማ፦ሲባዛ በመቶ (DVD)

አጠር ብለው ረዘም ያሉ ንግግሮች፦ ሲባዛ በመቶ (DVD)

ፕሮግራሙ ሁሉ “በ DVD” ናቸው።

የሰለጠነው ዓለም ማንም የፈለገ ባለሥልጣን ቢሆን ከአጭር ደቂቃዎች በላይ የቴሌቭዥን የአየር ጊዜ አይሰጠውም። እኛ ቤት ግን አንድ የቀበሌ ኃላፊ አጠር ብላ ረዘም ያለች ታሪክ ይተርክልናል። ይህ እኛ ቤት ነው። በሰለጠነው ዓለም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን መግለጫ ቢሰጡ እንደ እኛ አጠር ብላ ረዘም ያለች ሳትኾን በቃ! አጠር ያለች ናት። ትሻልን ትተሽ ትብስን አመጣሽ” አሉ እትዬ ጣይቱ! ይባስ ብለው የወንዶቹ አስር ሺህ ፍጻሜ ካለቀ በኋላ ኢቲቪ ስንከፍት ክቡራን ተመልካቾቻችን ውድድሩ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ይጀመራል” አሉን። እስከ ዛሬ ድረስ ለካ DVD ነው የምናየው። በኢቲቪ DVD ማጫወቻ የተከተተው DVD ሲያልቅ ከእንደገና ሪዋይንድ አድርገን ጥንት ያለቀውን ሩጫ እንደ አዲስ ማየት እንችላለን። ምን ይህ ብቻ መቶ ጊዜ የሚደጋገመውም ለካ DVD ስለሆነ ነው! በጣም የሚገርመኝ ደግሞ ያቺ በዜና ላይ የምናያት የጋዜጠኞቹ ኮምፒተር ናት። እንደ አርቴፊሻል አበባ ለጌጥ የተቀመጠች ይመስለኛል። አንዳች ትኩስ ነገር ሳይነበብባት ለጌጥ የተቀመጠች አርቴፊሻል አበባ መሆንዋ እኔ ጣይቱ ገብቶኛል። ከትላንት በስቲያ በኦሎምፒክ ቻይና በዘጠኝ ወርቅ እየመራች በስድስት ወርቅ ትመራለች ተብሎ ተነግሮናል። ታዲያ ኮምፒተሩ ስራው ምንድን ነው? የኮምፒተሩ ስራማ DVD ማጫወት ስለሆነ የሚከፈትልንን እናያለን አሉ እትዬ ጣይቱ ገና በጠዋቱ!


እትዬ ጣይቱ ከአዲስ አበባ ለንደን የገቡት በቅርቡ ነበርና ለሳቸው ተብሎ ETV ዲሽ ተገጠመ። የእንግሊዘኛ ፕሮግራም ብዙም ስለማይገባቸው አይጥማቸውምና እስኪ ያችን DVD” ክፈትልኝ አሉ እትዬ ጣይቱ ስልችት ብለው። እኔም በቅርብ ያገኘሁትን DVD ከፈትኩላቸው። እትዬ ጣይቱ ግን ፍግግ እያሉ እዲያ እኔ ያልኩት የኢቲቪን DVD ነው አሉ። እኔም ከትከት ብዬ ሳቅኩና ደግሞ የምን DVD ፕሮግራም ተጀመረ? አልኳቸው። እዲያ ያን የሀገሬን DVD ክፈት አሉኝ እትዬ ጣይቱ ሪሞቱን በእጃቸው እያሳዩኝ። ከዛች ቀን ጀምሮ እትዬ ጣይቱ ባወጡለት ስም መጥራት ጀመርን። ETV ሳይሆን “DVD ብለነዋል።


እትዬ ጣይቱ ከዘራቸውን ደገፍ ብለው በሐሳብ ባቡር ተሳፈሩና እንዲህ እያሉ ታሪካቸውን አወጉኝ። ቢቢሲ ዘወትር ቅዳሜ ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ የሚያሳየው ድንቅ ፕሮግራም አለ። ፕሮግራሙ ተፈጥሮ ድንቅ ናት” ይባላል። ተፈጥሮ ከነልጆችዋ ከነውበትዋ እጇን ይዘው ቤታችችሁ ድረስ የመጣች እስኪመስላችሁ ድረስ እጅግ ይመስጣል። የአናብስትና የአራዊቱ ልብ የሚመስጥ ፍጥጫ፣ የዝሆኖች ልፊያ ፣ የዓሦች አክሮባቲክ ድንቅ ችሎታ ልብና ዓይንን ገዝቶ አፍን አስከፍቶ ያስቀራል!


በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓሦች ሲዋኙ ግርማ ሞገሥ ያለው ሻርክ ይመጣና ይፎክርባቸዋል። ሻርክ በቀን 6 የሚያህሉ ዓሦችን መብላት አለበትና እንደ ጉድ ያራውጣቸዋል!


ዓሦቹም እንደ ጉድ ይራወጣሉ!

እንደ ጉድ በግሩፕ ይከፋፈላሉ!

እንደ ጉድ ነፍሴ አይጪኝ እያሉ ውር ውር ይላሉ!

ሻርኩም የኦሎምፒክ ጅምናስቲክ ውድድር ያለበት ይመስል ለአፌ ጅምናስቲክ የሚሆኑ ዓሦች ካላገኘሁ አላርፍም እያለ እንደ ጉድ ውኃውን በትጋት ይጋልባል! ይህ ሻርክ እንደ ዋና ብቃቱ ከሆነ በኦሎምፒክ ሪከርድ ይሰብራል ተብሎለታል! በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓሦች በሚሊዮን በሚቆጠሩ ግሩፕ ተከፋፍለው ቀስ በቀስ ብቸኛ ዓሣ ይኾናሉ። ሻርኩም ይህችን ብቸኛ ዓሣ የገባችበት ገብቶ እንደጎመጀው ለአፉ ጅምናስቲክ ያደርጋታል!  ይህች የዕለቱ የመጀመሪያ አፕታይዘር ናት። አቶ ሻርክ ቢያንስ 6 ዓሦችን ካላገኘ የበላ አይመስለውምና ይህን ሂደት እንደገና ይጀምራል……      “ዓሣ የጌቶች ምሳ የገረድ አበሳ” አሉ እትዬ ጣይቱ ፍግግ እያሉ! ወዲያው ፈገግታቸው ከፊታቸው ጠፍቶ እንዲህ እያሉ ብሶታቸውን ቀጠሉ። እነዚያ በተፈጥሮ ውበት ልባቸው የከነፈ ባለሙያዎችም የውኃ ውስጥ ካሜራቸውን ይዘው የውኃን ዓለም እንደ ጉድ ያሳዩናል። ይግረማችሁ ብለው ኢትዮጵያ ገቡና ግሩም ድንቅ ተፈጥሮን አሳዩን! አንድ ትልቅ ንሥር እጅግ ከፍ ካለ በሀገሬ ተራራ ላይ ወጣና በአፉ የያዘውን አጥንት ለቀቀው። ያ አጥንት እየተምዘገዘገ መጣና ዐለቱን መታ። አጥንቱም እዬዬ ብሎ ጮኸ! እንደ ጉድ ደቀቀ! ንሥሩ ክንፉን እያማታ እንደ ጉድ ወደ ታች ተምዘገዘገ! ከአጥንቱ የወጣውን ቦን ማሮው እንደ ጉድ በላ! ከዚያም እንደ ጉድ ክንፉን እያማታ በረረ!


