Saturday, 11 February 2012

                        “እናታችንን ለሁለት እንካፈላት!”




ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ ታሪክ ልንገራችሁ፤








በነገሥታት ዘመን ነው አሉ አንዲት ደግ እናት ሁለት ወንድ መንታ ልጆችን ወለደች፤ ሁለቱም ካደጉ በኋላ አንደኛው ልጇ እጅግ ደግና ታዛዥ ሆነ፤ “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደ ነብር ፀጉር” እንዲል ሁለተኛው ልጇ ግን ከንቱ ልጅ ሆነ። ይህን ግዜ ያቺ ደግ እናት በጣም ተጨነቀች፤ እናት ናትና በሕጻንነቱ እንደምታደርገው ፀጉሩን እያሻሸች ያንን ከንቱ ልጅ ብዙ መከረችው፣ አስመከረችውም። ያ ልጅ ግን የከንቱ ከንቱ ሆኖ ቀረ። ከፍ ሲልም በወንድሙ ላይ ተነሳሳ፣ እናቱንም ጠላት። ከዕለታት በ፩ኛው ቀን ተነሳና “ሩቅ ሀገር መሄዴ ነው፤ እናቴን ግን ማጣት አልፈልግምና በሰይፍም ቢሆን ተቆርጣ ከወንድሜ ጋር ለሁለት እንካፈላት”! አለ፤ የሰፈሩ ሰዎች ጉድ እንግዳ ነገር ብለው እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጫኑ፤ ሽማግሌዎችም ነገሩ አስጨነቃቸው፤ ትዕቢተኛንና ወራጅ ውሃን ቆመህ አሳልፍ እንዲሉ ጉዳያቸውን ወደ ንጉሡ አስተላለፉት፤ ንጉሡም እንደ ንጉሥ ሰለሞን ጠቢብ ነበርና ይህችን ደግ እናት ለደጉ ልጇ እንድትሆን ፈርዶ ያ ከንቱ ልጅ ግን ልብ እስከሚገዛ ድረስ እንዲቀጣ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ይህች ደግ እናት ቤተክርስቲያን ናት፤ ደጉ ልጅ ታማኝ ክርስቲያኖች ሲሆኑ እናታችንን ለሁለት እንካፈላት ያለው ልጅ ደግሞ “ተሐድሶ” ናቸው፤



 እናታችንን ለሁለት እንካፈላት!

ተሐድሶዎች የሕንድ ቤተክርስቲያንን ለሁለት ለመክፈል የተጠቀሙበት ታክቲክ እጅግ ግሩም ነው! ይህንኑ ስልት አውሮፓዊያኑ በተሐድሶ ስም በኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ላይ ለመድገም እነሆ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ለእኔ ብለህ ስማ እንዲሉ በሕንድን ቤተክርስቲያን ታሪክ የተሐድሶን እንቅስቃሴ እናያለን፦


ተሐድሶዎች በሕንድ ቤተክርስቲያን ተመሳስለው ገቡና ብዙ ደጋፊዎችን አፈሩ፤ ከጳጳሳት ፣ ከካህናት፣ከሰባኪያን ፣ከዘማሪያን፣ ከምዕመናን ግማሽ የሚያህለውን በራሳቸው እጅ አስገቡ። ድምጻቸውን አጥፍተው ውስጥ ለውስጥ ተስፋፉ። “ልብ ያሰበውን አፍ ይናገራል፤ ዓይን ያየውን እጅ ይሰራል” እንዲሉ እያደር የተሐድሶን ስራቸውን በግልጽ መስራት ጀመሩ፤ በመጨረሻም የሚገርም ጥያቄ ጠየቁ፤ “እኛ ተሐድሶን እንፈልጋለንና የሕንድ ቤተክርስቲያንን ከኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ጋር ለሁለት እንካፈላት!” ብለው ጮሁ፤ በየቤተክርስቲያኑም ረብሻ ፈጠሩ። ይህን ግዜ መንግሥት የሕንድ ቤተክርስቲያንን ንብረት ቆጠረ፣ ስንት ቤተክርስቲያን እንዳሉ፣ ስንት ገዳማት፤ ስንት ጥሬ ገንዘብ እንዳላቸው ቆጠረና እንዳለ ለሁለት ከፍሎ አከፋፈላቸው!

