አስከናፍር የሚባል ፍቅሩ ፍፅምት የሆነች ደግ ሰው ነበር። ይህ ደግ ሰው ነገርን ሁሉ በቅን ልቡና የሚያስብ ነው። ይህን ደግነቱን ያዩ በቁጥር 13 የሆኑ የበረሃ ሽፍቶች ሊዘርፉት አሰቡና የባህታዊያን ልብስ ለብሰው ከልብሳቸው ውስጥ ጩቤ ሾተል ጎራዴ ታጥቀው ወደ አስከናፍር ቤት ገሠገሡ። አስከናፍር አሥራ ሦስቱን ሽፍቶች ሲያያቸው የመነኮሳት ልብስ ለብሰዋል። ሲቆጥራቸው 13 ስለሆኑ ጌታ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርት ጋር ቤቴ መጣ ብሎ እጅግ ደስ አለው። ወዲያው እግራቸውን አጠበ። አንድ ሽባ ልጅ ነበረውና በእግራቸው እጣቢ ልጁን አጠመቀው። ከእምነቱ የተነሳ ልጁ ዳነለት። ይህን ጊዜ አስከናፍር ይበልጥ ደስ አለው። ከእናንተ ውስጥ ክርስቶስ የቱ ነው? ሐዋርያው ጴጥሮስስ? ዮሐንስን አሳዩኝ? እያለ መጠየቅ ጀመረ። ይህን ጊዜ በሽፍቶቹ ያደረው ክፉ መንፈስ ሸሸ። ሽፍቶቹም ወዲያው መናዘዝ ጀመሩ። ፩ድ ፩ድ መስፈሪያ ምስር ይዘው በረሃ ገቡተው ለቁመተ ሥጋ ብቻ ጥቂት ምስር እየበሉ ለሰላሳ ዓመት ተጋደሉ።
በዚያን ዘመን አንድ አላዊ ንጉሥ ጣዖት ካላመለካችሁ ብሎ ሕዝቡን አስጨነቀ። እነዚያ አስራሦስት ሽፍቶች ይህን ነገር ሲሰሙ ወደ ንጉሡ ገሠገሡ። በንጉሡ ፊት ክርስትናቸውን መስክረው ሰማዕትነትን ተቀበሉ። ወዲያው እንደ ቅ/ጳውሎስ የሰማይ አክሊልን ተሸለሙ። አስራ ሦስቱ ሽፍቶች ይህን የሰማዕትነት ክብር የተቀበሉት በዚያ ደግ ሰው በአስከናፍር በጎ ሕሊና ምክንያት ነበር። ፍፁም ፍቅር ሽፍቶችን ሰማዕት የማድረግ ብርቱ ኃይል አለው!
ይህ ታሪክ የተተረከበት ምክንያት አለ። ነገሩ ወዲህ ነው፦
“በካብ ላይ ብሰራ እባብ መከራ ፣ በዛፍ ላይ ብሰራ አሞራው መከራ ፣ በምድር ብሰራ እረኛው መከራ የት ውዬ የት ልደር አለች ወፍ!”