ይህ ነው መዝናኛ ማለት!

ይህ ነው ሊታይ የሚገባው!

ይህን ነው ለማየት መጓጓት!

ዓይን ካላዩበት ግንባር ነው” አሉ እትዬ ጣይቱ ዓይናቸውን ጨፍነው ግንባራቸውን አንዴ ኮስተር አንዴ ፈታ እያደረጉ! እትዬ ጣይቱ ጨዋታ አሳምረው ከማወቃቸውም በላይ ንግግራቸው ሁሉ በእንቅስቃሴ የታጀበ ስለሆነ ነገረ ስራቸው ሁሉ ያስቀናል። የእትዬ ጣይቱ እሮሮ ቀጠለ።  ልብ በሉ ነጮቹ ይህችን እይታ ለሕዝባቸው ለማሳየት ነው ይህን ሁሉ ባሕር አቋርጠው ኢትዮጵያ የመጡት። እኛስ? ኢቲቪዬዋ እንደምን አሉልኝ? እምዬ ኢቲቪ እንዲህ ቢያዝናኑን አሁን ምን ነበረበት? ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል” አሉ እትዬ ጣይቱ ሆዳቸውን በእጃቸው እየዳሰሱ። በእትዬ ጣይቱ ንግግር ኢቲቪ ክፉኛ አኮረፉ። ሆደ ሰፊ ይሻላል ከአኩራፊ ሲባል አልሰሙም እንዴ?” አሉ እትዬ ጣይቱ የተፈጥሮ ሆዳቸውን አየር ምገው ሰፊ እያደረጉ። በቃ! ሆደ ሰፊ ሆነው ስሙኝ። ምን መሰሎት አሁን እሺ እኛ ቤት ስንመጣስ ምን እናያለን? የባለሥልጣናትን አጠር ብለው ረዘም ያሉ ንግግሮችን? አጠር ብለው ረዘም ያሉ ማሳሰቢያዎችን? አጠር ብለው ረዘም ያሉ ውይይቶችን? ለሁሉ ጊዜ አለው አለ ጠቢቡ። አዎ ለሁሉም ቦታና ጊዜ አለው። ለእነዚህ ሁሉ ራሳቸውን የቻሉ ቦታ አላቸው አሉ እትዬ ጣይቱ ገና በጠዋቱ። መናገር መልካም ነው ማዳመጥ ይበልጣል” ብለህ ነው መሰል ዝም ብለህ ትሰማኛለህ፤ በል ተናገር ብዙ ዝምታ ይሆናል በሽታ” ብለው እንደለመዱት በአባባላቸው ወጋ አደረጉኝ። እኔም በንግግራቸው ስለተወጋሁ ሌላ ሳይጨመርብኝ መናገር ጀመርኩ።


 እትዬ ጣይቱ በእርግጥ እርሶ ያሉት  ትክክል ነው። 24 ሰአት የሚተላለፍ የፓርላማ ንግግር ያለበት ራሱን የቻለ ቻናል አለ። ያን የወደደ ያያል። 24 ሰአት የሚተላለፍ የዜና ቻናል አለ። ያን የወደደ ያያል። 24 ሰአት የሚተላለፍ የፊልም ቻናል አለ። ያን የወደደ ያያል። ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ አንጋፋ ብሔራዊ ድራማ አላቸው። ያን የወደደ ያያል።

ይህ ነው ምርጫ!
ይህ ነው መዝናኛ!

ዘወትር ቅዳሜና እሑድ ማታ የቀኑ ጨዋታ” እያሉ የእግር ኳስ ፍቅር ላለን ሰዎች ፕሪሚየር ሊጉን ያሳዩናል።

ይህ ነው መዝናኛ!
ይህ ነው እይታ!

ይህ ሁሉ እኛ ቤት ቢሆን እንዴት ውብ ነበር? እኔ ኳስ ከልቤ ብወድም አንዳቸውንም የኢትዮጲያ ተጫዋቾችን በቴሌቭዥን መስኮት አይቼያቸው አላውቅም። እዚህ ግን እነ አሌክስ ፈርጉሰን በጋዜጠኞች ይፋጠጣሉ። እነ ሩኒ እየመጡ ካሸነፉ ደረታቸውን እየነፉ ከተሸነፉ ራሳቸውን እያከኩ ይናገራሉ። አሁን ማን ይሙት እኛ ቤት ይህ እንዳይሆን ምን ይከብድ ይሆን? አልኳቸው። እትዬ ጣይቱም እሱስ ምንም አይከብድም ልፋ ያለው በሕልሙ ሸክም ይሸከማል” የሚለው ተረት ብቻ ነው የሚከብደው አሉኝ። እኔም ሳላስበው ድንገት ብሶቴ ከእትዬ ጣይቱ ብሶት ጋር ተደመረ። የቴዲ አፍሮ ዘፈን እንዳይተላለፍ ታገደ ሲባል ሰማሁ። እትዬ ጣይቱ እርሶ ምን ይላሉ? ብዬ ጠየኳቸው። እትዬ ጣይቱ ትንሽ ፍግግ እያሉ የተከለከሉ ነገሮችን የማወቅ ጉጉት የሰው ተፈጥሮ ነውና እገዳው ብዙዎች ጆሮ ሰጥተው እንዲሰሙት ያደርጋል” አሉኝ። እባባላቸው ገረመኝ። እዚህ ጋ የምንነጋገረው ዘፈን ጠምቶን ሳይሆን ስለ ብሮድካስት ነፃነት ነው።

ይህችን ጥሑፍ ጥፌ ልጨርስ ስል እትዬ ጣይቱ ሲባዛ ፕሮግራም ጀምሯል በል ክፈትልኝ አሉ። ኧረ ለመሆኑ አዘጋጆቹ ማባዛት ብቻ ነው እንዴ የተማሩት? መደመር የሚባል ሒሳብም አለኮ። ዝግጅቶችን ብትደምሩልን አንከፋባችሁም። መቀነስም የሂሳብ  ሕግ ነው። ረዘም ረዘም ያሉ ወሬዎችን ብትቀንሱ ከቶ አንከፋም። ኧረ ማካፈልም ሒሳብ ነው። ፕሮግራሞቹን እጥር ምጥን ያለች ዝግጅት ብታደርጉ ማን ይሙት እንዴት ደስ ባለን ነበር። እድለኛ አይደለንምና ማባዛት ብቻ ሆነብን። አንዷን የተቀረፀች ፕሮግራም በመቶ ተባዝቶ መቶ ጊዜ ይቀርባል። የአየር ጊዜኮ ውድ ነው። መቶ ጊዜ በተደጋገሙት ፕሮግራማችሁ ምክንያት ቴሌቭዥኖቻችን የተመጣጠነ ምግብ አጥተው እንዳይከሱ እፈራለሁ! አዬ ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል አሉ እትዬ ጣይቱ ምርር ብለው እንደለመዱት ሆዳቸውን በእጃቸው እየዳሰሱ።