እንግዲህ ይህች ቢላዋ ናት በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ላይ እየተሳለች ያለችው! ይህች ቢላዋ ስትሳል አልሰማችሁምን? ካልሰማችሁ ጥሩ ጥሩ የተሳሉ ቢላዎች አሉና በመቀጠል እናያቸዋለን፤

ተሐድሶ ልክ በሕንድ ቤተክርስቲያን ላይ በተጠቀሙት ፎርሙላ መሰረት የራሳቸውን ግሩፕ ከሰበሰቡ በኋላ ከቀሪው የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ጋር መለየታቸውን በግልጽ ያሳውቃሉ፤ ከዛም የኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ትገባኛለች እያሉ ይጮሃሉ ማለት ነው! በሕንድ ቤተክርስቲያን ላይ እንዳደረጉት ሁሉ መንግሥት ቤተክርስቲያኒቷን ለሁለት እንዲያካፍላቸው ታላቅ ምኞታቸው ነው!


ከዚህ በተጨማሪ ተሐድሶ የሚጠቀሙበት ስልት ቤተክርስቲያንን ከሁለት አቅጣጫ ለመሳብ ሁለት ኃይሎችን በመጠቀም ነው፤
ይህም ከውጭ ወደ ውስጥ /በግልፅ ተሐድሶ ያስፈልጋል እያሉ የሚናገሩ ኃይሎች ሲሆን/ ሁለተኛው ኃይል ደግሞ ከውስጥ ወደ ውጭ /ተመሳስሎ በውስጥ የሚያገለግሉ ኃይሎች ናቸው/
ለዚህ ነው “የትግሉን ሜዳ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማድረግ አለብን፤ ከቤተክርስቲያን መውጣት ቀረ” እያሉ የሚፎክሩት።

እናታችንን ለሁለት እንካፈላት!

ይህን የረጅም አመት ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ብዙ ድርጅቶችን በኢትዮጲያ ከፍተዋል፤ ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን ማወቅ ግዜው ግድ ይለናል፦

/1/ ሐይማኖተ አበው፦ ይህ ማህበር የተቋቋመው በ1951 ዓ.ም ሲሆን እስከ 1963 ዓ.ም ድረስ የመናፍቃንን ስራ ሲቃወም የቆየ በጎ ማህበር ነበር፤ ይህን ስራውን ያዩ ተሐድሶዎች ግን ማህበሩን የዓለም ክርስቲያን ተማሪዎች /World Christian students federation/ አባል እንዲሆን አደረጉት፤ ቀስ እያሉ ሙሉ በሙሉ ወደ ራሳቸው አላማ አሰጠሙት!  ብዙ ጥፋት ካጠፉ በኋላ በ1980 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሐይማኖት ሰብሳቢነት ቅዱስ ሲኖዶስ ተሰብስቦ ማህበሩን ዘጋው፤ በ1983 ለውጡን ተከትሎ ዘው ብሎ ወደ ቤተክርስቲያን ገባ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የዘጋውን በራሱ ፈቃድ እንዴት እንደገባ ሲጠየቅ ችግሬን አስተካክያለሁ ብሎ ነበር። ነገር ግን የተሐድሶን ልብስ ባለመቀየሩ ምክንያት በ1984 ዓ.ም በድጋሚ በሲኖዶስ አዛዥነት ተዘጋ። ዛሬስ? ይህ ሁለት ግዜ በሲኖዶስ የተዘጋ ማህበር ዛሬም የተሐድሶ ልብሱን እንደለበሰ በ2000 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ 50ኛ ዓመቱን እንዲያከብር ተፈቅዶለታል፤ የጋዜጣ ቢሮና የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ተደርጓል።

/2/ የመነኮሳት ማህበር፦ በ1990 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል ቆባቸውን እንደ ኮፍያ እያውለበለቡ በዘለሉት የስም መነኮሳት የተመሰረተ ነው። በኋላ መበታተን ቢያጋጥማቸውም አሁን ግን በአሜሪካ ቤተክርስቲያንን የመከፋፈል ስራቸውን በፍጥነት እያቀላጠፉት ይገኛሉ።

ብዙ የተሐድሶ ማህበራት ቢኖሩም ከብዙ በጥቂቱ ከረጅሙ በአጭሩ እነዚህ ናቸው፦ ማሕበረ በኩር፤ጮራ፣ፍኖተ ሕይወት ማህበረ መድኃኔ ዓለም፣የምሥራች አገልግሎት በኢትዮጲያ፣ ከሣቴ ብርሃን ….

እነዚህን የተሐድሶ ማህበራት በበላይነት ይዤ በአጭር ግዜ ውስጥ የኢዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በእጄ አስገባታለሁ! እያለ የሚፎክር የእንግሊዝ ፕሮቴስታንት ድርጅት ብቅ ብሏል!ይህ ድርጅት የሕንድ ቤተክርስቲያንን በመክፈል ሰይጣናዊ ልምድ ያለው ነው።



መርፌ የራሷን ቀዳዳ ሳታይ የሌላውን ቀዳዳ ትጠቅማለች!