ልክ እንደዚህች ወፍ ሠላም አጥታ የተቸገረች አንዲት እናት አለች። ይህችውም ቤተክርስቲያን ናት።
በጥንታዊቷ በለንደን ከተማ ሲያዩት ግርማ ሞገስ ያለው መንፈስን የሚያድስ የቅስት ማርያም ቤተክርስቲያን አለ። ይሁንና በስም ብቻ ኢትዮጵያዊ የሆኑ “ፖለቲከኞች” ተነሱና “ቤተክርስቲያኒቷ በቅ/ሲኖዶስ ሳይሆን እንደ ካምፓኒ በቦርድ መመራት አለባት” አሉ! ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አይደል ተረቱ። ቤተክርስቲያኒቷ በሕዝቡ ገንዘብ ስለተገዛና ወጪ ስለሌለባት የምዕመኑ የሙዳይ ምጽዋት ሁሉ የፖለቲከኞቹ ኪስ ማሞቂያ ነበር። ይህም አልበቃ ሲል ጭራሹን ዐይን ያወጣ ጥያቄ ጠየቁ። ያደቆነ ሰይጣን ሳቀስ አይቀርም አይደል ተረቱ። ይህች ቤተክርስቲያን ያለፉት ፓትርያርክ የአቡነ ጳውሎስን ስም በቅዳሴ ላይ አንጠራም በሚሉ ምክንያቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት ራስዋን አግልላ ነበር። በዚህ ምክንያት በለንደን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የምናገለግል የሰ/ት/ቤት መዘምራንና ካህናት ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን ማገልገል ጀመርን። አሁን የቅ/ሥላሴን ቤተክርስቲያን የምንጠቀመው በክራይ ነው ። ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሕንጻ አጥቶ ሲቸገር ቅ/ማርያም ቤተክርስቲያን ደግሞ ሕንጻው ካምፓኒ ይሁን ተባለ! እናላችሁ አሁን የቤተክርስቲያኑ ዕጣ ፋንታ ምን ይሁን? እየተባለ ነው። ሕዝቡ ሕገ ቤተክርስቲያንን ያውቅ ዘንድ ጉባኤ ተዘርግቷል።
በለንደኑ ጉባኤ ዲያቆን ብርኃኑ አድማሱ እና ዘማሪ ምንዳዬ ተጋብዘው ነበር። ጉባኤው ገና ሲጀመር ሽበት ጣል ጣል ያለባቸው አንድ ሽማግሌ ተነሱ። ሁላችንም ፍጥጥ ብለን አየናቸው። ሽማግሌው ጥያቄ አለኝ አሉ። እሺ አልናቸው። “አስተማሪ ከኢትዮጵያ ለምን መጣ? ዲያቆን ብርኃኑ አድማሱ ስለቤተክርስቲያናችን መጥፎ አስተሳሰብ አለው ለምን መጣ?” ብለው ክርክር አመጡ። ድንገት አንዱ ከመሃል ተነሳና ከሽማግሌው ጋር ተደመረ። ሴቶቹም ከማን እናንሳለን አሉና ተነስተው መጨቃጨቅ ጀመሩ። መምህር ታሪኩ እና መሪጌታ አዲስ ለምን ተባረሩ? ሲሉ ወገንተኝነታቸውን አሳይተዋል። መምህር ታሪኩ በቅርቡ ከኢትዮጵያ የመጣ ሰባኪ ሲሆን ፖለቲከኞቹ እሱን ሊጠቀሙበት በምድረ እንግሊዝ እንዲቀር ይፈልጋሉ የሚል ሀሜታ አለ።
የለንደን ቅድስት ማርያም ሰ/ት/ቤት እውነት በእውነት ምስጋና ይገባቸዋል። ጨጓራቸው እስኪላጥ ለዘመናት ከፖለቲከኞቹ ጋር ተከራክረዋል። “ሕዝቤ እውቀት በማጣት ጠፋ” እንዲል ሕዝቡ የቤተክርስቲያንን ሕግ ያውቅ ዘንድ ዲያቆን ብርኃኑ አድማሱ እንዲያስተምር ሁኔታውን ያመቻቸው ሰ/ት/ቤቱ ነበር። ሰ/ት/ቤት የቤተክርስቲያን የጀርባ አጥንት የተባለውን ፈጽመዋልና እግዚአብሔር ያበርታቸው። ፖለቲከኞቹ ሲዛናኑብን አንድ ወጣት ቦግ አለበትና “ብታሰርም ልታሰር ጥርስሳችሁን አረግፋለሁ” ብሎ ግብግብ ጀመረ። ነገሩ ቢያናድደው ቦክስ ካልገጠምኩ አለ። በእርግጥ ትዕግስት ያስፈልጋል። አለበለዚያማ ክርስትናው የቱ ላይ ነው?