መቼስ በእኔና በእትዬ ጣይቱ የብሶት ንግግር እምዬ ኢቲቪ ሳይቀየሙን አልቀረም። ክፉኛ አዝነውብን ፊታቸውን እንደ ፎጣ አጣጠፉት። በመጨረሻም ኢቲቪ ይህን አባባል ደረደሩ።




“ዕርቅ የፈለገ ንጉሥ ገበሬ ያስታርቀዋል ዕርቅ ያልፈለገን ገበሬ ንጉሥ አያስታርቀውም


ኩርፊያውም ቀረ። እኔም ዕርቅ ያልፈለገውን ገበሬ እንዳልሆን ፈራሁና ስለ ኢቲቪያችን በልቤ ይህን አልኹ።

የልብ ሳይደርስ እድሜ ይደርስ! አሉ እትዬ ጣይቱ።



Saturday, 4 August 2012

“እውነትም ጥሩነሽ”


ሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
ጫን አስተማርሽ አፈትልከሽ ሮጠሽ!
ይ ተደሰቺ ባንዲራውን ይዘሽ
ልማትሽ ይህ ነው ለፈሰሰው ላብሽ!

ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ እናትሽ!
ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
ይህን ድንቅ ስምሽ ማን ይሆን የሰጠሽ!

ጥሩነሽ እስኪ ልጠይቅሽ
ምነው ቪቪያን ጥለሽ ብቻሽን ገሠገሥሽ!?
እልልልል እኛን ደስ ብሎናል
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ አባትሽ!
ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
ወርቅ ይዘሽ መጣሽ ለእናት ሀገርሽ!!


የዕንባ ሳቅ”

“ላይፈሩ ቁጣ ከእብደት አንድ ነው ትል ነበር ንግሥት ጥሩነሽ! ቪቪያን ጥሩነሽን አልፈራትም ወርቁም የኛ ነው ጨፍሩ” ብላ ሳይኮሎጂ ተጠቅማ ነበር። ለአፍ ዳገት የለውም” አሉ እትዬ ጣይቱ። ንግሥት ጥሩነሽ ግን ሩጫ የአፍ ስፖርት ሳይሆን የሜዳ ላይ ፍልሚያ መሆኑ ስለገባት ብዙ ኃይል አላባከነችም። 

ቪቪያን “ጥሩነሽን አልፈራትም” ስትል ንግሥት ጥሩነሽ ከትከት ብላ ሳቀችና ድብድብ አይደለም በሜዳ ላይ እናያለን” ብላ በሜዳ ላይ ንግሥትነቷን አሳየችን! ብዙ የፎከረችው ቪቪያን አፍዋ ጀግና ቢሆንም እግሯ ከዳት። አፍና እግር አልጣጣም አሉ። ይህን ጊዜ ንግሥት ጥሩነሽ ከአፍ ወለምታ የእግር ወለምታ ይሻላል” አለችና ከአጠገብዋ አፈትልካ ገሠገሠች። ቪቪያን አንዳች ማድረግ አትችል ነገር ንግሥቷን ከሩቅ እያየች አይ አፌ ጉድ ሰራኝ የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም“ አለች። ንግሥት ጥሩነሽም ቀበል አድርጋ ልጅ ለእናትዋ ምጥ አስተማረቻት” ብላ ሩጫን ለቪቪያን ጥሩ አድርጋ አስተማረቻት!

ይድረስ ለንግሥት ጥሩነሽ፦ ሩጫው ሲጀመር ልቤም በፍርሃት ይመታ ጀመር።ወርቁ በእጃችን ገብቷልና መጨፈር ትችላላችሁብላ እኮ ነበር ኬንያዊቷ ቪቪያን። ይህ ደግሞ ፍራቻውን ጨመረ። ኢትዮጲያዊያን በሙሉ ልባቸው በያሉበት ይመታ ነበር። ንግሥት ጥሩነሽ እግሮቿ ሲፈተልኩ ልቧ ሲመታ እኛም በያለንበት ልባችን ይመታ ነበር። መቀመጥ አቅቶኝ ቆሜ አብሬያት በመንፈስ እሮጥ ነበር። ሳይታሰብ አፈትልከሽ ስትቀድሚ ዕንባዬም ሳላስበው ቀደመኝ። በእውነት እየዘለልኩ በዕንባ አሳቅሽኝ። የዕንባ ሳቅ ልበለው። አዎ! ንግሥት ጥሩነሽ ዲባባ ይህ ይገባሻል።

“ወርቅ ለማግኘት ወርቅ ይዞ መነሳት” ትል ነበር ንግሥት ጥሩነሽ። እውነትም ወርቅ የሆነችውን “ንግሥት ወርቅነሽን” ይዛ ተነሳች። “ንግሥት ወርቅነሽ ኪዳኔ” እውነትም ወርቅ ናት። ጥርሷን ነክሳ ለሀገርዋ የተፋለመች ታላቅ ወርቃችን ወርቅነሽ ኪዳኔ ናት። አደራ በሰማይ በምድር ዋናው ሞተር ንግሥት ወርቅነሽ እንዳትረሳብን። ወርቅነሽ ወርቁ የአንቺና የሀገርሽ ልጅ የጥሩነሽ ዲባባ ነው!


አማትባ ተነሳች ወርቅ ይዛ ንግሥት ሆነች። ንግሥት ጥሩነሽ ጥሩ አድርጋ የከፈተችው በር ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ ማነቃቂያ ነው። አሁንም እንደተለመደው ቆሜ ንጉሥ ቀነኒሳን አያለሁ። ሌሎቹም እንዲሁ በዕንባ ያስቁናል! የዕንባ ሳቅ!!”