አውሮፓዊያኑ ግብረ ሰዶማዊነት ኃጢአት አይደለም የሚባልበትንና ሰይጣን የሚመለክበትን ሃገር ይዘው ወደ ኢትዮጲያ መጡና ቤተክርስቲያን ትታደስ አሉ! ይህ ነው መርፌ የራሷን ቀዳዳ ሳታይ የሌላውን ቀዳዳ ትጠቅማለች! የሚያሰኘው። መጽሐፍ ቅዱስን ለድሃ ሃገራት በነጻ የሚያድሉትስ ለመጽደቅ ነውን? ይህ “ኦ ዓቃቤ ሥራይ ፈውስ ርእሰከ” ያሰኛል፤ ሉቃስ [4: 23] ለራሳቸው ጽድቅና ኩነኔ አለ ብለው የማያምኑ ሲሆን ከገንዘባቸው ከፍለው ለእኛ ሐዋርያ የሚልኩልን እነሱ የማያምኑበትን ጽድቅ ለእኛ ከየት አስበው ሊያሰጡን ይሆን? ይህን ማሰብና መጠየቅ ያለባቸው እነሱ ሳይሆን እኛ ነን፤ እነሱማ ስራቸውን እየሰሩ ነው።


“የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአፍሪካዊያን”
የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአፍሪካዊያንና በካረቢያን እጅግ እየተፈለገች ነው፤

አውሮፓዊያኑ በሃይማኖት ስም አፍሪካዊያንን ወደ ሃገራቸው በመውሰድ ስቃይ ስላበዙባቸው አፍሪካዊያን በአውሮፓዊያኑ ላይ ጥላቻ አድሮባቸዋል፤ በዚህ ምክንያት አፍሪካዊያኑ የአባቶቻቸውን እምነት ፍለጋ ሲባዝኑ ኖሩ፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሐዋሪያዊ ቅብብሎሽን ጠብቃ የቆየች ጥንታዊት መሆኗን ስለሚያውቁም መብራት እያበሩ ኢትዮጲያን ፍለጋ መጡ!
እኔ ባለሁበት በለንደን ከተማ እንኳን የካረቢያን ወገኖቻችን ወደ ኢትዮጲያ በመሄድ ዋልድባ ገዳም ገብተው ሥርአተ ቤተክርስቲያንን ክህነትንና ዲቁናን ተምረው የመጡ ብዙ ሰዎች አሉ፤ እነዚህ ወገኖቻችን በቅዱስ ሲኖዶስ ፍቃድ በእንግሊዝ ሃገር ቤተክርስቲያን ተመስርቶ ብዙ ወገኖቻቸውን እያስተማሩ ነው።  ካህናቱና ዲያቆናቱ ድምጻቸው እንኳን ሲሰማ ግሩም የቤተክርስቲያን ጣዕም አለው!


የኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ከጠነከረች አፍሪካዊያን በጥላዋ ይጠለላሉ፤ ስለዚህም ይህችን ተስፋ የተጣለባትን ቤተክርስቲያን አውሮፓዊያኑ ተረባርበው ማጥፋት ይመኛሉ፤ ይህንንም ለመፈጸም እየሰሩ ነው። IMF ውስጥ ለ12 አመታት በከፍተኛ ኃላፊነት ሲሰራ የነበረው ቡድሆ የተባለ አንድ ሰው የሰራቸውን ስራዎች እንዲህ ገልጾታል፦
I may hope to wash my hands of what in my mind eye is the blood of millions of poor people; the blood is so much; you know it runs in rivers. Sometimes I feel that there is not enough soap in the whole world to clean me.
/New york new Horizons press, 1990/

/በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ላይ ያለኝ ደም እንደ ወንዝ ይፈሳል እጅግም ቡዙ ነው፤ አንዳንዴ ሳስበው ይህን ደም ከእጄ ለመታጠብ በአለም ላይ ያሉ ሳሙናዎች የሚበቁ አይመስለኝም/

+++ ከእኛ ምን ይጠበቃል? ድርሻችንስ ምንድን ነው? +++

/1/ ዋናው የተሐድሶ አላማ የሕንድን ታሪክ በኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ላይ መድገም ነው፤ ይህን ለማድረግም ከላይ እንዳየነው ብዙ ደጋፊዎችን በማሰባሰብ ቤተክርስቲያኒቷ ትገባኛለች ብለው ለሁለት እንድትከፈል እጅግ ይጎመጃሉ፤ ስለዚህም የሰባኪ ደጋፊ ፣የመዘምራን ደጋፊ በአጠያላይ የግለሰብ ደጋፊ መሆን እንደሌለብን ከምንግዜውም በላይ ልናውቅ ይገባናል!