እኔን በጣም የገረመኝ ሕዝቡ ተቀምጦ ፖለቲከኞች እንደልባቸው ሲናገሩ በማየቴ ነው። ቆሞስ አባ ግርማ ክርክሩን ለማብረድ እግዚአብሔር ይመስገን እያሉ አዘመሩን። ዛሬ ዛሬ ዘመኑ ሰልጥኖ ይሁን ሰይጥኖ ከሕዝብ ፣ ከካሕናት፣ ከቤተክርስቲያን በላይ የሆኑ ፖለቲከኞች በቤተክርስቲያን ላይ እየተዝናኑባት ነው። በእርግጥ ዘመኑ ለቤተክርስቲያን የከፋ ዘመን ኾኗል። በሐዋርያትም ዘመን የሐሳብ ልዩነት ነበር፤ አሁንም አለ ወደፊትም ይኖራል። እኛ ከመላዕክት ወገን አይደለንምና የሐሳብ ልዩነት ይኖራል። ልዩነቱን በፍቅር መፍታት ይገባል። ከላይ እንዳየነው በቤተክርስቲያን ውስጥ ሞቅ ያለ ክርክር ነበር። የሠላም መርከብ በሆነችው ቤተክርስቲያን ኹከትና ረብሻ ነበር። ነገሩ ሁሉ የገረማቸው መምህር ዲ/ን ብርኃኑ “እንኳን በቤተክርስቲያን በገበያም እንዲህ መሆን የለብንም” ብለዋል። ዲያቆን ብርኃኑ አድማሱ ቦክስ ካልገጠምን ያሉትን ሁሉ በወንጌል አረጋጉ። የሻከሩ ልቦችን በወንጌል አለሰለሱት። ፍፁም ጥላቻን ወደ ፍፅምት ፍቅር ቀየሩት። እንደነ ዲያቆን ብርኃኑ አድማሱ እና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የመሰሉ ደገኛ ሰባኬ ወንጌል የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን።
የተሳሳቱትን ይበልጥ ማሳሳት በጥላቻ የመጡትን ይበልጥ መገፋፋት የቤተክርስቲያን ሥርዓት አይደለም። ፍቅር ያሸንፋል። ፍቅር ብርቱ ነውና ሁሉንም ይገዛል። ፍቅር ለክፉ የመጡትንም እንኳን እግዚአብሔር ባወቀ ልባቸውን አራርቶ ወደ በጎ ይቀይራቸዋል ሲሉ ዲያቆን ብርኃኑ አድማሱ መልካም ወንጌል ሰብከዋል። ልበ አምላክ ዳዊት “አንተ ኃጢአትን ብትቆጣጠር በፊትህ ማን ይቆማል” እንዳለው ሁላችንም ቆመን “በከመ ምህረትከ አምላክነ ወአኮ በከመ አበሳነ” አምላካችን ሆይ እንደ ቸርነትህ ነው እንጂ እንደበደላችን አይሁን ተባባልን።
ፍፁም ፍቅር ሽፍቶችን ሰማዕት የማድረግ ብርቱ ኃይል አለው! ለጥቅም ለኪሱ ለፖለቲካው የመጣውን በፍፁም ፍቅር የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ይሆን ይሆናል ማን ያውቃል? ቤተክርስቲያንን ሊዘርፉ የመጡ ፖለቲከኞች ያን ደግ ሰው አስከናፍርን ሊዘርፉ እንደመጡት ሽፍቶች ቢሆኑስ ማን ያውቃል? እንደ አስከናፍር ሁሉን በፍቅር መግዛት ይቻላል።
- 294 people like this.
- Yad Tit kale hiwot yasemlin Egziabeher lehulachin asitaway libona yisten bet kirsitnachinin kemifetatenat kifu menifes egziabeher yitebikilin!
- Sihene Siraj tarikun betam wededkut.Balmeterater Yemenadergew wede bogo yelewetal. Bego hilina YeseTen, amen