Thursday, 2 August 2012

==>“ጾመ ፍልሰታ”<==



  
በደገኛዋ በዘመነ ሐዋርያት ጊዜ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለአገልግሎት የሚመላለሱት በደመና ተጭነው ነበርበአንድ ወቅት ከደገኞቹ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅ/ቶማስ በደመና ተጭኖ ከሀገረ ስብከቱ ከሕንድ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዝ ነበር። በዚህ የደመና ጉዞ ላይ እመቤታችን ወደ ገነት ስታርግ አገኛት። ቶማስከዚህ በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ተጠራጣሪ ሆንኩ፤ ያንቺንም ትንሣኤ ላላይ ነበር” ብሎ በጣም አዝኖ ከደመናው ላይ ሊወድቅ ፈለገ። እመቤታችንም ከአንተ በቀር ማንም ዕርገቴን አላየም ብላ አጽናናችውና የተገነዘችበትን የወርቅ ጨርቅ ወይም ሰበናዋን ሰጠችው። ቶማስም የእመቤታችንን ሰበና ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ገሠገሠ። የእመቤታችንን ሰበና ለደገኞቹ ሐዋርያት አሳያቸው። ሐዋርያቱም ለቶማስ እንደታየሽ ለእኛም ተገለጪ ብለው ጾመው ሱባኤ  ይዘው እመቤታችን ለደገኞቹ ሐዋርያት ተገልጣላቸዋለች። ይህም ፍልሰታ” ብለን የምንጾመው ልጅ አዋቂው የሚወዳት ጾም ናት።

   
እንኳን “ለጾመ ፍልሰታ” በሰላም አደረሳችሁ


“ፍልሰታ” ማለት ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡


የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማዕታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ፡፡ /መዝ 44:9/

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፦ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና በጽኑ ምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡

የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታው ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን /መግነዟን/   ሰጥታው ዐረገች፡፡

ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት። እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ “አንተ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን?” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም። ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሰበኗን /መግነዟን/ ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡ (ዲያቆኑ ከመስቀሉ ጋር የሚይዘው ጨርቅ የእመቤታችን ሰበና ምሳሌ ነው)

ሐዋርያትም ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ /ረዳት/ ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ /ዋና/ ዲያቆን አድርጐ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን ዕርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡

ቤተክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዓበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም እንድንጾም አድርጋናለች፡፡ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሳኤና ዕርገት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ልጆቼ” ይላቸው ለነበሩ ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች፣ አረጋውያንም የጾመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል፡፡

የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ /በጾመ ፍልሰታ/ ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው፤ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ በሰሙነ ፍልሰታ ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡

ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጅዋ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡

እመቤታችን ጥር 21 ቀን ዕረፍት በሆነበት ዕለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ ዕረፍት /የመቃብር ቦታ/ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው “ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች ዐረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን፤ ኑ ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው “ታውፋኒያ” የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በኅቡዕ ተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች

እመቤታችን ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣ መድኃኔዓለምን በማህጸንዋ ጸንሳ ዘጠኝ ወር ፤ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ ነቢያት አስቀድመው ስለ እመቤታችን እረፍትና ትንሳኤ በምሥጢር ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር /መዝ 131:8/ “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ብሎአል፡፡ ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡



ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሐ ምጡቀ ፤

በአእባነ ባህርይ ዘተነድቀ፤

ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደኒ ሠቀ  ፤                         


ትርጉም፦ እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል። ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል (መልክአ ማርያም)

ለደገኞቹ ሐዋርያት ለደገኞቹ አባቶቻችን ለአባ ሕርያቆስ ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች መቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን። ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን። ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ጾመ መድኃኒት ያድርግልን- አሜን ፡፡


Thursday, 26 July 2012

==>“የምክር ዓይነቶች”<==



በአንድ ወቅት ሰዎች ማማሰያን ለምን እዚህም እዚያም ድስት ውስጥ ትገቢያለሽ?” ብለው ጠየቋት። ማማሰያም ባካችሁ እኔ ያልገባሁበት ድስት አይጣፍጥም” አለች ይባላል! 


በአንድ ወቅት በታክሲ ውስጥ ተሳፍሬ እየሄድኩ ነበር። ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት የኾነውን ነገር እያሰብኩ በሐሳብ ባቡር ጭልጥ ብዬ ነጎድኩ….

     ከዛሬ 15 ዓመት በፊት “የሚሸጥ ትኩስ እንጀራ አለ ብዬ በለንደን የመጀመሪያ የሆነችውን የእንጀራ መሸጫ ሱቅ ከፈትኩ። የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ድሮስ በነጻ ልታድለን ነበር? አሉ። እኔም የሚሸጥ የሚለውን ሰረዝኩና “ትኩስ እንጀራ አለ” የሚለውን ብቻ አስቀረሁ። ሰዎቹ ግን ድሮስ የሻገተ እንጀራ ልትሸጥልን ያምርሃል? አሉ። እኔም ትኩስ የሚለውን ሰረዝኩና እንጀራ አለ” ብዬ ጻፍኩ። ነዋሪዎቹ ግን አሁንም ጤፍስ የለህም? ድርቆሽስ የለም? እያሉ ተሳለቁብኝ። ግራ ሲገባኝ አለ” የሚለውን ብሰርዘው “እንጀራ የሚለው ብቻ ቀረ። ግራ ይግባኝ ቀኝ ይግባኝ ማን ይጭነቀው እቴ አሁንም እንጀራ ምን ይሁን? አሉኝ። እኔም ማስታወቂያውን ሙሉ ለሙሉ ሰረዝኩትና ከስሬ በለንደን የመጀመሪያ የሆነችውን የእንጀራ ቤት ተዘጋች! ይኸው እኔም እስከ ዛሬ እንጀራ እንደዘጋኝ አለሁ!!

እናቴም እንደ ልጅነቴ ፀጉሬን እየዳሰሰች “ሞኝና ውኃ እንደ ወሰዱት ይሄዳል” እያለች ተረተችብኝ። እንዲያውም ለልጄ ያልሆነ ለማን ሊሆን ኖሯል ብላ የለንደንን እማ ወራ ሰብስባ የተረት ቀን አዘጋጀችልኝ። ከተረት ዘሪዎቹ እማ ወራ መካከል እትዬ ጣይቱ ምክር ሊመክሩኝ ቸኩለው እየተንደረደሩ ሲመጡ ድንገት የቤቱ ክፈፍ አደናቀፋቸውና በጭንቅላታቸው ሲተከሉ ልናያቸው ነበር። እትዬ ጣይቱ ግን እንደ መውደቅ አሉና የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ብለው አሳቁን። ወዲያው ምክር ከድሃ ነበርሽ ማን ቢሰማሽ” ብለው እንደለመዱት ወገባቸውን በእጃቸው ይዘው እያቃሰቱ የእርጅና ሳውንድ ትራክ አሰሙና ኧረ ኡ ኡ እርጅና ብቻህን ና ብለው ከአጠገቤ ተቀመጡ።  በሁኔታቸው ሁሉም ሳቁ። እኔም ከትከት ብዬ ለመሳቅ አሰብኩና ሆድ ካልሞላ ጥርስ መቼ ይስቃል” ብዬ መሳቄን ተውኩት። “ሰዎች በሚሰጡህ አስተያየት ሁሉ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ በዚህ ዓለም ላይ መኖር አትችልም” አሉኝ እትዬ ጣይቱ በሹክሹክታ። እትዬ ጣይቱ ሀገር ቤት እያሉ አጥራቸውን በእጃቸው እየነቀነቁ “የሴት ምክር የሾህ አጥር የሚሉት አባባላቸው ትዝ አለኝ። መቼስ የእትዬ ጣይቱ ምክር በለንደን ከተማ ፍቱን መፍትሄ ነው። እንዲያውም በለንደኑ ኦሎምፒክ አክራሪዎች ችግር እንዳይፈጥሩ ብዙ ምክር መክረዋል ይባላል። ምከረው ምከረው እንቢ ካለ ጣይቱ ትምከረው ይባልላቸውም ነበር!