/2/ ይህን የተሐድሶ አላማ በሚገባ ነቅቶ መከታተልና በሚገባ ተገንዝቦ ለሌሎችም ማሳወቅ! /ለምሳሌ ይህችን ጽሁፍ በኢሜልም ሆነ በፌስ ቡክ ላይ ሼር ማድረግ እንደ ምሳሌ ሊታይ ይቻል ይሆናል/

/3/ ተሐድሶዎች ቤተክርስቲያንን እንዳይከፍሏት ነቅቶ መጠበቅ! ምንም አይነት እድልም አለመስጠት።

/4/ ሰ/ት/ቤቶችንና ጉባኤዎችን በቅርብ መከታተል፤ በፌስ ቡክ የምናነባቸውን የግለሰብ ጽሁፎች የተሐድሶ አንደበት እንዳልሆኑ ለይቶ ማወቅ፤ ሥጋ በል ዕጽዋት አሉና ነቃ ብሎ ማየት!

/5/ የእምነት ጸሎት ኃይልን ታደርጋለች እንዲል ስለቤተክርስቲያን ሠላምና አንድነት፤ ከፈተናም እንድትጠበቅ አጥብቆ መጸለይ! በአጠቃላይ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያኒቷ ታማኝ ልጆች በሙሉ በዚህ ወሳኝ የፈተና ወቅት ሁሉንም የሥራ ድርሻ ለመስራት ቆርጦ መነሳት፤

ለቤተክርስቲያናችን “ሰላም ክብርና ሞገስ”
ለዘለዓለም ይሁን አሜን!!!
-//-

Friday, 3 February 2012

ነነዌ እና ዮናስ፦

ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ ፩
  
ለነብዩ ዮናስ የእግዚአብሔር ቃል መጣ
ነነዌን ለመስበክ ተነሳና ውጣ
በህዝቡ ኃጢአት ቁጣዬ እንዳይመጣ

ነብዩ ይህን ግዜ በልቡ አሰበ
የጌታ ባህሪው ይቅርታ እንደሆነ
ዮናስ ወደ ተርሴስ መኮብለል ወደደ
ወደ ከተማይቱ ምታልፍ መርከብ አየ
ዋጋም ከፈለና በመርከብ ተጓዘ።

ማን ይኮበልላል ከእግዚአብሄር መዳፍ
ወደ ጥልቁ ቢሄድ እንደንስር ቢመጥቅ
ጌታ ሁሉን ገዝቷል በኀይልና ክብሩ
ታላቅ ንፋስ መጣ ማዕበልን ይዞ
መርከቡን ቢያናውጥ ሁሉም እጅግ ፈሩ
እንዲቀልላቸው እቃቸውን ወደ ባህር ጣሉ
ወደ አምላካቸው አበርትተው ጮሁ
በጉዞው ከባድ እንቅልፍ ይዞት
ኮብላዮ ነብይ ይህን ሁሉ አላየም
የመርከቡ አለቃ ወደ ዮናስ ቀርቦ
ምነው ተኝተሃል ስንጠፋ ዝም አትበል
ሁሉ እንደለመነ ፈጣሪህን ለምን
ደግሞም ይህ ነገር በማን እንዳገኘን
በመካከላችን እጣ እንጣጣል
እጣውም ተጣለ በዮናስ ደረሰ
ማበሉ ፀጥ እንዲል ወደ ባህር ተጣለ።
በፈተና ግዜ መውጫው ይሰጠናል
ዮናስ በባህር ውስጥ አሳ ታዞለታል
በአሳ ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ጮኸ
በአምላኩም ተሰማ ባህር ተሻገረ
ወደ አምላካቹ ኑ ተመለሱ እያለ
ታላቋን ከተማ ነነዌን ሰበከ
ንጉስ ለአምላኩ ክብሩን አዋረደ
ትንሹም ትልቁም ወደ አምላኩ ጮኸ
፫ ቀን በነነዌ ታላቅ ፆም ታወጀ
ጌታም ለዛች ሀገር ምህረትን ሰጠ።

ነብዮ ከፀሐይ ሊጠለል ወደደ
በ፩ ቀን ተክል እጅግ ተደሰተ
በንጋታው ቢያጣታ እጅግም አዘነ
ጌታም መለሰለት እንዴት እንደሆነ
አንተ ላልዘራኸው ምታዝን ከሆነ
እኔም ለህዝቤ አዘንኩ አይተህ ተማር አለ።

“የዓሣ ሆድ ውስጥ ፀሎት”
ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ
ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ፀለየ፤ እንዲህም አለ፤
ተጨንቄ ሳለሁ ወደ እግዚአብሔር ተጣራሁ፤
እርሱም መለሰልኝ፤

ከመቃብሩም ጥልቅ እርዳታን ፈልጌ ጠራውህ፤
አንተም ጩኸቴን ሰማህ፤
ጥልቅ ወደ ሆነው ወደ ባህሩ መካከል ጣልኸኝ
ፈሳሾችም ዙሪያዬን ከበቡኝ፤
እኔም ወደ ቅዱስ መቅደስህ እመለከታለሁ አልኩ
አቤቱ ጸሎቴ ወደ መቅደስህ ትግባ

እግዚአብሔር ዓሣ አንበሪውን አዘዘው
እርሱም ዮናስን በየብሱ ላይ ተፋው!!!
    ትንቢተ ዮናስ ምዕ. [፪ -ፍ]

ለአጽዋማትና ለበአላት መሰረታቸው ነነዌ ነው፤
ጾመ ነነዌ ፣ ዐብይ ጾም ፣ ጾመ ሐዋርያት ሁል ግዜ በሰኞ ቀን ይጀምራሉ።
ደብረ ዘይት ፣ ሆሣዕና ፣ በዓለ ትንሣኤ ፣ በዓለ ሃምሳ ደግሞ ሁል ግዜ በእሁድ ይውላሉ።
ርክበ ካህናትና ጾመ ድህነት ሁል ግዜ ረቡዕ ቀን ይውላል። ስቅለት ሁል ግዜ በአርብ ቀን ፣ ዕርገት ደግሞ ሁል ግዜ በሐሙስ ቀን ይውላል። ጾመ ነነዌ የበረከት ጾም ይሁንልን ፤ አሜን።
     ወሥበሐት ለእግዚአብሔር [ተክለ መድህን]

Friday, 27 January 2012

             “የእናታችን ወተት ያስፈልገናል በሉ”!

ዘና ብላችሁ ተቀመጡና እስኪ ገጠመኜን ላውጋችሁ፤
የዛሬው ገጠመኜ ካለሁበት ከተማ ከለንደን ነው ፤
ግዜው የፈረንጆቹ ሰመር ነበርና የጠዋቷ ፀሐይ ፈካ ብላ ወጥታለች። የከተማዋ ሰዎችም እድለኛ ናቸውና ብዙ የመዝናኛና የእስፖርት መለማመጃ ትላልቅ ፓርኮች አሏቸው። ብዙዎቹ የፀሐይ መከላከያ መነፅራቸውን በቄንጠኛው አድርገው በየሜዳው ተዘርረዋል፤


ከአጠገባችን የተቀመጡ ሰዎች በእጃቸው ላይ የያዙትን መፅሐፍ ቅዱስ ገልጠው ይወያያሉ፤ በተወሰኑ ወጣቶችም ተከበዋል። እኛም ለማየት ያህል ቀረብ አልን፤ በመጀመሪያ ጆሯችን የገባው “ወንጌል አንዲት ናት እናንተ ግን ገድል ተዓምር እያላችሁ ብዙ መፅሐፍ አላችሁ; ይህን ሁሉ ከየትኛው ወንጌል አምጥታችሁ ነው የፃፋችሁት” የሚል ነበር።
    


ከመካከላችን አንዱ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰላቸው፤
ጥያቄያችሁን ለመመለስ ያህል ወንጌላዊው ማቴዎስ እንዲህ ይልላችኋል አለና ከሞባይሉ ላይ የጫነውን ማስታወሻ አነበበላቸው፦ “በነብያት ናዝራዊ ይባላል ተብሎ የተነገረው ይፈፀም ዘንድ ናዝሬት ወደ ምትባል ከተማ ገብቶ ኖረ” [ማቴ. 2: 23] ይህን ካነበበ በኋላ ቀና ብሎ አየና እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦

ናዝራዊ ይባላል ብሎ የተነበየው ነብይ ማን ነው? በየትኛው ትንቢት ላይስ ይገኛል?

ግሞሾቹ ዝም አሉ ሌሎቹም ከማስታወሻቸው ፈለጉ፤ አንዱ ግን ከኋላ ሆኖ መፅሐፍ ቅዱስ ሲያገላብጥ አየው።

ብዙ አትድከሙ ይህን ትንቢት በመፅሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ብትፈልጉት አታገኙትም! እነሆ ነብያቱ “ናዝራዊ ይባል ዘንድ ናዝሬት ወደ ምትባል ከተማ ገብቶ ኖረ” ብለው ተንብየው ነበር፤ ይህ ትንቢት በነብያት ተነግሮ በምርኮ ግዜ በጠፉት መጻሕፍት የነበረ ሲሆን መጽሐፍቱ ቢጠፉም በቃል ለሐዋርያት ደርሷል። እነሆ ማቶዎስም በወንጌሉ ፃፈው!