እውነትም የምክር ዓይነቶች ብዙ ናቸው ለካ! ሁሉም ምክር ጠቃሚ አይደለም። ሁሉም ምክር ጎጂ አይደለም። በአንድ ወቅት አኪ ጦፌ ንጉሥ ዳዊት ላይ ክፉ ምክር መከረ። አኪ ጦፌ ለአቤሴሎም አባትህ ዳዊት ዮርዳኖስን ሳይሻገር አሁኑኑ ወርደን እንያዘው” ብሎ  መከረው። ታማኙ የዳዊት አገልጋይ ኩሲ ግን በደንብ ተደራጅተን ዳዊትን እንግደለው ብሎ አቤሴሎም እንዲዘገይ አድርጎ በድብቅ ዳዊት ይሸሽ ዘንድ ላከበት። አኪ ጦፌ ምክሩ እንደከሸፈበት ሲያውቅ ታንቆ ሞተ። እኔ ያልመከርኩት ምክር ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ የሚሉትን ማማሰያ ይቁጠራቸው ያልኳችሁ ለዚሁ ነው። አሁን አባትና ልጅ ካልተጋደሉ ብሎ መታነቅን ምን እንበለው? “ሰውን አትመኑ አብዷል ዘመኑ ብንለው ደገኛ ሰዎችን መበደል ይሆንብናል። ዋሽተው የሚያስታርቁ እንዳሉ ሁሉ ዋሽተው ባል ከሚስት ልጅ ከእናት የሚለያዩ አሉ። በሰው አስተያየትና በሰው ሐሳብ ብቻ ከተመራን ትርፉ ይህ ብቻ ነው። ፈሪ ከውኃ ውስጥ ያልበዋል” እንዲሉ አግባብ ባልሆነ ፍራቻ ብቻ የአቶ እገሌን ምክር “አሜን ብለን እንቀበላለን። ነፍስ ይማርና እትዬ ምክር ሞትና እድሜ ቢፈሩት አይቀርም” ይሉ ነበር። አንድ ሰው እስከ የትኛው የልባችን ክፍል ነው መግባት የሚችለው? ልባችን ሁሉም ሰው ዘው የሚልበት በር የሌለው በረት መሆን የለበትም። አንዳንዱም ያስጨነቀው ያስጠበበው ችግር የሚቀልለት በማውራት ስለሚመስለው ለሰው ሁሉ ችግሩን ዘክዝኮ ያወራል። አጅሬ ሰይጣንም ከአፉ ቃላት እየመረጠ ችግሩን ይዘከዝክለታል። እዚህ ጋ ዝምታ በራሱ ድምጽ የሌለው ገዳይ ነውና ችግራችንን ታቅፈን መታፈን አለብን ለማለት አይደለም። ብዙ ዝምታ ይሆናል በሽታ” አይደል የሚባለው። ዐይነ ስውሩ በጥለሚዮስ በኢያሪኮ ጎዳና ላይ ሲጮህ ትዝ አይላችሁም? ሰው ሁሉ ዝም በል” ሲለው እሱ ግን አብዝቶ ጮኸ። ዐይነ ስውሩ በጥለሚዮስ ለማን መጮኽ እንዳለበት ያውቅ ነበር። የኢያሪኮ ነዋሪዎች የብዙዎቹ ምክር ለዐይነ ስውር መስታወት እንደመሸለም ነበር” ወገኔ! አብዝተን መጮኽ ያለብን ወደ ላይ ነው! የሰውን ሐሳብ መስማት ባይጠላም ለምክሮች ሁሉ ግን የማጣሪያ ወንፊት ያስፈልገናል። ሞኝ ለጠበቃው ሚሥጢር ይሸሽጋል” አሉ እትዬ ምክር። ሁነኛ መካሪ አባ ወራ እና እማ ወራ አሉን። ችግሩ በሀገርም ሆነ በቤተሰብ መካሪነት ከእነሱ ጋ መጣላታችን ነው። ሞኝ ከመካሪው ዕውር ከመሪው ይጣላል” አሉ እትዬ ምክር።

ሰውየው በግ ሊገዛ በግ ተራ ወጣና ዐይኑን በግ ፍለጋ ያንከራትት ጀመር። በድንገት ጥቁርና ነጭ ዐይኑ ጥቁርና ነጭ በግ ላይ አረፈ። በጉን ስለወደደው ሊገዛው ቢፈልግም ጓደኞቹን ማማከር ፈለገ። አስተያየት እንዲሰጡትም ጠየቃቸው። አንደኛው “ላቱ አጭር ነው” አለው። ቀጠለ ሁለተኛው “ቀንዱ የከረከረ ነው” አለው። ሦስተኛውም በጉ ጥፍሩ ዘርዝሯል እየው እስኪ” አለው። ሰውየው ግራ ገባው። ግራ ቢገባው ቀኝ ቢገባው ለመካሪዎቹ ዋናው ምክራቸው መሰማቱ ብቻ ነው። በመጨረሻም ሰውየው ልቡ የወደደውን በግ እንደ ዐይነ ስውር የፊደል መቁጠሪያ በእጁ እየዳሰሰ ይህ በግ ስንት ነው?” ብሎ በግ ሻጩን ጠየቀ።

“አንድ ሺ ብር ብቻ ነው ጌታዬ በግ ሻጩ መለሰ። 

“ደግሞ አንድ ሺ ብር ብቻ ይለኛል እንዴ! በአንድ ሺ ብር በግ ከምገዛ በቅሎ መግዛት አይሻለኝም እንዴ? አለ ሰውየው በንዴት።

በግ ሻጩም ጌታዬ እኔ የማውቀው የበጉን ዋጋ ብቻ ነው፤የሚጣፍጦትን እርሶ ያውቃሉ” አላቸው ይባላል!!