አንድም ሙሴን የተቃወሙትን ጠንቋዮች ስማቸውን አልነገረንም፤ ቅ/ጳውሎስ ግን “ኢያኔስና ኢያንበሬስ” ብሎ ስማቸውንም ጭምር ተናግሯል [2ኛ ጢሞ. 3: 8] ማን ነገረው? እነሆ በትውፊት ያገኘውን ተጠቅሞ ታላቁ ሐዋርያ በመልዕክቱ ላይ ጽፎታል።

አንድም ቅ/ጳውሎስ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ለተግሳጽና ለምክር ያስፈልጋሉ ብሎ ለጢሞቴዎስ አስተምሮታል [2ኛ ጢሞ. 3: 15] ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ አንዴ በተግባር አንዴ በመልዕክቱ እየፃፈ ስለ አዋልድ መፅሐፍት ጢሞቴዎስን አስተምሮታል።

አንድም ሐዋርያው ይሁዳ ስለ ቅ/ሚካኤልና ስለዲያቢሎስ ክርክር በመልዕክቱ ላይ ይነግረናል [ይሁዳ 1:8] ይህ ክርክር ግን በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ አልተፃፈም ፤ ታዲያ ሐዋርያው ይሁዳ ይህን ታሪክ ከየት አምጥቶ ነው የፃፈው?

እነሆ ታሪኩ እንዲህ ነው፦  ሊቀ ነብያት ሙሴ እጅግ ታዛዥና የዋህ ስለነበር ሀገረ ከንዓንን ለማየት ወደ ናባው ተራራ በወጣ ግዜ ሁለት መላዕክት በአረጋውያን ተመስለው መቃብር ሲቆፍሩ ሲያይ ላግዛቹ ብሎ መቆፈሪያውን ተቀበላቸው፤ እነሱም በመጨረሻ “ሰውየው በአንተ ልክ ነውና እስቲ ገብተህ ለካልን አሉት”  እሱም በየዋህነቱ ጉድጓዱ ውስጥ ገብቶ እንደተኛ እንደ እንቅልፍ አሸልቦት በዚያው ዐረፈ; መላዕክትም ቀበሩት። እስራኤላዊያን ሙሴን እጅግ ስለሚወዱት የሙሴን መቃብር እንደ ጣዖት እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን መቃብር ሰወረው፤ ነገር ግን ጠላት ዲያቢሎስ ሊያሳያቸው በመነሳቱ ቅዱስ ሚካኤል ተቃወመው; በመጨረሻም ቅዱስ ሚካኤል ዲያቢሎስን እግዚአብሔር ይገስጽህ ብሎ ከራሱም ሰወረበት።

ሐዋርያው ይሁዳ ይህን ታሪክ ያገኘው እርገተ ሙሴ ከሚባለው የትውፊት መፅሐፍ ነው።
Source፦ the Assumption of Moses
የሐዋርያው ይሁዳ መልዕክት
ቁጥር 8

እነሆ ቤተክርስቲያንም ሐዋርያት እንዳስተማሯት እኛን ታስተምረናለች! አለንና ወደ ኋላው ዞር እያለ “ታዲያ በዚህች ቤተክርስቲያን አትኮሩም እንዴ”? ብሎ ጠቀየቀን፤ ሁላችንም “ኧረ እንኮራለን” ብለን መለስንለት። የደስታ ስሜት ተነበበበትና እኔን የሚገርመኝ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? አለን ጓደኛችን፤

“ምን ገረመህ”? አልነው በልባችን፤
እንዲህ ብሎ ቀጠለልን፤

እኔን በጣም የሚገርመኝ ባሕረ ጥበብ የሆነችው ቤተክርስቲያን እያንዳንዱ ሥርዓትዋ በሚስጢር የተዋቡ መሆናቸው ነው! ኧረ ሰዎች ይህችን ጥበበኛ እናት በደንብ እንወቃት፤ ከጣራ እስከ ግድግዳዋ ያስተምረናል። እኛ ለማወቅ እንፈልግ እንጂ ይህች እናት እንደዘመኑ ሴቶች የተፈጥሮ ወተትን ነፍጋን አርቴፊሻል ወተት አትግተንም!