ሰው ብዙ አስተያየት ብዙ የምክር ዓይነቶችን ሊሰጥ ይችላል። የሚጠቅመንንና የሚጣፍጠንን የምናውቀው ግን ያ በግ ሻጭ እንዳለው እኛ ብቻ ነን።

ከተሳፈርኩበት የሐሳብ ባቡር በድንገት ያነቃኝ የመኪናው ክላክስ ነበር። በተሳፈርኩበት ታክሲ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ይመክሩ ይዘክሩ ይከራከሩም ነበር። አንዱ ተነሳና መፅሐፍ ቅዱስ ላዘነ ሰው የወይን ጠጅ ስጡት ድህነቱን ይርሳ” ይላልና ለድህነት መጠጥ ፍቱን መድኃኑቱ ነው አለ። ቀጠለ ሁለተኛው። ላዘነ ሰው መጠጥ ያስፈልገዋል” ብሎ የታክሲ ተሳፋሪውን በሙሉ በዐይኑ እያማተረ መከረን። እንዲያውም ወይን ያስተፈስ ልበ ሰብ” ብሎ ግዕዙንም ጨምሮ ሽንጡን ይዞ ተከራከረ። ሦስተኛው ግን ላዘነ ሰው የወይን ጠጅ ስጡት ድህነቱን ይርሳ” የሚለው ጥቅስ በመፅሐፍ ቅዱስ ይኑር አይኑር አላውቅምና የምለው የለኝም አለ።

ክርክራቸውን ስሰማ ገረመኝ። አንዱ ስለ ድህነት ይናገራል ሌላው ስለ ኃዘን ይናገራል ጥቅሱ ግን ከሚሉት ጋር አይገናኝም። ነገሩ እንዲህ ነው።     


ወወይነ ይስተዩ ትኩዛን ከመ ይርስዕዋ ለኀዘን ወሕማም ኢይዝክሩ እንከ።

“ላዘነ ሰው የወይን ጠጅ ስጡት ድህነቱን ይርሳ[ምሳሌ 31: 6]

ይህ ጥቅስ ትርጓሜው ምን ይሆን? “ላዘነ ሰው የወይን ጠጅ ስጡት ድህነቱን ይርሳ” ሲል ባዘንን ቁጥር መጠጥ እንጠጣ ማለት ነውን? ከቶ አይደለም። 

ላዘነ ሰው (በንስኃ ለተመለሰ ሰው) ወይን ስጡት (ሥጋ ወደሙን አቀብሉት) ድህነቱን ይርሳ (ከእግዚአብሔር ፀጋ ተለይቻለሁ ብሎ አያስብ) ከእግዚአብሔር ጸጋ መየለየት ድህነት ነውና አሁን ግን ንስኃ ስለገባ ይህን ድህነቱን ይርሳ! [ምሳሌ 31: 6]

እነዚያ የታክሲ ውስጥ ምክር መካሪዎቹ ምን አለ የማያውቁትን አናውቅም ቢሉ? “አናውቅም አስገድሎ አያውቅም ትላለች እናቴ። ነገር ነገርን እንዲወልድ የወለደችኝ እናቴ የነገረችኝ ግጥም ትዝ አለኝ።

አንበሳ አረጀና ቤት በመዋሉ
አራዊት ተጨንቀው የት ደረሰ ሲሉ
ነብር ተነሳና ከመካከላቸው
አታላይዋ ጦጣ ክፉ ብትመክረው
እኔ ነኝ አንበሳ እጅ ንሱኝ አላቸው።

ነብር ነብር እንጂ አንበሳ እንዳልሆነ
ምንም የሚታወቅ ቢሆን የታመነ
ደፍሮ ለመናገር ሁሉም ስለፈሩ
ለነብር ማደግደግ እጅ መንሳት ጀመሩ።

ሌሎች እንዲፈሩት እንዲሰግዱለት
አንበሳ ነኝ ብሎ በዋሸው ውሸት
አመነበትና ከጊዜ ብዛት
እሱም ማን መሆኑን ጀመረ መርሳት።

አንበሳ ነኝ ብሎ ተቀምጦ ቤቱ
ሌሎችም ነህ ብለው ሲሰግዱ በፊቱ
አንበሳ መኖሩን ገና በሕይወቱ
በሩቅ ሲወራ ድንገት በመስማቱ
መሬት ጠበበችው ተቆጣ በብርቱ።

ሁሉም አምኖ እንዲኖር ነብር ያለውን
ከእሱ ሌላ አንበሳ አለመኖሩን
አዋጅ አዋጅ ብሎ ሰብስቦ ዓለምን
አንበሳን ሰደበ ከፍ አድርጎ ድምጹን።

የተኛው አንበሳ እድሜ ተጭኖት
የነብርን ስድብ ሰማና ድንገት
አጉራርቶ ቢነሳ ወኔው ቀስቅሶት
ነብር ግራ ገባው መሄጃ ጠፋው
መሬት አፏን ከፍታ ድንገት አትውጠው
ሰማይ እንዳይወጣ ክንፍ አልነበረው።


ልቡን ፍርሃት ሞልቶት እየተጨነቀ
ጥፋተኛነቱን ወዲያው ስላወቀ
አንበሳም ዘቅዝቆ አየና ነብርን
እግሩን እየሳመ ምህረት ሲለምን
ሞት ሊፈርድበት የሚገባውን
ከእግሩ ስር አንስቶ ሳመው ጠላቱን!

አንበሳ በሰራው ዓለም ተገረመ
የወንጌልን ትዕዛዝ አይቶ እንደፈፀመ።


ይህችን ጽሑፍ እንደጨረስኩኝ ቀና ስል ሰጎን እንቁላልዋን አትኩራ እንደምትመለከት አንዱ ዓይኑን ሳይነቅል ትኩር ብሎ ያየኝ ነበር። እኔ በሐሳብ ባቡር ስሳፈር ለካስ ለብዙ ደቂቃዎች አትኩሮ ኑሯል። ሞት ይርሳኝ ረሳውህ አይደል? አልኩት። አንዳች ሳይመልስልኝ አሁንም አትኩሮ ያየኛል። ሀገሬን ቤተሰቤን አስጥሎ ያሰደደኝ ትኩስ እንጀራ” ነበር አፍጥጦ ያየኝ። ምነው ያ እንዲያውም በሰዎች አስተያየትና በምክር ዓይነቶች የተዘጋው የእንጀራ ቤት ትዝ አይላችሁም? አዎ እሱ ነበር አትኩሮ የሚያየኝ። እናንተም በምክር ዓይነቶች የደረሰባችሁ ታሪክ ሳይኖር አይቀርም። “በከንቱ ምክር እኔም አለኝ ቁስል ያንተን የሚመስል፤ ሰውን ማመን ገደለኝ እኔን እየመሰለኝ” ያላችሁም አትጠፉም። ምን አልባት ታሪካቸውን የሚያካፍሉን ይኖሩ ይሆናል ማን ያውቃል።


ይህችን ጥሑፍ ጥፌ ኮምፒተሩን ላጠፋው ስል “ማነህ ልጄ እስኪ ያንን ማማሰያ አቀብለኝ” አለች እናቴ።


እኔ ያልገባሁበት ድስት አይጣፍጥም አለች ማማሰያ!” አልኩኝ በልቤ።


Friday, 13 July 2012

…….“እናት ቤተክርስቲያን ለመናፍቃን የማያዳግም መልስ አላት” …….



……. ያመነ የተጠመቀ ይድናል ይላልና ሳያምኑ እንዴት ማጥመቅ ይቻላል? ……. ሕጻናትን ሳያምኑ ሳይማሩ ነፍስ ሳያውቁ ለምን እየተጣደፋችሁ ታጠምቃላችሁ? ……. ለመጠመቅ’ኮ ማመን አለባቸው” ብላ አንድ ወዳጄ ጥቅሱን ጠቅሳ ጥያቄ ደራርባ ጠየቀችኝ ……. ማር [16:16]  

……. እህት ዓለም ጌታችን በወንጌል  ሕጻናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ብሏል……. ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ብዬ ጠየኳት……. ልጅቱ ከማሰብ በስተቀር መልስ አጣች…….

እህት ዓለም ሕጻናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ማለት’ኮ አይጠመቁ እያላችሁ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ አትከልክሏቸው ማለት ነው!! አልኳት።

ሕጻናት አይጠመቁ የሚሉ ሁሉ ይህንን እውነታ አውቀው ይፈሩ! አንድም ጌታችን ለሐዋርያቱ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ አላቸው እንጂ እድሜ እየጠየቃችሁ 30 ዓመት የሞላቸውን ብቻ አጥምቁ አላለም። አንድም ሐዋርያቱ እድሜ እየጠየቁ የልደት ካርድ እያዩ አላጠመቁም። እንዲያውም ቅ/ጴጥሮስ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ነው ብሎ ሰበካቸውና 3 ሺህ ሕዝብ አጠመቀ። ሐዋ [2:38] እዚህ ጋ ከ 3 ሺህ ሕዝብ መካከል ሕጻናት አልተጠመቁም ማለት ቅ/ጴጥሮስን ማቃለል ነው። ሐዋርያቱ እነ ቅ/ጴጥሮስ ይህን አያደርጉምና። “ሕጻናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ብሎ ጌታ አስተምሯቸዋልና ቅ/ጴጥሮስ ሕጻናት አይጠመቁ ብሎ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ አልከለከላቸውም!!

ከወዳጄ ጋ ይህን የመሳሰለውን ከተነጋገርን በኋላ በመኃል ሕጻናት አይጠመቁ ስትሉ under age መንግስተ ሰማይ አይገቡም እንዴ?” አልኳት ትንሽ ፈገግ እንድትል ብዬ። ሐሳቤ ተሳክቶ ፈገግ አለችና እንዲህ ብላ ተረተች።

አሁን ገና በራልኝ አለች እብድ ቤቷን አቃጥላ ብላ ወዳጄ ነገሩ ሁሉ ፍንትው ብሎ ገባኝ አለችኝ።


እስኪ ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ በጣም የገረመኝን ገጠመኝ ላውጋችሁ።

አንዲት እናት ልጇን ክርስትና ለማስነሳት በለሊት ቤተክርስቲያን መጣች። ይህ ምን ይገርማል? በሉኛ። ይህስ ባልከፋ የገረመኝ ወዲህ ነው። ጌታችን ሐዋርያቱን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ እንዳላቸው ካህናቱ ተሰበሰቡና

አጠምቀኪ በሥመ አብ
አጠምቀኪ በሥመ ወልድ
አጠምቀኪ በሥመ መንፈስ ቅዱስ

እያሉ ታናሽዋን ልጅ ማጥመቅ ጀመሩ።  ሚሥጢር ከተግባር ጋር አስማምታ ወንጌልን የምታስተምረን እናት ቤተክርስቲያን እንዴት ደስ ትላለች! ይህ ሁል ጊዜ ሲደንቀኝ በአንደኛው ሰንበት ደግሞ እጅግ የደነቀኝን ነገር አየሁ። እናትየው ልጇን ክርስትና ካጠመቀች በኋላ በቅዳሴ ላይ ወንጌሉን መሳለም ጀመርን። ይህን ጊዜ የክርስትና እናት ተብየዋ ወንጌሉን አልሳለምም አለች። የክርስትና እናትኮ ነሽ ወንጌሉን ለምን አትሳለሚም ብለን ጠየቅናት። ወይ ፍንክች ብላ አይሆንም አለች። እኛም ግራ ገባን። ግራ ቢገባን ቀኝ ቢገባን ልጅቱ አያስጨንቃትም። በመጨረሻም በቃ እኔ የሌላ እምነት ተከታይ ነኝ” አለችን። ክው ነበር ያልነው። ልጅቷ ጴንጤ ነበረች! የክርስትና እናት ጴንጤ ተጠማቂዋ ልጅ ደግሞ ክርስቲያን መሆኗ ነው!

ይድረስ ለካህናት”

ይህ የሚያስተምረን ሁለት ዐቢይ ነገሮች አሉ። ካህናቱ ሲያጠምቁ የክርስትና እናትና አባቶችንም የራሳቸውን የክርስትና ስም በመጠየቅ ማንነታቸውን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው። አንድም ወላጆች ጥምቀት ማለት ዝምድናን ለማጥበቅ መዛመቻ ሳይሆን ሚሥጢር መሆኑን መረዳት አለባቸው። ሚሥጢረ ጥምቀት መባሉ ከንቱ አይደለምና! የሰው መሰረቱ እናትና አባቱ” እንዲል ወላጆች፣ የክርስትና አባትና እናት ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል። መልካም ላባ ከመልካም ወፍ ይገኛልና ለልጆቻችን ክርስትናን በሚገባ ማስተማር አለብን።

ይህ ደንቆኝ ሳያባራ የሚጠየቀው ጥያቄ ደግሞ አስደመመኝ። ልጅቷ ሚሥጢረ ጥምቀትን እናስተምራችሁ እያለች እሪሪሪ…. ብላ ስታለቅስ በመገረም እጄን በአፌ ላይ ጫንኩኝ። እንዲህ አለችና በጥያቄ አፋጠጠችኝ። ጌታችን የተጠመቀው በ30 ዘመኑ ነው። እናንተ ወንድ በ 40 ቀን ሴት በ 80 ቀን የምትሉት ለምንድን ነው። ለምን? እንዴት? ወዴት? እያለች ጥያቄዋን አዘነበችው።

እህት ዓለም ብዙ ጠይቀሽኛልና እኔ አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅሽ አልኳት። ባትደሰትም ጭንቅላቷን በእሺታ ላይና ታች አወዛወዘችው።

አይበለውና 30 ዓመት ሳይሞላኝ ብሞት እጣ ፋንታዬ ምንድን ነው? ቅድም አንቺው ባመጣሽው ጥቅስ ያላመነ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል” ይላልኮ አልኳት። ማር [16:16]

ይህን ጊዜ ልጅቱ ለአርምሞ እንደዘጋ ባህታዊ ዝምታዋ በዛ።ለደቂቃዎች ዝም ብላ ቆመች። “አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው” ይላሉ የሀገሬ እማ ወራ። ጥቅሱን ያመጣችው እሷ እራስዋ ነበረች። በዝምታዋ ደቂቃዎች እሮጡ። መልስ ፍለጋ መሆኑ ስለገባኝ እስክትናገር ጠበኳትና አንችዬ ተናገሪ እንጂ አልኳት። አስባ አስባ መልሱ ቢጠፋት ሌሎቹን እጠይቃለሁ ብላ ከአጠገቤ እየበረረች ሔደች።

በሳምንቱ ከበፊቱ በዝተው መጡና አልተሸነፍንም ለማለት ጥያቄዎችን እንደ ጉድ ማውረድ ጀመሩ። ጥያቄያቸው በሙሉ እንደ ጉድ ተመለሰላቸው።

የኛ ተራ ደረሰና እኛም ጥያቄ መጠየቅ ጀመርን።


ጌታችን ለሐዋርያቱ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” አጥምቁ ብሎ አዘዛቸው። ማቴ. [28:19] ቅ/ጴጥሮስ ግን ሕዝቡን ካስተማራቸው በኋላ “ምን እናድርግ? ሲሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ተጠመቁ አላቸው። ሐዋ [2:38]

እስኪ ጥያቄ እናንሳ!