ከላም ወይም ከሌሎች የወተት አይነቶች ይልቅ የእናት ወተት ለህፃኑ ጠቃሚ ነው፤ በተለይ እናትየው በመጀመሪያ የምታጠባው ወተት ማለትም እንገር /colostrums/ የሚባለው ለህፃኑ ጤንነትና እድገት እጅግ ወሳኝ ነው። እኛም ከእናታችን ቤተክርስቲያን የመጀመሪያውን ወተት በጥምቀት አማካኝነት ተመግበናል። ይህ ልክ እንደ ህፃኑ ለጤንነታችንና ለእድገታችን እጅግ ወሳኝ ነው!

ደግ የሆነች እናት ቤተክርስቲያን አለን፤ ወተትዋን ለማጥባት የማትሰለች ደግ እናት! ጥምቀቱ ወተት ነው ልጅነትን ያሰጣልና፤ ቁርባኑ ወተት ነው ከኃጢአት ያነፃናልና፤ ተክሊሉ ወተት ነው የትዳራችን ውበት ነውና፤
ትምሕርቷ ሁሉ ግሩም ወተት ነው ያውም ለጤንነትና ለእድገት ወሳኝ የሆነ ጣፋጭ የእናት ወተት።

“የእናታችን ወተት ያስፈልገናል በሉ”!































Thursday, 19 January 2012

“ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ”

“Epiphany”
God Holy might, Holy living, immortal who was baptized in the Jordan & crucified on the cross have mercy up on us.

ባሕር አየች ሸሸችም፤
ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፤
ተራሮች እንደ አውራ በግ፤ ኮረብቶችም እንደ ጠቦት ዘለሉ፤
በእንስሳት በረት ተጨመረ ፤
የንጉሥንም እጅ መንሻ ተቀበለ ፤
ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕፃናት አለቀሰ።
በግልጥ ተመላለሰ፤ እንደ ሰውም ታየ፤
“በየጥቂቱ አደገ በሠላሳ ዘመን በዮርዳኖስ ተጠመቀ”
 ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ወመዝሙረ ዳዊት [መዝ 113: 3]

v  በሃገራችን ጥምቀት በግሩም ሁኔታ ይከበራል፤
ታቦታቱ ከመንበራቸው ወተው ውሃ ወዳለበት ሄደው ያድሩና ወደ መንበራቸው ይመለሳሉ። ይህ ለምን ይሆን? ቢሉ ምሳሌው ግሩም ነው፤ ይህም ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ የመጠመቁ ምሳሌ ነው ይህ በየትኛውም አለም የሌለ በሃገራችን ብቻ ያለ ድንቅ ሥርአት ነው።
v  ማየ ገቦ፦ ሀብተ ንጽህ ሀብተ ክቡር የሚሆን ቅዱስ
ሥጋውን ከኃጢአት የምንድንበትን ማየ ገቦን /ከጎኑ የፈሰሰውን ውሃ/ ሰጠን።
vጌታችን በእደ ዩሐንስ በባህረ ዩርዳኖስ ከለሊቱ በ10 ሰዓት
ተጠመቀ። ለምን ተጠመቀ ቢሉ ዲያቢሎስ አዳም ገብሩ ለዳያቢሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያቢሎስ ብሎ በሁለት ጽላት የእዳ ደብዳቤ ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል አስቀምጦት ነበረና ጌታችን በዮርዳኖስ ተጠምቆ ያንን የእዳ ደብዳቤውን ደመሰሰው። በሲኦል የነበረውን ደግሞ በእለተ አርብ ደምስሶታል፤ [በእኛ ላይ የነበረውን የእዳ ጽህፈት ደመሰሰው እንደሚል ቆላስይስ 2:11]

v                   ለመጀመሪያ ግዜ በዓለም ላይ ጥምቀትን የተጠመቀ ኢትዮጲያዊው ጃንደረባ [ባኮስ] ሲሆን ለመጀመሪያ ግዜ በዓለም ላይ ያጠመቀ ደግሞ ሐዋርያው ፊሊጶስ ይሆናል ማለት ነው።
      የአመነ የተጠመቀ ይድናል ማር16:16    ባኮስ ሲጠመቅ                                        
v  ጌታችን ስለምን ተጠመቀ ቢሉ አንድም ለቀድሶተ ማይ
/ውሃን ለመቀደስና/ ለቀድሶተ ጥምቀት ጥምቀትን ቀድሶ ለመስጠት ነው። አንድም ለምሳሌነት ነው፤ አንድም ዮርዳኖስ ወደ ሗላዋ ሸሸች የተባለው ትንቢት ለመፈጸም ነው። አንድም ለምን በ30 ዓመቱ ተጠመቀ ቢሉ አዳም የ30 አመት ጉልማሳ ሆኖ ተፈጠረና ገነት ርስቱን አጣት; በ30 አመቱ ያጣትን ገነትን ለመመለስ ጌታችን በ30 ዓመቱ ተጠመቀ። አንድም ስለምን ወንድ በ40 ቀን ሴት በ80 ቀን ይጠመቃሉ ቢሉ አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀኗ ገነትን አግኝተዋልና እኛም መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ በ40ና 80 ቀናችን እንጠመቃለን። 
vAnna Baptist [ዳግም አጥማቂዎች]
እነዚህ የፕሮቴስታንት ክፍሎች ሲሆኑ በሥላሴ አንድነትና ሶስትነት ስለማያምኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ከተጠመቅን በሗላ ዳግም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ አለብን የሚሉ ናቸው፤ ጥምቀት ግን አትደገምም አትከለስምም
“አንድ ጌታ አንዲት ጥምቀት” እንዲል ኤፌሶን [4:4]
 


ጾመ ገሃድ፦ በጥምቀት ቀን ጾም ፈጽሞ አይጾምም፤ ጥምቀት እሮብና አርብ ቢውል እንኳን አይጾምም፤

ጥምቀት እሮብ ቢውል ማክሰኞ፤ አርብ ቢውል ሐሙስ ይጾማል።

ሐሙስ ቢውል ማክሰኞ፤ ቅዳሜ ቢውል ሐሙስ ይጾማል። ይህም የገሃድ ጾም ይባላል።

ጥያቄና መልስ፦

ለመዳን የግድ መጠመቅ ያስፈልጋል፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ስለሚል ማር16:16፤ ይህ ከሆነ ፈያታዊ ዘየማን ተጠምቆ ነው ወይስ እንዴት ነው ገነት የገባው?


መልስ

የድሮ ክርስቲያኖች ለጥምቀት በሚሄዱበት ግዜ ገና በመንገድ ላይ እያሉ ሰማዕትነት ይቀበሉና በደማቸው ይጠመቁ ነበር፤ እነዚህ ደመ ሰማዕታት ሲባሉ ዋጋውም ከፍተኛ ነው 1ኛ ዩሐ. 5:6


ፈያታዊው ዘየማን “የጌታ ደም ደመ ጥምቀት” ሆኖለት
ወደ ገነት ለመግባት
የመጀመሪያው ሰው ሆኗል!!

ወ   ሥ   በ  ሐ  ት  ለ  እ  ግ  ዚ  አ  ብ  ሔ  ር
[ተክለ መድህን]


Monday, 16 January 2012

“Epiphany”



v     ደውል ተደወለ!

         ካህናቱ ተሰበሰቡ!

         መሪ ጌቶችም ለማህሌት ተነሱ!

         የሰ/ት/ቤት መዘምራን ለመዝሙር ከበሮውን አነሱ!

         ሕዝበ እግዚአብሔርም ተጠራ!

         እነሆ ጥምቀትበከተማችን በለንደን ለመጀመሪያ ግዜ  እጅግ ለየት ባለ ሁኔታ ሊከበር ነው!

         ቅ/ሥላሴ ፣ ጽ/ጽዮን ፣ ቅ/ገብርኤል ቤተክ በአንድነት በመሆን በአውሮፓ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቅ     
         በዓል ያከብራሉ፤


v     ቀንና አድራሻ፦

ከአርብ 20 Jan 7pm – ቅዳሜ 21 Jan 12 pm

St Pancras church;


Euston RD
London
NW1 2BA

Nearest station Euston /northern & Victoria line/


v     ይህ ሥርአት ግሩም ነው! እስራኤል አታውቀው አሜሪካም የላት እንግሊዝም አላወቀችው፤ እነሆ አያምልጦት! ከወገናችሁ ጋር በዓሉን ያሳልፉ፤ ኑ በአንድነትም እናክብር !!! ልጆቻችሁን አምጡና የሃገራቸውን ሐይማኖትና ባህላቸውን አሳውቁ! ካሜራችሁም በዛች ቀን ውብ የሆኑ ፎቶዎችንና ቪዲዮችን ለማንሳት እነሆ ብዙ ስራ ይጠበቅበታል!

v     በዚህ በዓል ላይ BBC እና የተለያዩ የእንግሊዝ ባለስልጣኖች ፣ የሃገሪቱ ነዋሪዎች ይገኛሉና ሃገራችንን በመልካም ጎኑ እናስተዋውቅ።

v     በለንደን የምትኖሩ ሁላችሁም ባህላዊ ነጭ ልብሳችሁን ለብሳችሁ ኑ ብላ ቤተክርስቲያን ትጣራለች!
          ከለንደን ውጪ የምትኖሩ ደግሞ ይህን ታላቅ በአል በቅርቡ you Tube ላይ ይጠብቁ!