ጌታችን “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” አጥምቁ እያላቸው ቅ/ጴጥሮስ እንዴት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ተጠመቁ አለ? የሐዋርያት አለቃ ነኝ ብሎ የጌታን ትዕዛዝ ሽሮ ይሆን እንዴ? ወይስ ያን ሁሉ ሕዝብ ሲያስተምር ድክምክም ብሎት ይሆን እንዴ? ወይስ ጌታ ያዘዘውን ረስቶ ተሳስቶ ይሆን እንዴ? ለምን ይመስላችኋል እንዲህ ያለው? ብለን ጠየቅናቸው። አንዳች መልስ ጠፋ። አሁንም እንደ ባህታዊ ዝምታቸው በዛ።


እኛው ጠይቀን እኛው መለስነው።

ቅ/ጴጥሮስ የጌታን ትዕዛዝ ሽሮም አይደል ፣ ደክሞት አልያም ተሳስቶም አይደል። ሐዋርያቱ ያጠመቁት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ነውና መንፈስ ቅዱስ ስለሚመራቸው ተሳስተው አይደለም። ደም ከደም ስር ጋር እንደማይጋጭ ሁሉ የሐዋርያቱም ትምህርት ከጌታችን ትምህርት ጋር አይጋጭም። ይህ ሚሥጢር ስላለው ነው እንጂ!


“በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” ማጥመቅ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ማጥመቅ አንድ ነው። በአገዛዝ ፣ በፍርድ ፣ በሥልጣን በአምላክነት አንድ ናቸውና!  ቅ/ጴጥሮስ ለዚህ እኮ ነው “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” ተጠመቁ ማለት ሲችል በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ተጠመቁ ያለው!


አንድም ጌታችን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ “ስም አጥምቁ አላቸው እንጂ “ስሞችአላላቸውም። በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ብሎ ሦስትነታቸውን” ስም ብሎ “አንድነታቸውን” ተናገረ!


ጥምቀት ኃጢአትን ያነጻል?


በጸሎተ ሐይማኖት ላይ ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኃጢአት” እንላለን።


ትርጉም፦ ኃጢአት በሚሰረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን። ይህም ጥምቀት ኃጢአትን እንደሚያስተሰርይ ያስረዳናል። እንዴት? ቢሉ ቅ/ጴጥሮስ ኃጢአታችሁ እንዲሰረይላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ ብሏልና ጥምቀት ኃጢአትን ያስተሰርያል። ሐዋ [2:38] አንድም ሐይማኖተ አበው በአንዲት ጥምቀት እናምናለን እንዲል ጥምቀት አንዲት ናት አትከለስም አትደገምም ኤፌሶን [4:4] አንድም ንጹሕ ውኃ እረጫችኋለሁ፤ እናንተም ትነጻለችሁ። የድንጋዩን ልብ አውጥቼ የስጋን ልብ እሰጣችኋለሁ እንዲል ጥምቀት ኃጢአትን ያስተሰርያል። ሕዝቅኤል [36:25]


ጥምቀት ከኃጢአት እንደሚያነጻ አይተናል። ሕጻናቱ የሚጠመቁት ግን ኃጢአትን ሰርተው ሳይኾን ከአዳም ጀምሮ በዘር የሚተላለፈውን ኃጢአት /ጥንተ አብሶ/ original sin ለማስተሰረይ ነው። “በአንድ ሰው ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ” እንዲል የአዳም ኃጢአት በሁላችንም አለ። ሮሜ [5:12] ሕጻናቱ ከዚህ ኃጢአት የሚነጹት በጥምቀት ነው!! የዘመናችን ሰዎች ልጆቻቸው እንዴት ይሆን ከዚህ ኃጢአት የሚነጹት? ኧረ ባካችሁ ሕጻናት መንግሥተ ሰማያት ይገቡ ዘንድ አትከልክሉ። 


አንድም ሕጻናት ሲጠመቁ ልብ ብላችሁ ካያችሁ ካህኑ ሕጻኑን ሦስት ጊዜ ውኃ ውስት ብቅ ጥልቅ ያደርገውና በሦስተኛው እንደወጣ ይቀራል። ይህ ግሩም ሚስጢር አለው። ሦስት ግዜ ብቅ ጥልቅ ማለቱ ጌታችን በመቃብር የማደሩ ምሳሌ ነው። ሕጻኑ በሦስተኛው እንደወጣ ይቀራል፤ ይህም የጌታችን ትንሳኤ ምሳሌ ነው። ቅ/ጳውሎስም ሞቱን በሚመስል ሞት ከሱ ጋር ከተቀበርን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ከሱ ጋር እንነሳለን ብሏል። ሮሜ [6:3] ፣ ቄላስይስ [2:11] ቤተክርስቲያናችን ወንጌሉን እንዲህ ተርጉማ በተግብር ታስተምራለች!


ሰባቱ ሚሥጢረ ቤተክርስቲያን ስማቸውንና ትርጉማቸውን ለማወቅ የሚያረዳ ግሩም ዘዴ አለ። እስኪ ይህን ዘዴ ኤፍራታ በምትባል ሕፃን በምሳሌ አብረን እንይ።

1. ጻን ኤፍራታ ገና እንደተወለደች በሰማንያ ቀኗ ትጠመቃለች። (ሚሥጢረ ጥምቀት)

2. ከጥምቀት በኋላ ወዲያው ሜሮን ትቀባለች (ሚሥጢረ ሜሮን)

3. በመቀጠል ትቆርባለች (ሚሥጢረ ቁርባን)

4. ከፍ ስትል በኃጢአት ብትወድቅ ንስሐ አለ። (ሚሥጢረ ንስሐ)

5. ንስሐ ለነፍስ ነው፤ በሥጋ ስትታመም በቀሳውስት የምትቀባው ቅዱስ ቅባት አለ (ሚሥጢረ ቀንዲል)

6. ከዚህ ሁሉ በኋላ ኤፍራታ ለጋብቻ ስትደርስልን ታገባለች። (ሚሥጢረ ተክሊል)

7. ወይዘሪት ኤፍራታ ይህንን ሁሉ ሚሥጢራት የፈጸመውን ካህን በሠርጓ ላይ ትጠራዋለች። (ሚሥጢረ ክህነት)


ሕጻናት አይጠመቁ የሚሉ ሁሉ ይህንን እውነታ አውቀው ይፈሩ! …….“እናት ቤተክርስቲያን ለመናፍቃን የማያዳግም መልስ አላት” …….